ጂቡቲ ‹‹ኢትዮጵያ የጦር ሰፈር እንድትገነባ አልፈቅድም›› አለች

Date:

ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን በቀጥታ እንድታስተዳድር አማራጭ ሃሳብ ማቅረቧን ያስታወቁት የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ኢትዮጵያ የባህር ሀይል ጦር ሰፈር መገንባት እንደማትችል አስታወቁ። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ድንበር በ100 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ታጁራ ወደብ እንድትጠቀምበት ሃሳብ ማቅረቧን አስታውቀው “ሆኖም ይህ አማራጭ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ለመገንባት ያላትን ፍላጎት እንደማያካትት” አመልክተዋል። ኢትዮጵያ ፍላጎቷን ለማሟላት ቢያንስ አስር ወደቦች ያስፈልጋታል ሲሉ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

“ከ100 ሚሊየን በላይ ሸማቾች ያላት ትልቅ ሀገር እንደመሆኗ ኢትዮጵያ ከሶስት እና አራት በላይ ወደቦች ያስፈልጓታል” ሲሉ የተደመጡት አሊ ዩሱፍ “ኢትዮጵያ አሁን ያላትን የገበያ ፍላጎት ለማሟላት አስር ወደቦች ያስፈልጓታል፣ ስለዚህ እነዚህን ፍላጎቶች እንረዳለን፣ የሚጠበቀውን ለማድረግም እንሞክራለን” ብለዋል። ዩሱፍ አክለው ጂቡቲ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የነበረው መልካም ግንኙነት ወደ ነበረበት እንዲመለስ እንደምትፈልግም አመልክተዋል።

“ኢትዮጵያ ከአንድ በላይ መተላለፊያ እንዲኖራት በማገዝ የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ እና ሁሉም እንዲረጋጋ በማድረግ በዋናው ቁምነገር ላይ ማተኮር ያለብን ይመስለኛል” ሲሉ የተደመጡት ሚኒስትሩ “እንደ ጂቡቲ የሚኖረን ሚና ያ ነው፤ ላለፉት አመታት ስናደርግ የነበረውም ይህንን ነው፤ አሁንም በእነዚህ መርሆች ላይ መስራታችንን እነቀጥላለን” ሲሉ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ፣ የጂቡቲን ጥያቄ ትቀበል ወይንም አትቀበል ግልጽ ባይሆንም የስምምነት አማራጩን ይፋ ያደረጉት የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ የሱፍ ከኢትዮጵያ መሪዎች ያገኙት ምላሽ አወንታዊ ነው ማለታቸውን የቪኦኤ ዘገባ ያሳያል።

በአፍሪካ ቀንድ የተነሳውን ውጥረት ለማርገብ ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን በቀጥታ እንድታስተዳድር አማራጭ ሃሳብ ማቅረቧን ጅቡቲ ማስታወቋ ይታወሳል። ኢትዮጵያ የባህር መዳረሻ እንድታገኝ አንደኛውን የጂቡቲ ወደብ “ሙሉ በሙሉ እንድታስዳድር” አገራቸው አማራጭ ሃሳብ ማቅረቧን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ መናገራቸውን ዘገባው አካቷል። አማራጭ ሃሳቡን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኦማር ጊሌህ ለኢትዮጵያ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መግለጻቸውን እና በተፈፃሚነቱ ዙርያ ዝርዝር አስተያየት ከመስጠት መቆጠባቸውም ተካቷል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ በቀረበላት ሃሳብ እስከአሁን ያለችው ነገር የለም ያለው ዘገባው ይሁን እንጂ ሚኒስትሩ በአማራጭ ሃሳቡ ዙሪያ በያዝነው ሳምንት በሚካሄደው የቻይና አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ከሁለቱ መሪዎች ጋር ለመወያየት ዕድል ሊኖር ይችላል ሲሉ መናገራቸውም ተመላክቷል።

ማይክ ሀማር ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው

የአሜሪካ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ማይክ ሀማር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ በድህረ ገጹ ባወጣው መግለጫ ማይክ ሀማር ከፈረንጆቹ መስከረም 3-13 ባለው ጊዜ ውስጥ ቤልጄየምን፣ ኬንያን እና ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ ብሏል። ነገርግን መግለጫው ማይክ ሀማር ሶስቱን ሀገራት እንደሚጎበኙ ከመግለጽ ወጭ የትኛውን ሀገር መቼ እንደሚጎበኙ ወይም ጉብኝታቸው ከየት እንደሚጀምር ግልጽ አላደረገም። ማይክ ሀመር በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የተፈረመው የፕሪቶሪያ የዘላቂ ስምምነት አፈጻጸም እንደሚገመግሙ መግለጫው ጠቅሷል። ማይክ ሀመር ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በሱዳን ጉዳይ ከኢጋድ እና ከአፍሪካ ህበረት ጋር ይመክራሉ ብሏል መግለጫው። አሜሪካ የቀድሞ ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ፣ እንዲበተኑ እና ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ በማድረግ፣ ተፈናቃዮች በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ በማድረግ፣ የሽግግር ፍትህን እና ተጠያቂነትን በማጠናከር እና በሌሎች መንገዶች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የፌደራል መንግስቱን እና ህወሓትን ለመርዳት ቁርጠኛ መሆኗን ገልጻለች።

