የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አርሶ አደሩን የፋይናንስ ተጠቃሚ ለማድረግ ዋነኛው ስትራቴጂካዊ መፍትሔ “ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ” መሆኑን አስታወቀ።
ባንኩ እስካሁን አርሶ አደሩን ከብድር ሥርዓቱ ውጭ አድርገው የቆዩትን የማንነት እና የብድር ታሪክ (Credit History) እጥረቶችን ለመቅረፍ ዲጂታል መሠረተ ልማቱ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጿል።
በብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ አካታችነት ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ፍቃዱ እንደገለጹት፤ ባንኮች ብድር ለመስጠት እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚጠይቁት የተበዳሪው ማንነት እና የቀድሞ የብድር አከፋፈል ታሪክ በአርሶ አደሩ ዘንድ አለመኖሩ ዘርፉን ለዓመታት ከፋይናንስ ድጋፍ ነጥሎት ቆይቷል።
አብዛኛው አርሶ አደር በባንኮች ዘንድ የሚታወቅ “ፕሮፋይል” የሌለው መሆኑ፣ የፋይናንስ ተቋማቱ አርሶ አደሩን እንደ ስጋት እንዲመለከቱት አድርጓቸዋል።
“የዲጂታል መታወቂያ መኖሩ አርሶ አደሩን በልዩ ሁኔታ ለይቶ ለማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ ተዓማኒነት ያለው የብድር ማጣቀሻ ሥርዓት (Credit Reference System) ለመገንባት መሠረት ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህም አርሶ አደሩ ያለፉትን የፋይናንስ ግብይቶች በማስረጃነት በመጠቀም ብድር እንዲያገኝ ያስችለዋል ብለዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም የዲጂታል መሠረተ ልማቱ መዘርጋት ባንኮች ለዘመናት ሲከተሉት የነበረውን “የቤትና የሕንፃ ዋስትና” ብቻ የመጠየቅ ግትር አሠራር የሚቀይር ነው።
የዲጂታል መታወቂያው አርሶ አደሩ ያለውን ተንቀሳቃሽ ሀብት እንደ ዋስትና በመጠቀም የብድር አገልግሎት እንዲያገኝ አዲስ የዕድል መስኮት ይከፍታል።
ይህ አሠራር ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ያወጣውንና ባንኮች ከሚሰጡት ጠቅላላ ብድር ውስጥ 5 በመቶውን ተንቀሳቃሽ ንብረትን እንደ ዋስትና በመያዝ ለግብርናው ዘርፍ እንዲያቀርቡ የሚያዝዘውን መመሪያ በተግባር ለመተርጎም ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ታምኖበታል።
የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቱ ከአርሶ አደሩ ማንነት ጋር መያያዙ፣ የምርት ገበያ ትስስርን ከማሳለጡም በላይ የገጠር ኢኮኖሚውን ወደ ዘመናዊ የገንዘብ ዝውውር በማምጣት የአገሪቱን የፋይናንስ አካታችነት ጉዞ እንደሚያፋጥነው ተመልክቷል።
