የዜጎች የጅምላ እሥር ለመንግሥት ምን ይረባዋል?

Date:

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን የዜጎች ጅምላ እሥራት እየተበራከተ መጥቷል፡፡ የእሥራቱ ዋነኛ ዓላማ ደግሞ ፖለቲካ ነው፡፡ እንደሚታወቀውና በርካታ ጥናቶች እንደሚያመላክቱትም አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት እሥረኞች የፖለቲካ እሥረኞች ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ በዚህ ዙሪያ ኢትዮጵያችን ግንባር ቀደም የምትኾንበትን ታሪክ ለማስመዝገብ እሽቅድምድም ውስጥ የገባች ይመሥላል፡፡  በሀገራችን ታሪክ ከፍተኛ የእሥር ታሪክ የነበረው በደርግና በኢሕአዴግ ዘመናት ነበር፡፡ የአነርሱ ወራሽ የኾነ የሚመሥለው የብልጽናው መንግሥትም ሪከርዱን ለማሻሻል አበክሮ እየሠራ ይመሥላል፡፡ የደርግ መንግሥት ‹‹ጸረ አብዮተኛ›› እያለ ዜጋውን ሁሉ አሥሮ ሲረሽን አሥራ ሰባት ዓመታት መሰንበት ችሏል፡፡ የእርሱን ፈለግ ተከትሎ መንበረ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው የኢሕአዴግ መንግሥትም ፖለቲከኞችን ከመረሸን ይልቅ ስቃዩ የበዛ እሥር ይመጥናቸዋል በሚል ለ27 ዓመታት ጽዩፉን ተግባር ሲፈጽም ባጅቷል፡፡

በተለይ ወደ መጨረሻው አካባቢ በርካቶችን ከማሠሩም በላይ አንዳንድ እሥር ቤቶች ቋንቋ እስኪቀየር ድረስ ተመሳሳይ ማንነት ያላቸው ዜጎችን በፖለቲካ እይታቸው ሲያጉር እንደነበር ብዙዎች ያስታውሳሉ፡፡ ከአቅም በላይ ኾኖበት ከእሥር ሲለቅም ‹‹አይደገምም›› የሚል ቲሸርት ማልበሱ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ የኾኖ ኾኖ በእርሱ እግር የተተካው የብልጽግና መንግሥት ከጅምሩ እሥር ቤቶችን ባዶ በማድረግ ‹‹ሳናጣራ አናሥርም›› ሲል ቃል ገብቶ አሁን ላይ በሺህ የሚቆጠሩ እሥረኞችን ወደ ማጎሪያ ካምፕ እያጋዘ ነው፡፡ በዘመቻ በህወሓት ዘመን የተጀመረውን የጅምላ እሥር በተሻለ ደረጃ አሳድጎ በዘመቻ ‹‹የዐይንህ ቀለም አላማረኝም›› ያለውን የአንድ ብሔረሰብ ተወላጅ እየለቀመ ማጎሩን ተያይዞታል፡፡ ባለንበት ወቅት እሥር ቤቶች ብቻ ሳይኾኑ ትምህርት ቤቶችም ጭምር የግዞት ቤት መኾናቸውን እንኳንስ ሌላ መንግሥትም መካድ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

