✍️✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)
♦️ጀግናዋ አትሌት ፅጌ ዱጉማና አትሌት ሳሮን በረሄን ጨምሮ በርካታ አትሌቶች ቪዛ ተከለከሉ
♦️ዶክተር አያሌው ጥላሁን፣መሐሪ ነጋሽ ቪዛ በመከልከላቸው ቡድኑ ያለ ህክምና ባለሞያና ያለ ኮሚኒኬሽን ለመጓዝ ተገዷል
♦️ሶስት የስፖርት ጋዜጠኞችም ዕድሉ ቀድሞ ስላልተሠጣቸውና በፌዴሬሽኑ ባለመታገዛቸው እነሱም ከፖላንድ ቀርተዋል
♦️ውጤታማው አሠልጣኝ ህሉፍ ይህደጎና ሁለት አሠልጣኞችም ቪዛ ተከልክለው ከጉዞ ውጪ ሆነዋል
♦️ጀግናዋ አትሌት መሠረት ደፋር እንደ ናንጂንግ(ቻይና)ሁሉ አሁንም ፌዴሬሽኑን በመታደግ ታሪክ የማይረሳው ውለታ ውላለች
♦️♦️በመጨረሻም 6 አትሌቶች 1 የቡድን መሪ፣1 አሠልጣኝና የፅ/ቤት ኃላፊው ዛሬ ምሽት ይጓዛሉ
ከ150 ሀገሮች የተውጣጡ ከ700 በላይ አትሌቶች ከ26 በላይ በሆኑ ዲሲፒሊኖች ይሳተፉበታል በሚል በመላው አለም በጉጉት የሚጠበቀው 21ኛው የአለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና የፊታችን ዓርብ በፖላንድ በይፋ ይጀመራል።
በዚህ ውድድር የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን አትሌቶች፣አሠልጣኞችና ባለሙያዎች ቪዛ በመከልከላቸው 6 አትሌቶች 1 የቡድን መሪ፣1 አሠልጣኝና 1 የፅ/ቤት ኃላፊን በቴክኒክ ባለሙያ ስም በመያዝ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ህክምና፣ያለ ማሳጂስትና ያለ ኮሚኒኬሽን ባለሙያ ዛሬ ምሽት እንደሚጓዙ ተረጋግጧል።
የሀገር ውስጥ ውድድር ለሆነው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና የተሠጠውን ያህል በስራ አስፈፃሚ ደረጃ እምብዛም ትኩረት ያልተሠጠው የፖላንዱ የአለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ላይ ተሳታፊ የሆኑ ሀገራት ተፎካካሪያችንን ኬንያን ጨምሮ አትሌቶቻቸውን ቀድመው ያሳወቁና ወደ ውድድሩ ስፍራ ያቀኑ ሲሆን በውድድሩ ለአሸናፊነት ከፍተኛ ግምት የተሠጠው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ግን የአውሮፓን ቪዛ ለማግኘት ከ45 ቀናት በላይ እንደሚወስድ እየታወቀ በአሜሪካ ከደረሠው ትምህርት በመውሠድ ቀድመው ማመልከትና ማጠናቀቅ ሲገባቸው እንደ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚና እንደ ፅ/ቤት የተሠራ ስራ ባለመኖሩ ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ እስከ ቀኑ 11:00 የፖላንድ ኤምባሲን ደጅ በማየትቪዛ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም የቪዛ ማመልከቻቸው ውድቅ በመሆኑ ጥቁት የማይባሉ አትሌቶች፣አሠልጣኞችና ባለሙያዎች ከውድድሩ መቅረታቸው ተረጋግጧል።
በዚህም መሠረት የፓሪስ ኦሎምፒካ የብር ሜዳልያ ባለቤቷን ጀግናዋን አትሌት ፅጌ ዱጉማ(ነገ በድጋሚ ሊሞከርላት እንደሆነ ተሠምቷል)፣የፔሩ ሊማ የወጣቶች ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊዋ ሳሮን በርኸ፣አትሌት ሞሲሳ ስዩም እና አትሌት ሐረገወይን ካዕላዩ ኤምባሲ ቢገቡም የቪዛ ማመልከቻቸው ተቀባይነት ባለማግኘቱ ከጉዞ መቅረታቸው ተረጋግጧል።
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ከውጤታማ አትሌቶች ጀርባ ያለው፣የትራክ ንጉስነቱን በውጤቱ ያረጋገጠው አሠልጣኝ ህሉፍ ይኽደጎ አራት አትሌቶችን ለሻምፒዮናው ያስመረጠ ብቸኛው አሠልጣኝ ቢሆንም እሱም ዛሬ ኤምባሲ ቢገባም የቪዛ ጥያቄው ውድቅ በመሆኑ ከፖላንዱ ጉዞ ውጪ ሆኗል።ከአሠልጣኝ ህሉፍ ሌላ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሠልጣኝ ሽባባውና የሸገር ሲቲው አሠልጣኝ ለውድዴሩ ቢመረጡም ፌዴሬሽኑ ምንም አይነት ጥረት ሳያደርግላቸው፣ኤምባሲ እንኳን እንዲገቡ ሳይደረግ ከጉዞ ውጪ ሆነዋል።
የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ፣ከታላላቅ አለም አቀፍ ውድድሮችና አትሌቶች ጀርባ የሚገኙት በሙያው የከፍተኛ ልምድና ዕውቀት ባለቤት የሆኑት ዶክተር አያሌው ጥላሁን፣ማሳጂስት(ፊዚይቴራፒስት)የሺ ጉልላት እና የፌዴሬሽኑ የኮሚኒኬሽን(ህዝብ ግንኙነት)ኃላፊ የሆነው ወጣት መሐሪ ነጋሽም በተመሳሳይ ቪዛ ቀመከልከላቸው ከፖላንድ የመቅረት ተመሳሳይ ዕጣ እንደገጠማቸው ታውቋል።
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ሶስት ጋዜጠኞችም ያገኙት ወርቃማ ዕድል ባክኖባቸዋል፤ፌዴሬሽኑ ጋዜጠኞቹን የዕድሉ ባለቤት መሆናቸውን በደብዳቤ ቢያሳውቃቸውም አክሰስ ኮዱን ቀድሞ ሊሠጣቸው ባለመቻሉ እንዲሁም ከአትሌቶችና አሠልጣኞች ጋር ቪዛ እንዲያገኙ በኤምባሲ ደረጃ ሊሞክርላቸው ባለመቻሉ የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8ቱ ጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሠ፣ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽኑ ጋዜጠኛ ወርቅነህ ጋሻውና የፕሬስ ድርጅቱ ጋዜጠኛ ቦጋለ ወርቃማው ዕድል አምልጧቸዋል።
እስከ አሁን ባገኘነው የተረጋገጠ መረጃ ቪዛ አግኝተው ወደ ፖላንድ የሚሄዱት ቀደም ሲል ቪዛ የነበራቸው አትሌት ብርቄ ኃዬሎም፣አትሌት ጌትነት ዋለ እና ንግስት ጌታቸው እንዲሁም ጀግናዋ አትሌት መሠረት ደፋር ዛሬ ባለቀ ሠዓት መስዋዕትነት ከፍላ ቪዛ ያስመታችላቸው አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ፣ አትሌት ባለሽኝ ባወቀ፣አትሌት አዲስ ይሁኔ ከውድድሩ ከመቅረት ተርፈው ዛሬ ምሽቱን ወደ ውድድሩ ስፍራ ይጓዛሉ።
ከሳምንታት በፊት ወላጅ እናትዋን በሞት የተነጠቀችው ጀግናዋ አትሌት መሠረት ደፋር ሐዘኗንና የግል ጉዳዮቿን ትታ በተከታታይ ቀናት ኤምባሲ በመመላለስ ዝናዋንና ታዋቂነቷን ተጠቅማ የአትሌቶቹ ህልም እንዳይጨልም ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች፤ከዚህ በፊትም በናንጂንግ ቻይና የአለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና አትሌቶች በተመሳሳይ በቪዛ ችግር ውስጥ በወደቁበት ሠዓት ፈጥና በመድረስ የታደገችው አትሌት መሠረት ደፋር እኔ ያሳለፍኩት ከባድ የአትሌቲክስ ፈተና በኔ ብቻ ይለፍ በማለት አሁንም አትሌቶቹን በመታደግ
ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ታሪክ የማይዘነጋው ታላቅ ታሪክ አፅፋለች።
ከአሜሪካ ኤምባሲ በገጠመው የቪዛ ችግር ያልተማረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚና ፅ/ቤት ከ45 ቀናት በፊት የአትሌቶችን ዝርዝር በሎንግ ሊስት አቅርበው ማመልከት ሲገባቸው ባለቀ ሠዓት መሯሯጣቸውና እስከዛሬ 11:00 ኤምባሲውን ሲማፀኑ መዋላቸው ብዙዎችን ያሳዘነ ሲሆን በውድድሩ ለሀገራቸው ታሪክ የመስራት ህልም የሠነቁትን አትሌቶችና አሠልጣኞችን ህልም ለሁለተኛ ጊዜ እንዲጨናገፍ ከማድረግ ባለፈ በፌዴሬሽኑ ታሪክም በጥቁር መዝገብ ተከትቦ የሚቀመጥ ታሪካዊ ስህተትም ሆኖ ተመዝግቧል።
በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ከአስር አትሌቶች 6 አትሌቶችን ብቻ 1 የቡድን መሪ(አቶ ቢኒያም ምሩፅን)፣1 አሠልጣኝ(አሠልጣኝ ቴውድሮስ ኃይሉን)፣1 የፅ/ቤት ኃላፊውን አመንሲሳ ከበደ(ዶ/ር) የቴክኒክ ቡድን መሪ አድርጎ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ህክምና ባለሙያ፣ያለ ማሳጂስትና ያለ ኮሚኒኬሽን ባለሙያ በፍራንክፈርት አድርገው ምሽት ላይ ወደ ፖላንድ ያመራሉ።
ከውድድሩ በፊትና በኃላ አትሌቶች ላይ የጉዳት ጥያቄ ቢነሳ ማን ክፍተቱን ይሞላል የሚለው እንዲሁም ከስፍራው ትኩስ መረጃዎችን ማን ይሠጣል?ለሚለው ጥያቄ ምላሹን ለፌዴሬሽኑ።
መልካም ውጤት ለአትሌቶቻችን ድል ለሀገራችን!!