መግለጫው ከፕሪቶሪያው ስምምነት በተጨማሪ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭትም በሰላም በሚቋጭበት ሁኔታ ከባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ ብሏል። አሜሪካ በሁለቱ ክልሎች ያሉ ግጭቶች በውይይት ብቻ እንዲፈቱ አዲስ አበባ ባለው ኢምባሲዋ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል በተደጋጋሚ መግለጫ አውጥታለች። የኢትዮጵያ መንግስት ኃይሎች፣ በኦሮሚያ ክልል “ሸኔ” ተብሎ በሽብር ከተፈረጀው ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር ለአመታት፣ በአማራ ክልል ደግሞ ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ከባለፈው አመት ሚያዝያ ጀምሮ የትጥቅ ግጭት ውስጥ ገብተዋል። በአማራ ክልል ያለውን ግጭት ለማስቆም መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ የጸጥታ ኃይል ያሰማራ ቢሆንም ግጭቱ አልቆመም። በክልሉ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ እና ከግጭቱ አውድ ውጭ በርካታ ንጹሃን በዋናነት በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እየተገደሉ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን (ኢሰመኮ) ጨምሮ በርካታ አለምአቀፍ የመብት ተቆርቋሪ ተቋማት ሪፖርት ማውጣታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አሥመራ የሚያደርገው በረራ ተቋረጠ

አየር መንገዱ ከሰሞኑን በሰጠው መግለጫ አዲስ አበባ አስመራና ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ ሲያደርግ የነበረውን በረራ “አቋርጫለሁ” ሲል አስታቋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱ ወደ ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ማቋረጡን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል። ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ አየር መንገዱ በረራውን ከነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ማቋረጡን ገልፀዋል። አየር መንገዱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በኤርትራ ውስጥ አገልግሎቱን ለመስጠት ባጋጠመው ከአቅም በላይ በሆነ የአሰራር ችግር ምክንያት እንደሆነም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የገለጹት። ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው አክለውም፤ ምክንያቱን ባላወቅነው መንገድ አስመራ ውስጥ ያለንን የዶላር ገንዘብ እንዳናወጣ ተከልክለናል ብለዋል።

“በአስመራ የሚገኘው ተወካያቸው ከሽያጭ የተሰበሰበ ገንዘብ ለማስገባት ሲል ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ መላክ እንደማይቻል ተነግሮታል፤ ይህ የሆነው ሐምሌ 20 በተጻፈ ደብዳቤ አማካኝነት ነው፡፡ ከነሃሴ 25 በኋላ ሂሳባችሁ ታግዷል ለሀገር ውስጥ ወጪም መጠቀም አትችሉም መባሉን ተከትሎ ከዛሬ ጀምሮ በረራውን ለማቋረጥ ተገደናል። የበረራ ወጪያችንን መሸፈን ባለመቻላችን ተገደን ወጥተናል” ብለዋል ዋን ስራ አስፈጻሚው በመግለጫቸው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤርትራ ውስጥ የናቅፋ እና የሀርድ ከረንሲ (ዶላር) የሂሳብ ደብተር ያሉት ሲሆን፤ የናቅፋ አካውንት የቆየ እና የማይንቀሳቀስ የሂሳብ አካውንት መሆኑን ገልጸዋል። የዶላር አካውንሩ ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትኬት ሲሸጥ የነበረው በውጭ ምንዛሬ መሆኑን ገልጸው ይህንን ገንዘብም እገዳው እስከተላለፈበት ቀን ድረስ በተለያዩ ጊዜዎች ገንዘቡን ሲያንቀሳቅስ እንደነበረ ገልጸዋል። በኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ያወጣውን የጉዞ ክለከላ ተከትሎ የዶላር አካውን እንዳያንቀሳቅስ መከልከሉ በመግለጫቸው ተጠቁሟል። አክለውም አየር መንገዱ ገንዘብ ካላገኘ እና እዛ ለሚያስፈልጉ ወጪዎች መጠቀም ካልቻለ በረራ ማቆም ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ተናግረዋል። “አየር መንገዱ ከኤርትራ የወጣው ተገዶ ነው” ያሉት አቶ መስፍን ዋናው ችግሩ ለምን እንደታገድን አለማወቃችን ነው፤ በተጻፈው ደብዳቤም ላይ ምንም የተገለጸ ነገር የለም ብለዋል። የኤርትራ ሲቪል አቬሽን ከአንድ ወር በፊት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ በሚጓዙ ተጋዦች ላይ “የተደራጀ እና ስልታዊ የሻንጣ ስርቆት፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ፣ ማንገላታት እንዲሁም ካሳ አለመክፈል የሚሉ ምክንያቶችን አስቀምጦ ነበር።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...