በሥር ፍርድ ቤቶች ከረዳት ዳኝነት ጀምረው እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከ20 ዓመታት በላይ የሠሩ የዳበረ ዕውቅትና ልምድ ያላቸው ሦስት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ ሥራቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸው ታወቀ፡፡
ሦስቱም ዳኞች ለፌዴራል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ባቀረቡት ተመሳሳይነት ባለው የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ፣ ‹‹በተሰጠኝ ኃላፊነት አገሬንና ሕዝቤን አቅሜ በፈቀደ መጠን አገልግያለሁ፡፡
አሁን ግን በግል ምክንያት በሥራዬ መቀጠል የማልችልበት ሁኔታ ስለተፈጠረ ከዳኝነት ሥራ ለመልቀቅ ተገድጃለሁ፤›› በማለት የመልቀቂያ ደብዳቤ አቅርበዋል፡፡
ጽሕፈት ቤቱም ጥያቄያቸውን በመቀበል፣ መልቀቂያ ያቀረቡት ሦስቱም ዳኞች በሥራ ላይ በነበሩበት ጊዜ፣ በሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት ተቀጥተው የማያውቁና መልካም ሥነ ምግባር እንደነበራቸው፣ በጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ በአቶ ቡላ ዋጋሪ በርቶላ ፊርማ የተረጋገጠ ማስረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከፌደራል ፍርድ ቤት ስራቸውን የለቀቁት ዳኞች አቶ ሀብታሙ ዕርቅይሁን አስፋው፣አቶ ኑረዲን ከድር ሱልማንና፣አቶ ብርሀኑ መንግስቱ ቱሉ ናቸው።
