ያንዣበበው ሀገራዊ አደጋ በምን ይገታ ይኾን?

Date:

በአንድ ሀገር ላይ ረሀብ በሦስት ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል የዘርፉ ሰዎች ይጠቁማሉ፡፡ የመጀመሪያው የረሃብ ምንጭ የሰላም እጦት እንደኾነ ይታመናል፡፡ ዜጎች ተረጋግተው መኖር የማይችሉበት ሁኔታ ከተፈጠረና በሀገሪቱ ላይ እንደጦርነት ያሉ ሀገራዊ ቀውሶች ከተፈጠሩ ዜጎች ለከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስና ረሀብ መጋለጣቸው አይቀሬ ይኾናል፡፡ በታሪክም በርካታ ሀገራት ይህ ሁነት ያመጣባቸውን የረሀብ አለንጋ ተጋፍጠውት አልፈዋል፡፡ አሁን ላይም እንደየመን፣ ሶሪያና ሊቢያ ያሉት ሀገሮች የቀውሱ ተግባራዊ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የረሀብ ምንጭ ሊኾን የሚችለው ሀገሪቱ የምትከተለው ፖሊሲ ነው፡፡ አንድ ሀገር በግብርናው ዘርፍ ብቻ ሳይኾን በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ተቋማቶቿ ላይ የምትከተለው ፖሊሲ ለዚህ ችግር ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ በዚህ ዝንፈት ምክንያትም ነው በርካታ አፍሪካውያን በየዓመቱ የረሀብ አለንጋ ተገራፊ ኾነው የቀሩት፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የረሃብ ምንጭ ተደርጎ የሚነሳው የተፈጥሮ አደጋ ነው፡፡ የተፈጥሮ አደጋን በከፊልም ቢኾን ሀገራት በፖሊሲያቸው ሊጋፈጡት ቢሞክሩም ላላደጉ ሀገሮችና ለድንገተኛ ክስተት ግን ፖሊሲ ብቻውን ረሀብ ቀውሱ ልጓም ሊኾን አይችልም፡፡

የኾኖ ኾኖ አሁን ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ረሀብ ወደተሰኘው ሰቆቃ በመንደርደር ላይ የምትገኝ ይመስላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከፍ ሲል የተጠቀሱት ሰበበረሀቦች በተግባር የተፈጸሙ መኾናቸው ነው፡፡ እንደሚታወቀው አሁን ላይ በሀገራችን  ከፍ ያለ የሰላም እጦት አለ፡፡ በዚህ ሳቢያም መፈናቀል፣ ሞት፣ ስደትና ሁለገባዊ ማኅበራዊ ቀውስ ተፈጥሯል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሀገሪቱ የምትከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በራሱ የችግሩ ምንጭ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በትግራይና በአፋር ክልል ከፍተኛ የኾነ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ተከስቷል፡፡ ከዚህ አንጻር ሀገሪቱ አሁን ላይ ከፍ ወዳለ የረሃብ እንድርድሮሽ እየገባች መኾኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በትግራይ ክልል የተጋረጠው ረሀብ የክልሉ ፖለቲከኞች ሕዝቡን የሚፈልጉት ለፖለቲካ ግባቸው እንጂ ለሌላ እንዳልኾነ ያረጋገጠ ሁነት ነው፡፡ የትግራይ ፖለቲከኞች ሁልጊዜ ሕዛባችን እያሉ ቢያላዝኑም መሬት ያለው ሀቅ ግን ከዚያ የተለየ ነው፡፡ 27 ዓመታትን በትግራይ ሕዝብ ስም ምለው ተገዝተው ሀገር ዘርፈው ለትግራይ ሕዝብ ግን እነደጦስ ዶሮ የሚረግፍበትን የመከራ ዶፍ የዓለም ታላቁን ጦርነት አዋለዱለት፡፡ በምላሹም በብዙ ሺ የሚቆጠሩ እንቁ ልጆቹን በጥይት አረር አስጨፈጨፉት፤ በሺ የሚቆጠሩ ወገኖቹን ለዘላቂ አካል ጉዳተኝነት ዳረጉት፡፡ ያም ኾኖ ግን ዛሬም ሕዝባችን እያሉ ይለምኑበታል ግን አያበሉትም፡፡ ሕዝባችን እያሉ ለፖለቲካ ሥልጣን ይታገሉበታል ግን አይጠብቁትም፡፡ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ክልሎችም የዚሁ አምሳያ ናቸው፡፡

