ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን የመኖሪያ ቤት እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል፡፡ መንግሥትም ይህን አንገብጋቢ ችግር ለመቅረፍ በየጊዜው ተለያዩ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ በዚህ ዙሪያ ካከናወናቸው ዋነኛ ተግባራት ውስጥ ግንባር ቀደሙና ተጠቃሹ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንደሚኒየም) መገንባትና በእጣ ለቤት ችግረኛው ማኅበረሰብ ማከፋፈል ነው፡፡ ሌላው መንግሥት የቤት እጥረት ችግርን ለመቅረፍ ከሄደባቸው ርቀቶች ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጠው ደግሞ ቤት መሥሪያ ቦታዎችን ለባለሐብት በመሥጠት ሪል ስቴቶችና መሰል አፓርታማዎች እንዲገነቡ ማድረግ ነው፡፡
መንግሥትን ይህን መሰል እቅድ በመከተል በርካታ ባለሀብቶች በዘርፉ ላይ ተሠማርተው እንዲሠሩ አድርጓል፡፡ በዚህ ዙሪያ ተሠማርተው ከሚገኙ ተቋማት ውስጥ ደግሞ አንዱ “ፍሊንትስቶን ሆምስ” የተሰኘውና ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በተለያዩ የኮንስትራክሽን ሥራዎች የሚታወቀው ተቋም ነው፡፡ ፍሊንትስቶን ሆምስ የዘርፉን ችግር ለማቃለል ያለፉትን ዓመታት በዘርፉ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ከመጪው ሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮም የአክሲዮን ሽያጭ ሊያካሂድ መኾኑን ሰሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡ የተቋሙ መሥራችና ባለቤት የኾኑት ኢንጅነር ፀደቀ ይሁኔ በጋዜጣዊ መግለጫው እንዳስታወቁት ፍሊንትስቶን ሆምስ ያለፉትን ረጅም ዓመታት የተለያዩ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሥራዎችን ሲያከናውን ቢቆይም በተለይም ያለፉትን ዐሥራ አምስት ዓመታት በሪልስቴት ግንባታው ላይ ተሰማርቶ አመርቂ ተግባራት ማከናወኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ድርጅቱ አሁን ላይ የአክሲዮን ሽያጭ ለመጀመር እየተንደረደረ እንደኾነ አመላክተውም የአክሲዮን ባለቤትነቱ ከብር ሃያ ሺህ የማያንስና ከብር ሁለት ሚሊዮን የማይበልጥ ይኾናል ብለዋል። ድርጅታቸው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 10 ሺህ ቤቶችን ለደንበኞች የማቅረብ እቅድ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ የአክሲዮን ሽያጩ ድርጅቱ የሚያቀርባቸውን ቤቶች በተመጣጣኝ እና በአስተማማኝ መንገድ ለደንበኞች ማቅረብ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ድርጅቱ ከተቋቋመበት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ በልዩ ልዩ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራ ተቋራጭነት ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ከዐሥራ አምስት ዓመታት በፊት በተጨማሪ ወደ ቤቶች ልማት ገበያ የተቀላቀለው ፍሊንትስቶን በትምህርት፣ በውሃ፣ በመብራት ኃይል፣ በመንገድ እና በመንግሥት የቁጠባ ቤቶች ፕሮጀክቶች ላይ ግዙፍ አሻራዎችን እያኖረ የመጣ መኾኑም በጋዜጣዊ መግለጫው ተመላክቷል። ወደ ሪልስቴት ከተቀላቀለ በኋላም ያለፉትን ዐሥራ አምስት ዓመታት በሺህ የሚቆጠሩ ደንበኞችን የቤት ባለቤቶች እንዳደረገም ተጠቁሟል።
