የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እያከናወናቸው ያሉትን የቤት ልማት፣ የኢንቨስትመንት ስራዎች ይበልጥ ለማጠናከር እና የፋይናንስ አቅሙን ለማሳደግ ከሲንቄ ባንክ ጋር በተለያዩ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።
ኮርፖሬሽኑ በአገሪቱ የኢኮኖሚና የማህበራዊ እድገት ላይ እያበረከተ ያለውን አወንታዊ ተፅዕኖ ይበልጥ ለማስፋት እና ዘመናዊ የቤት ልማት ስራዎችን ተደራሽ ለማድረግ ከሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያለውን አጋርነት እያጠናከረ ይገኛል።
በዚህም መሰረት ዛሬ በተፈረመው ስምምነት ኮርፖሬሽኑ ለሚያከናውናቸው ሰፊ የቤት ልማት ፕሮጀክቶች የሚሆን የፋይናንስ አቅርቦት ማመቻቸትንም ያጠቃልላል። ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ ተቋማት በሌሎች ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ በቅንጅት ለመስራት ተስማምተዋል።
በዚህ የስምምነት ስነ-ስርዓት ላይ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ረሻድ ከማል እና የሲንቄ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ንዋይ መገርሣ እንዲሁም የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
በወቅቱም የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ረሻድ ከማል እንደገለጹት፤ ይህ ስምምነት ኮርፖሬሽኑ የጀመራቸውን ግዙፍ የቤት ልማት ፕሮጀክቶች በላቀ የፋይናንስ አቅም ለማገዝ እና የኮርፖሬሽኑን ተወዳዳሪነት ይበልጥ ለማሳደግ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
