ግዮን ኹለት መቶኛ ዕትም ሞላት!

Date:

የኢትዮጵያ የሕትመት ሚዲያው ዘርፍ፣ ይልቁንም ነጻ ፕሬስ የሞት አፋፍ ላይ ቆሟል፡፡ ይኽ ጆሮን ጭው ሊያደርግ የሚገባ መርዶ ነው፡፡ በትውልድ የንባብ እና የሥነ ጽሑፍ ተስፋ ላይ እንደ ድማሚት የፈነዳ መርዶ! የሐሳብ፣ የፍልስፍና እና የሥርዓታዊ ጽሕፈት ዕድገትና ጉልምስና በሚገድደው ማንኛውም ዜጋ አእምሮ ላይ የተወነጨፈ መርዶ! ‹‹ንባብ ለሕይወት›› ላሉ አሰላሳዮች ነጠላን አስዘቅስቆ ለቅሶ የሚያስቀምጥ ክፉ መርዶ!

እንዲህ ያለው ዜና ምን ያህል ሀገርን እና ትውልድን የመስበር አቅም እንዳለው መረዳት የቻለ መንግሥት እንዳለ ግን አጠያያቂ ነው፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ በጥቂት የጨውና የበርበሬ ነጋዴዎች ሞኖፖሊ የተያዘው የወረቀት ንግድ አብዮት የማይመልሰው ውድቀት እያዋለደ እንደሚገኝ አብዛኛው የሀገር እና የትውልድ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚለው ወገን የገባው አይመስልም፡፡ ሁሉም በምንግዴነት ነገሩን ችላ ብሎታል፡፡

መጽሔታችን ግዮን እንዲህ ባለው እጅግ ከባድ እና ፈታኝ ኹኔታ ውስጥ አልፋ ነው ኹለት መቶኛ ዕትሟን ወደ እናንተ ክቡራን አንባቢዎቿ ይዛ የመጣችው፡፡ እንደሚታወቀው እና በተደጋጋሚም እንደገለጽነው መጽሔታችን ግዮን በነጻው ፕሬስ ውስጥ ረጅም እና ሰፊ ልምድ ባላቸው ጋዜጠኞች የምትሰናዳ መጽሔት ናት፡፡ ባለፉት ከሩብ ክፍለ ዘመን ለሚልቁ ዓመታትም ዕንቁ፣ ሐምራዊ፣ ሐበሻ ሪቪው፣… በሚሉ መጽሔቶችና ጋዜጦች በኩል ከሞያሌ እስከ መቀሌ ጫፍ ያለውን ሰፊ አንባቢ የሕብረተሰብ ክፍል በመረጃ እና በዕውቀት ተደራሽ ለመኾን ዋጋ ስትከፍል ኖራለች፡፡ ከየካቲት 2010 ዓ.ም ወዲህ አንስቶ ደግሞ “ግዮን” መጽሔትን እና “ኢትዮ ሐበሻ” ጋዜጣን ወደ ገበያው በማምጣት ነባሩን የነጻ ፕሬስ ኃላፊነት ለመወጣት ስትታትር ቆይታለች፡፡

ኾኖም ድኅረ 2010 ያሉት ዓመታት በብዙ መልኩ ሀገራችን ፈተና ውስጥ ገብታ የቆየችበት ቢኾንም፣ በሕትመት ሚዲያው ዘርፍ ላሉ ሚዲያዎች ደግሞ በተለየ መልኩ ዐዳዲስ የሚባሉ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ የተገደዱበትም ነው፡፡ ፈተናውን የፕሬሱ ውጤቶች ያለ ምንም መንግሥታዊ ፖሊሲ እና የሕግ ከለላ ብቻቸውን እንዲጋፈጡ የተፈረደባቸው መኾኑ ደግሞ አቅማቸው በእጅጉ እንዲዝል ምክንያት ኾኗል፡፡ የቱንም ያህል ሥርዓታዊ እና መዋቅራዊ ለውጦች ዛሬም ለሀገራችን እንደ ሰማይ የራቁ ጉዳዮች መኾናቸው ግልጽ ቢኾንም፣ ቢያንስ የብዙኃን መገናኛ ሕጉ፣ የኤሌክትሮኒክስ እና የሕትመት ሚዲያው ከመንግሥታዊ ተቋማት ፍትሓዊ የኾነ ማስታወቂያ እንዲያገኝ አሰራሩን በማሳለጥ ረገድ ተጥሎበት የነበረው ተስፋ በዚህ ልክ አልቦ ይኾናል ብሎ የጠበቀ የለም፡፡

በዛ ላይ የመንግሥት መዋቅሩ ዛሬም ነጻ የሕትመት ውጤቶች ማበብ በሚያቃዣቸው እና በሚያባንናቸው ግለሰቦች የተጠለፈ መኾኑ፣ እንኳንስ ለጉዳዩ ዋጋ ሊሰጡ እንዲያውም ስልታዊ በኾነ መንገድ ለማጥፋት ተባባሪ እንዲኾኑ የተመቻቸው ይመስላል፡፡ ዳሩ ግን ሃይ ባይ እና ተቆጣጣሪ የሌለው የበይነ መረብ የሚዲያ ማዕበል በተጥለቀለቀበት በዚህ ዘመን የሚዲያን የሥነ ምግባር መርኆ ጠብቆ እና ሥርዓት ባለው የኤዲቶሪያል ፖሊሲ የሚመራን የሕትመት ብዙኃን መገናኛ ዘርፍ ከገበያ ማስወጣት ምን የተለየ ትርፍ እንደሚያስገኝ የሚያውቁት እነኚህ ወገኖች ብቻ ናቸው፡፡

ግዮንም ኾነች ሌሎች አሁን ላይ ከሕትመት ሚዲያው ዘርፍ የወጡ እና የመውጣት ፈተና በተጋረጠባቸው መጽሔት እና ጋዜጦች ፈጣን የኾነ የአሠራር ሥርዓት ካልተዘረጋላቸው ዘርፉ ወደታሪክነት ላለመቀየር አንዳችም ዋስትና የላቸውም፡፡ መጽሔታችን እንዲህ ባሉ የወረቀት እና የማተሚያ ግብዓቶች ከሦስት ዕጥፍ በላይ መወደድ እና ሌሎችም ጫናዎችን ተቋቁማ የኹለት መቶኛ ዕትሟን ወደ እናንተ አንባቢያን ስታደርስ፣ በዘርፉ የነበራትን ወርቃማ እና የማይረሳ ተሳትፎ አጠናክራ እንድትቀጥል እና በሌሎችም ዘመኑ በወለዳቸው የሚዲያ አማራጮች ራሷን ለመከሰት ትችል ዘንድ ተገቢውን ድጋፍ እንድታደርጉላት በመተማመን ጭምር ነው፡፡ እንኾ ግዮን ኹለት መቶኛ ዕትም ሞላት!                   

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...