የድርጅቱ አጀማመርን በተመለከተ መሥራችና ባለቤት የኾኑት ኢንጂነር ፀደቀ እንደተናገሩት “ድርጅቱ ሲመሠረት 1983 ዓ.ም እና 1984 ዓ.ም ከፍተኛ ብሔርተኛነት የነበረበት ዘመን ነበር፡፡ ስለዚህ በወቅቱ የድርጅቴን ስም ለማውጣት ተቸግሬ ነበር፡፡ በወቅቱ ፍሊንትስቶን ሆምስ የሚለውን ሥም ለመጠሪያነት ስመርጠው የሁሉም ኢትዮጵያውያን እንዲኾን በማለም ነበር፡፡ እንዳልኩትም ተሳክቶልኝ ድርጅቱ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የእኔ ብቻ ሳይኾን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊኾን ችሏል፡፡ ፍሊንት ስቶን ማለት የእሳት ማውጫ ባልጩት ድንጋይ ማለት ነው” ሲሉ አብራርተዋል፡፡ አክለውም “ድርጅቱ የተመሠረተው ከእናቴ በተበደርኩት 6ሺህ ብር ነው” ብለዋል፡፡ ኢንጂነር ፀደቀ ድርጅቱ አሁን ላይ በ11 ክልሎች እየተንቀሳቀሰና አሻራውን እያስቀመጠ እንደሚገኝ ጠቅሰው በቅርቡ በርካታ ባለአክሲዮኖችን አሳትፎ የላቀ ሥራ እንደሚያከናውን አውስተዋል፡፡ በተጨማሪም “ፍሊንትስቶን ዛሬ ላይ ደግሞ፤ ከሃገሪቱ ተስፋ የመነጨውን የድርጅቱን ራዕይ ዕውን ለማድረግ ፍሊንትስቶን ከእስካሁኑም እጅግ የላቀ ተልዕኮ ሊፈጽም ይገባዋል፡፡ በጥቂት ባለሃብቶች የሺዎችን ቤት ማቅረብ ከተቻለ ፤ ሺህ ኾኖ ደግሞ ለሚሊዮኖች እንኳን ቢከብድ ለመቶ ሺህዎች የመኖሪያ እና መነገጃ ሥፍራ ማዘጋጀት እንደሚቻል አያጠራጥርም፡፡” ሲሉ አክለዋል፡፡
ከባለ አክሲዮኖች 10 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እንደታቀደ የተገለጸ ሲኾን ለሽያጭ የቀረበው አነስተኛ የአክሲዮን መጠን ብር 20ሺህ ከፍተኛው ደግሞ 2 ሚሊዮን የተደረገበትም አንዱ ምክንያት እነዚህ ሁለት ጣምራ ዓላማዎች ሊሳኩ የሚችሉት ብዙኃኑን ማሳመን እና ማርካት የሚችል ኩባንያ ከኾነ ብቻ እንዲኾን ለማድረግ ታቅዶ ነውም ተብሏል። በርግጥ “ድርጅቱን እዚህ ደረጃ ያደረሱትን አሠራር ቦታ የሚያሳጣ የአክሲዮን ግብይት መልሶ ድርጅቱን ለአደጋ አያጋልጠውም ወይ?” የሚል ሃሳብ ሊያስነሳ ይችላል፤ ይህ ስጋት ተገቢ ቢኾንም በአመራሩ ብርታት በመተማመን በቅድምያ አከሲዮን የሚገዙት ብዙኃን በነባሩ ስንፍናም ኾነ በተተኪው አመራር አዲስ ሃሳብ ወይም ጉብዝና፣ በሂደት ብዙኃኑን የሚወከል አዲስ አመራር እያበጁለት እንደሚሄዱ ተመላክቷል። ተቋሙን ለአክሲዮን ሽያጭ ማቅረብ ያስፈለገውም የአክሲዮን ገበያ፣ ትውልድ የሚሻገር ኩባንያ ጠንካራ መሠረት ይኾናል ተብሎ እንደሚታሰብም ተጠቁሟል። ድርጅቱ ለአክሲዮን ሽያች መቅረቡ በግለሰቦች ትከሻ ላይ ከሚንጠለጠል የማኅበረሰብ ቢኾን የተሻለ አፈጻጸም ኖሮት ይበልጥ ትርፋማ ሊኾን ይችላልም ተብሏል፡፡
“ሁሌም በለውጥ ሰዓት ለባለሃብቶች ሦስት ነገሮች የመኾን ዕድል ያጋጥማል፣ ቆዛሚም፣ አዝጋሚም ተምዝገዛም መኾን ይቻላል፡፡ ተምዘግዛጊ መኾኑ ግን እጅጉን ያዋጣል፣ እንደ ንግድ ድርጅት፡፡ ሀገራችንን በጋራ፣ ሀብታችን በአክስዮን እንገንባ” ሲሉም የተቋሙ ባለቤቶች ጥሪቸውን አስተላልፈዋል፡፡ አሁን ላይ ፍሊንትስቶን ሦስት ነገሮች ላይ አተኩሮ እንደሚሠራ የተጠቆመ ሲኾን የመጀመሪያው አክሲዮን መሸጥና ባለአክሲዮኖችን ወደ ደንበኞችም መቀየር ነው ተብሏል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በአክሲዮን የተሰበሰበውን ገንዘብ ማሳወቅና እንዲሁም በሦስተኛ ደረጃ አነስተኛ ባለአክሲዮኖች በባለብዙኃኑ ባለአክሲዮን እንዳይሸፈኑ የዲጂታል መተግበሪያ መዘጋጀቱንና መተግበሪያው ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ሥራ ላይ እንደሚውል ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም ፍሊንትስቶን እራሱን እንደንግድ ተቋም የሚያይ ሳይኾን የደንበኞችንና የሀገርን አደራ ኃላፊነት በመውሰድ ለመሥራት የሚሞክር ተቋም እንደኾነ የተመላከተ ሲኾን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከ10 ቤቶች በላይ ተገንብተው ለደንበኛው እንደሚቀርቡና ይህን ሥራ ውጤታማ ለማድረግም የባለ አክሲዮኖችን ብዛት ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