የእሥር ሰለባ የሚኾኑት ‹‹ከሊቅ እስከ ደቂቅ›› እንዲሉ ከሎተሪ አዟሪ እስከ መጽሐፍ ቸርቻሪ፤ ከነጋዴ እስከ ባጃጅ ነጂ፤ ከጋዜጠኛ እስከ ፖለቲከኛ፤ ከመምሕር እስከ ኃይማኖት አባት ሁሉንም ያጠቃለለ ነው፡፡ አንዳንዴ ጥቅል ሁኔታው ሲታይ ታዳኙ ኃይል የሀገሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማኅበረሰብ በመኾኑ እንጅ እንደአሣሪዎቹ አካሄድ ብሔረሰቡ ጠቅላላ እሥረኛ ይኾን ነበር የሚሉ ወገኖች የተፈጠሩትም ለዚህ ነው፡፡ የኾኖ ኾኖ ይህ ጉዳይ ያለው ፖለቲካዊ አንድምታ ከፍ ያለ መኾኑ እሙን ነው፡፡ በአንድ በኩል አፋኙ ኃይል ሰላማዊ ዜጎችን በማሠር ለጥቂት ጊዜ በፍርሐት ሸብቦ ሰላም ያሰፈነ ቢመስለውም፣ በሌላ በኩል ታፋኙ ኃይል ይበልጥ ትግሉን የሚያጠናክርበትን ማታገያ ይፈጥርለታል፡፡ ስለዚህ ይህ የጅምላ እሥር ተጠናክሮ የሚቀጥል ከኾነ በቀጣይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ከባድ ነው፡፡

ይህን የእሥር ጉዳይ አስመልክቶ የተለያዩ የሲቪክና የፖለቲካ ተቋማት መግለጫዎችን አውጥተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ(ኢሰመጉ) ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎች በርካታ እሥሮች እየተፈጸሙ እንደሚገኙ የገለጸ ሲኾን  እነዚህ እሥሮች የሕግ ሥነ ሥርዓትን ያልተከተሉ እና የሚታሠሩ ሰዎችም በተገቢው ሰዓት ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ አመላክቷል፡፡ በዚህም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የኾኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የኾኑት ዶ/ር ካሳ ተሻገር ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ በፖሊስ ተይዘው በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንደሚገኙ፣ የአልፋ ሚዲያ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን መሥራች እና ባለቤት የኾነው ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው፣ የጄነራል ተፈራ ማሞ ባለቤት የኾኑት ወ/ሮ መነን ኃይሌ የተያዙበት ምክንያትም ከእዚህ ቀደም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ባስተላለፏቸው መልእክቶች እንደኾነ እና ከእነዚህ እሥሮች በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ የጅምላ እሥሮች እየተፈጸሙ መኾኑን ጠቁሟል፡፡ ኢሰመጉ አክሎም እሥሩ በአስቸኳይ እንዲቀርና የታሣሪዎችም ሰብዓዊ መብት ሕጋዊ በኾነ መልኩ እንዲጠበቅ አሳስቧል፡፡ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም (ኢሰመኮ) ከኢሰመጉ ጋር አንድ ዓነት ይዘት ያለው መግለጫ አውጥቷል፡፡ የጅምላ እሥር ሂደቱንም አውግዟል፡፡

የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ በኾችው ወልቂጤ ከተማም ማንነት ተኮር እሥር እና አፈና እንዲቆም የከተማው የአገር ሽማግሌዎች እና የወጣት ተወካዮች የመንግሥት አመራሮችን መጠየቃቸው ከቀናት በፊት ተሰምቷል። በከተማዋ ረዥም ዘመን ከኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች እየተለቀሙ በጅምላ ሲታሠሩ የሀገር ሽማግለሌዎች ለምን ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች የዘፈቀደ እሥር፣ ሰዎች ከታሠሩ በኋላም ለቤተሰቦቻቸው አድራሻቸውን አለማሳወቅ ድርጊት በተለይም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ በበኩሉ በእሱ ስር ከአዋጁ በኋላ የተያዙ ተጠርጣሪዎች 23 ብቻ እንደኾኑ ከእነስም ዝርዝራቸው በፎቶ አስደግፎ ይፋ አድርጓል። በቅርቡ የኮማንድ ፖስቱ መርማሪ ቦርድም የታሣሪዎችን ሰብዓዊ አያያዝ ጉብኝት ባደረገበት ወቅትም ቅኝት ያደረገው በእነዚሁ 13 ግለሰቦች ዙሪያ ብቻ ነበር፡፡

