ግብፅ እና ሱዳን በዓባይ ውኃ እና በሱዳን ቀውስ ዙሪያ ተወያዩ

Date:

የግብፁ ፕሬዝደንት ዐብደል ፋታህ ኤል-ሲሲ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሌተናል ጄኔራል ዐብደል ፋታህ አል-ቡርሃንን ጥቅምት 5 ቀን 2018 ዓ.ም. በካይሮ በሚገኘው አል-ኢቲሃዲያ ቤተ መንግሥት ተቀብለው ውይይት ማድረጋቸው ተዘገበ።

በውይይቱ ወቅት በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በዓባይ ወንዝ የውኃ ጉዳይ እንዲሁም በሱዳን ባለው ግጭት ዙሪያ በዝርዝር ተነጋግረዋል።

የግብፅ ፕሬዝደንታዊ ቃል አቀባይ አምባሳደር ሞሃመድ ኤል-ሸንናዊ እንዳሉት፣ ፕሬዝደንት ኤል-ሲሲ የሌ/ጄኔራል አል-ቡርሃንን ጉብኝት በደስታ በመቀበል፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል ያለውን “ሥር የሰደደ የወንድማማችነት ግንኙነት” እና በተለያዩ የትብብር መስኮች የታየውን እድገት አድንቀዋል።

ከፕሬዝደንቱ ጽህፈት ቤት በወጣው መግለጫ መሠረት፣ ሁለቱ መሪዎች የዓባይ ወንዝ የውኃ ጉዳይን በተመለከተ በቅርቡ የተፈጠሩ ለውጦችን ተወያይተዋል። የዓባይ ወንዝ ላይ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረር “ማንኛውንም የተናጠል እርምጃ” በጽኑ እንደሚቃወሙ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

ሌ/ጄኔራል አል-ቡርሃን ግብፅን እና ሱዳንን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላቸውን የተቀናጀ አቋም አጽንኦት ሰጥተው በመግለጽ፣ የጋራ የውኃ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ የውይይትና የማስተባበር ስልቶችን ከፕሬዝደንት ኤል-ሲሲ ጋር ሆነው ለማጠናከር ተስማምተዋል።

በተጨማሪም፣ በስብሰባው ላይ በሱዳን ያለውን የአሁኑን ሁኔታ እና ግጭቱ አብቅቶ መረጋጋትን ለመመለስ እየተደረጉ ያሉትን ጥረቶች ተመልክተዋል።

ፕሬዝደንት ኤል-ሲሲ የሱዳንን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፉ አረጋግጠው፣ የሀገሪቱን ብሔራዊ ትስስር ሊያናጉ የሚችሉ ወይም ትይዩ (ተመሳሳይ) አስተዳዳሪ አካላትን የሚፈጥሩ ማናቸውንም ሙከራዎች እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል።

ሌ/ጄኔራል አል-ቡርሃን በበኩላቸው፣ የግብፅን ቀጣይ ድጋፍና የፕሬዝደንት ኤል-ሲሲን ጥረቶች አመስግነዋል። ይህ ድጋፍ “በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ጥልቅ ትስስር” የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፣ ሱዳን አሁን የገጠማትን ቀውስ እንድትቋቋም አስተዋፅኦ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በስብሰባው ላይ ከግብፅ በኩል የውጭ ጉዳይ፣ የስደትና የግብፅ የውጭ አገር ዜጎች ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር በድር ዐብደል-አቲ እና የጠቅላላ መረጃ ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ሀሰን ረሻድ ተገኝተዋል።

በሱዳን በኩል ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሂ አል-ዲን ሳለም፣ የጠቅላላ መረጃ ዳይሬክተር ሌ/ጄኔራል አህመድ ኢብራሂም ሙፈዳል፣ በካይሮ የሱዳን አምባሳደር ሌ/ጄኔራል ኢንጅነር ኢማድ አል-ዲን ሙስጠፋ አዳዊ እና የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝደንት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ዓደል ኢስማኢል አቡበክርን ያካተተ ልዑካን ቡድን ተካፍሏል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ካናዳ ምዝገባም ሆነ ስምሪት አልተጀመረም

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መቀመጫውን ካናዳ ካደረገው "ፊውቸር ፊት ኢንተርናሽናል"...

የክቡር ዶክተር ጋሽ መሐሙድ አዲስ አልበም ለአድማጮች ሊደርስ ነዉ

ታዋቂው ድምፃዊ ክቡር ዶክተር አርቲስት መሐሙድ አሕመድ «ለታሪክ» የተሰኘውንና...

ሜታ ‘ፌስቡክ እና ኢንስታግራም በቀረበባቸው ክስ 18 ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ

ግዙፉ የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያ ሜታ በፌስቡክ እና በኢንስታግራም ምክንያት...