ከትግራይ ክልል አንጻር አሁን ባለው ሁኔታ ምንም እንኳን የክልሉ ሕዝብ በአስከፊ ቀውስ ውስጥ ቢገኝም ሊሂቁ ግን ለዳግም ጦርነት በቅስቀሳ ላይ ይገኛል፡፡ አሁንም ጥቂት የክልሉ ልሂቃኖች የእንግሊዝና የፈረንሳይን የጦርነት ታሪክ እንደሞዴል መቁጠር ጀምረዋል፡፡ በታሪክ እንደሚታወቀው እነዚህ ሁለት ሀገሮች በዓለም ላይ ረጅሙን ጦርነት ያካሄዱ ሀገሮች ናቸው፡፡ ከ1337 እስከ 1453 ዓ.ም ለ116 ዓመታት የዘለቀ የግዛት ይገባኛል ፍልሚያን አካሂደዋል፡፡ የግዛት ጥያቄ ያለባት ቦታ የፈረንሳይ ኖርማንዲ ግዛት ነች። ለብዙ ዓመታት እንግሊዞች ኖርማንዲን ጨምሮ ብዙ የፈረንሳይ ግዛቶችን ተቆጣጥረው ያስተዳድሩ ነበር። ፈረንሳይ ደግሞ አቅሟ እየጎለበተ ሲሄድ ቀደምት ግዛቶቿን መሰብሰብ ተያያዘች፡፡ በዚህ ሳቢያም በዚህች ግዛት ላይ ረጅም ዓመታትን የዘለቀ ውጊያ ልታካሂድ ቻለች፡፡ በመጨረሻም ፈረንሳይ ከሦስት ትውልድ የእንግሊዝ ወረራ በኋላ ግዛቷን መልሳ አገኘች። የትግራይ ፖለቲከኞችም ይህ ቅዠት በልባቸው አለ፡፡

እነዚህ ልሂቃን በዚህ ሂደት ውስጥ የዘነጉት ነገር ግን ፈረንሳይ “ኖርማንዲ” የተሰኘችው ግዛት ሀቃዊ ባለቤት መኾኗን ነው፡፡ አንድም ፈረንሳይና እንግሊዝ ጎረቤታሞች ሀገር እንጅ አዋሳኝ ክልልሎች አለመኾናቸውን ነው፡፡ የኛይቱ ትግራይና አማራ ጎረቤታም ክልል እንጅ አገሮች አይደሉም፡፡ የትግራይ ፖለቲከኞች ግን የፈረንሳይ የዓመታት የጦርነት ጉዞና ድል በቅናት በልቷቸው ዛሬም ስለሕዝባቸው ነባራዊ ሁኔታ ሳይኾን በጉልበት ወስደው በጉልበት ስለተቀሙት የወልቃይትና የራያ ግዛት መጠቅለል ያስባሉ፡፡ ለዚህ ግዛት ሲሉ የትግራይ ሕዝብ በሙሉ ቢከስም እንኳ ግድ የሚሰጣቸው አይመስልም፡፡ ለዚህ ማረጋገጫው ደግሞ ባለፈው ጦርነት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የትግራይን ሕዝብ አስበልተው ወደተሸነፉበት ጦርነት ድጋሜ የጦርነት ግስጋሴ መሥመር ሲዘረጉ መታየታቸው ነው፡፡ በተመሳሳይ በአማራና በሌሎች ክልሎች በኩልም የሚታየው አጠቃላይ ሁኔታና ጦረኝነት ረሀብን እያዋለደ ነው፡፡

