በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚ በግፍ የተጨፈጨፉ 6 ሚሊዮን አይሁዳውያን የሚታሰቡበት 81ኛው ዓመት የሆሎካስት መታሰቢያ ሥነ-ሥርዓት፣ ጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ በተከናወነው በዚህ መርሐ ግብር ላይ በእየሩሳሌም የሚገኘው የዓለም ሆሎኮስት መታሰቢያ ማዕከል ያዘጋጀው “Art in the Holocaust” የተሰኘ ልዩ ኤግዚቢሽን ለእንግዶች ክፍት ሆኗል።
መታሰቢያውን የእስራኤል ኤምባሲ፣ የጀርመን ኤምባሲ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጋራ በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን፣ የሰው ልጅ በማንነቱ ሊገደል እንደማይገባውና የጥላቻ ንግግር የሚያስከትለው አደጋ ለዓለም ትምህርት ሊሆን እንደሚገባ ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ዶክተር አቭራሃም ንጉሥ በእለቱ እንደገለጹት፣ አይሁዳውያን የተጨፈጨፉት በፈጸሙት ጥፋት ሳይሆን “በማንነታቸው” ብቻ ነው።
ለዚህ አሰቃቂ ድርጊት መሠረቱ የጥላቻ ንግግር መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደሩ፣ አሁን በጀርመንና በእስራኤል መካከል ያለው መልካም ግንኙነት በትብብርና በአስተሳሰብ ለውጥ ላይ የተገነባ መሆኑን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ወይዘሮ ብርጊት ቦሪን፣ እልቂቱን ማስታወስ ለጀርመናውያን ትልቅ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸው ጀርመን ለተፈጸመው ጥፋት ተጠያቂነቱን እንደምትቀበል አረጋግጠዋል።
አሁንም በዓለም ላይ የሚታየው ፀረ-ሴማዊ ጥላቻ ታሪክ ለዛሬ ትምህርት አለመሆኑን እንደሚያሳይ በመጥቀስ፣ ጀርመናውያን ፀረ-ሴማዊነትን ለመዋጋት ከአይሁዳውያን ጎን እንደሚቆሙ አስታውቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየዓመቱ ጃንዋሪ 27ን ዓለም አቀፍ የሆሎኮስት እልቂት መታሰቢያ ቀን ሲል ማወጁ ይታወሳል።
እለቱ በናዚ ግፍ የተገደሉትን አንድ ሦስተኛ የሚሆኑ የአይሁድ ሕዝቦች በማሰብ፣ ጭፍን ጥላቻና ዘረኝነት ስለሚያስከትለው አደጋ ለዓለም ሕዝብ የዘላለም ማስጠንቀቂያ ሆኖ እንዲያገለግል ታስቦ የሚከበር መሆኑን ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አብራርቷል።