እውነታው ግን በሺህ የሚቆጠሩ ታሣሪዎች ናቸው በየእሥር ቤቱና ትምሕርት ቤቱ ያሉት፡፡ እነዚህ ሁሉ ታሣሪዎች አብዛኞቹ የታፈሱት ከፍ ሲል እንደተገለጸው በጥፋታቸው ሳይኾን በማንነታቸው ነው፡፡ የኾኖ ኾኖ ሰሞኑን ደግሞ እነ ጋዜጠኛ ዓባይ ዘውዱ እና አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ በርካታ እሥረኞች  ወደ አዋሽ አርባ መወሰዳቸው እየተነገረ ይገኛል። እነዚህ እሥረኞች ሰሞኑን “ፍርድ ቤት” ይቀርባሉ የተባለ ቢኾንም ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው በፊት ወደ አዋሽ አርባ መወሰዳቸው ተነግሯል፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ስደተኞች በሳውድ አረቢያና የመን ድንበር ላይ በጸጥታ ኃይሎች በስናይፐርና ሞርታር የጅምላ ግድያና እሥር እየተፈጸመባቸው መኾኑን ሚክስድ ሞኒተሪንግ ሴንተር ገልጿል፡፡ በስደተኞች ጥናትና ክትትል ላይ የሚሠራው ሚክስድ ሞኒተሪንግ ሴንተር የተሰኘው ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ለሚድል ኢስት አይ እንደገለጸው፤ የኢትዮጵያውያን የጀምላ ግድያና ጾታዊ ጥቃት እንዲሁም እሥር እንደቀጠለ ነው፡፡ አሁን ላይ ይህ በስደት ሀገር የኾነው አስነዋሪ ሰብዓዊ ጥሰትና ድርጊት በሀገራችን ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኝ ይመስላል፡፡ እየታየ ያለው የጅምላ እሥር እና ሰብዓዊ ጥሰት በቶሎ የማይቆም ከኾነ ይዞት የሚመጣው አደጋ ከፍ ያለ ሊኾን እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ እሥሩ ማንነት ተኮር መኾኑ ደግሞ አደጋውን ከባድ ያደርገዋል፡፡ የብልጽግናው መንግሥት ከጭፍን ጉዞውና የእሥር መንገዱ ወጥቶ ቀደም ሲል በገባው ቃል መሠረት አጣርቶ ለማሠር ቢጥር መልካም ይኾናል የሚለው አስተያየት ገፋ ብሎ እየተደመጠ ያለውም ለዚህ ነው፡፡ በተለይ በፖለቲከኞችና በጋዜጠኞች ብሎም በአክቲቪስቶች ላይ ከሚደረገው እሥርም በላይ በለፍቶ አደር ዜጎች ላይ የሚደረገው ጅምላ እሥር በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ በእነዚህ እሥረኞች ላይ የሚወሰደው ማናቸውም እርምጃ በሕግም በሞራልም ተቀባይነት የሌለውና ሕዝብን እንደሕዝብ ለማዋረድና ለማቅለል ሲባል የሚደረግ እሥር ከመምሰል የተሻገረ እርባና የሌለው በመኾኑ አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ በአፋጣኝ መፍታትና እየተካሄደ ያለውን አፈሳም ማቆም ለነገ የማይባል ሥራ መኾኑን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አርሰናል ከቦርንማውዝ በጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ

በ32ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ቀን...

በአሜሪካ እና ኢራን ድርድር ላይ የሚነሱ አራት ቁልፍ ጥያቄ

በፓኪስታን የሚደረገው የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር እየተጠበበፓኪስታን ነገር ግን...

መንገዳችን ረጅም፣ ጉዟችን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል...

የተመድ ዋና ጸሐፊ ኢራን እና አሜሪካ “በቅን ልቦና” ወደ ድርድሩ እንዲገቡ ጠየቁ

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሜሪካ እና ኢራን...