የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጠንካራ ተፎካካሪነት ይልቅ ወደ ግልና ቡድን ግንባታ ዝቅ ብለዋል ሲል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግሯል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፀሐፊ አቶ ደስታ ዲንቃ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ “በኢህአዴግ ጊዜ ቢያንስ ጠንካራ ተፎካካሪ የሚባሉና ኢህአዴግ ራሱ የሚፈራቸው ፓርቲዎች ነበሩ፤ ስልጣን ባይሰጣቸው እንኳ የሚያነሱትን ሃሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ይሯሯጥ ነበር” ያሉ ሲሆን “በአሁኑ ጊዜ ግን የፖለቲካ ፓርቲዎችም የፖለቲካ መሪዎች የሚባሉትም አሁን ራሳቸውንና ቡድናቸውን ወደ መገንባት፣ ወደ ግልና ቡድን ጥቅም ዝቅ ያሉበት ሁኔታ ነው የማስተውለው” በማለት ተናግረዋል።
በፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ በትብብር ላይ የተመሰረተ ፉክክር ለማድረግ ራሳቸውን አዘጋጅተው ፖለቲካን የመስራት ሁኔታ እንደማይስተዋል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፀሐፊው ገልፀዋል። የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት አለበት በሚለው ላይ ሁሉም ቢስማሙም፣ ነገር ግን ‘ባይሰፋም ችግር የለም’ የሚሉ የመንግስትን ስራ ብቻ የሚደግፉ አሉ በተጨማሪም ምህዳሩ ቢሰፋም፣ ባለበት ቢቀጥልም ችግር የሌለባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችም አሉ በማለት አቶ ደስታ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እምብዛም በመርህ ላይ የተመሰረተ ትብብርና ግንኙነት እንደማይስተዋል ገልፀው፣ የተከፋፈለና አንዱ ሌላውን የማዳመጥ ባህል ያልዳበረ ስለሆነ ቤታቸውን ዘግተው ነው የተቀመጡት ብለዋል።