በአጠቃላይ አሁን ላይ ሀገሪቱ እንደሀገር ከፍተኛ ቀውስ ላይ የምትገኝ ቢኾንም በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ግን እጅግ የሚያሳስብ መኾኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቂያ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ወደ25 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች እርዳታ ፈላጊዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ተረጂዎች መካከል ደግሞ የዕለት ደራሽ ምግብ እንኳን የሌላቸው አብዛኛውን ቁጥር የሚሸፍኑት ትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ናቸው፡፡ በመኾኑም ጉዳዩ የሚመለከተው ማንኛውም አካል ችግሩ ከዚህ በላይ ከመግፋቱ በፊት አስፈላጊውን ርብርብ ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ አደጋው ምንም እንኳ ሰሚ ያጣ ቢኾንም የክልሉ መንግሥትም ይሁን የፌደራል መንግሥት እየተባባሰ የመጣውን ረሀብ ለማስቆም ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በትግራይ ክልል ያለውን ሰብዓዊ ቀውስና የተጋረጠውን የረሀብ አደጋ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የሚመለከተው አካል በአስቸኳይ የእርዳታ እጆቹን ካልዘረጋ በቀጣይ ሊፈጠር የሚችለው ችግር እጅግ ከባድ ሊኾን እንደሚችል አሳስቧል፡፡

ጉባኤው በመግለጫው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UNOCHA) ሐምሌ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መረጃ መሠረት በእዚህ ግጭት ምክንያት በትግራይ ክልል ከአንድ ሚሊዮን (1,000,000) በላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቁሞ በተመሳሳይ የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ሐምሌ 14 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት መሠረት የትጥቅ ግጭቱ በክልሉ ያስከተለውን ቀውስ ተከትሎ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪ የምግብ እርዳታ ላይ የተደገፈ መኾኑን በመግለጽ በክልሉ ኮሌራና መሰል በሽታዎች መከሰታቸውን ገልጿል፡፡ በተመሳሳይ የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ይፋ እንዳደረገው ከአንድ ሺህ (1000) በላይ ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል፡፡ በተጨማሪ በቅርቡ የትግራይ አረጋውያን ማኅበር እንዳስታወቀው በትግራይ ክልል የጡረታ ደመወዝ ባለመከፈሉ እንዲሁም ባለው የምግብ እጦት በረሃብና በበሽታ ከ75 ሺሕ በላይ አረጋውያን የሞት አፋፍ ላይ ናቸው። በጥቅሉ ይህ ችግር በትግራይ ክልል ብቻ ተወስኖ የማይቆይ በመኾኑ ከወዲሁ አፋጣኝ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል፡፡ በተለይም አሁን ላይ እንደአጠቃላይ በሀገሪቱ ያለውን የማዳበሪያ እጥረት በአስቸኳይ በመቅረፍ ገበሬው ያመርት ዘንድ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ይህን ለማድረግ ደግሞ በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልል አካባቢ የሚደረገው ጦርነት መቆም ይኖርበታል፡፡ በዚህ ዙሪያ ደግሞ ከምንም በላይ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት በመኾኑ ዜጎችን ከረሀብ ለመታደግ አስፈላጊ የኾኑ ማኅበረሰቡ እረፍትና ሰላም የሚያገኝበትን እርምጃ ሁሉ ማከናውን ይጠበቅበታል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አርሰናል ከቦርንማውዝ በጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ

በ32ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ቀን...

በአሜሪካ እና ኢራን ድርድር ላይ የሚነሱ አራት ቁልፍ ጥያቄ

በፓኪስታን የሚደረገው የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር እየተጠበበፓኪስታን ነገር ግን...

መንገዳችን ረጅም፣ ጉዟችን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል...

የተመድ ዋና ጸሐፊ ኢራን እና አሜሪካ “በቅን ልቦና” ወደ ድርድሩ እንዲገቡ ጠየቁ

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሜሪካ እና ኢራን...