ግጥም እንደ ታቦት ፤ እሷም እንደ መቅደስ

Date:

ጌራወርቅ ጥላዬ

ያንድ ነገር ንፉግነት ሲገለጽ ‹‹ወርቅ ቢሰጡት፣ ጠጠር ይመልሳል›› ይባላል። የጎጃም መሬት ለጋስነት ግን ጠጠር ቢዘሩበት ወርቅ ያበቅላል የሚያስብል ነው። (ይህን ስል ደሞ ጠጠር ዘርተህ የወርቅ ማሳ ጠብቅ አሉህ) አነጋገሬን (አጻጻፌን) ለተረዳ ግን ‹‹እውነት ነው የበላሁት ጤፍ ምሥክር ነው›› ይላል። ዛዲያ ጎጃም ከጤፍ ያላነሰ የባለቅኔ ማሳ፤ የቅኔ አዝመራም ነው። (‹‹ነበር›› ለሚልም ነበር…)

ጎጃም ሲነሳ በላተኛው ማኛ ጤፍ፣ ጠቢቡ ቅኔ ይታወሰዋል። ርግጥ ነፍስና ሥጋ ከያዘ ሰው ሁለቱም የሚጠበቅ ነው። እኔም ሥጋኛዊ ሳልሆን እንደ ሰው ሥጋኛ ስለሆንኩ ጤፍን ባልረሳም፤ ይህንን ጽሑፍ እንደሚጽፍ፥ እንደቅኔ ወዳጅ ሰው፣ እንደ ‹ባለቃል› ደሞ አደላለሁ ለቅኔው።. . .

መሬቱ አላምጠው ቢተፉበት የሚያበቅለውን ያህል ጎጃም ልክ እንደእህል ሰው አብቅሏል። ሰው ሲባል ሁሉን ሆኖ ባፉ እህል የሚያስገባን ሳይሆን በአፉ ቅኔ የሚያወጣን ባለቅኔን ሰው ማለቴ እንጂ።

ቅኔ እንደጤፍ ጎጃም እንደሚያበራይ፣ እንደሚያመርት፤ ለመንገር እንዲያው ዋሸራን፣ ዲማን፣ ጎንጅን፣ ጽላሎን. . .፣ መጥቀስ ይጠበቅብኝ ይሆን? ርግጥ ለማያውቅ ማሳወቁ ያስተዋውቃል። ቅኔ እንዳፈቀረ፣ ግጥም እንደወደደ፣ ‹ባለቃል› እንደሆነ ሰው እኔም እንዲህ ብያለሁ፤ እንደሚከተለው. . .፦

 ቀለም ደረቀ እንጂ ጣፊ በመንጠፉ

  ከዋሸራ! ነበር፣

  ከዲማ! ነበረ፣

  ከጎንጂ! ነበረ፣

  ከጽላሎ! ነበር፤ የቅኔ ቃል አፉ።

ጎጃም የቅኔ አድባር። ይህን ስል እውነት አልዋጥለት ላለ አንባቢ ግን ጎጃም የጸሃፊ አድባር መሆኑን ለመንገርና ለመናገር ጉምቱውን ተዋነይን እጠቅሳለሁ፤ ሞትን ሰባት ዓመት እንደጅብራ ገትሮና ቀስቶ አፍንጫህን ላስ፣ ‹ፈስህን ጠጣ› ማለቱን ከራሱ ከተዋነይ ጋር አፈ ታሪክ ለሆነበት ትውልድ ደግሞ የቅኔዋን እመቤት እማሆይ ገላነሽ አዲስን ‹‹የቅኔ እምዬ›› ስል ጊዜና፣ ‹‹ማን ትሆን?›› ላለ ሰው፣ ከመታገስ ጋር ተሥፋ ባለመቁረጥ ትዝ ለማስባል የማይረሳውን መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬን አስታውሳለሁ። ከመጽሐፈ ቅኔ ጋርም አድማሱ ጀምበሬን ለረሳ ልበ ልልና ልበ ውልቅ ግን ሌላ ብለው ሌላውን አያውቅምና ከወደ ጎጃም በመጣችው በመቅደስ ጀምበሩ ማስታወሱን እደመድማለሁ። ከዚህ ውጭ ግን በጎጃሜኛ ‹‹ክላ›› ብያለሁ።

፠ ፠ ፠

በኔ መረዳት፣ በኔው አይምሮ፣ በሰማሁበት ጆሮ (ያልሰማኋቸው ቢኖሩም)፥ ከሰማኋቸው መካከል ግን ግጥማቸውን ሳነብ ሳይሆን ግጥምን ወይም ግጥማቸውን ሲያነቡ ‹‹ባፋችሁ ማር ብሉበት›› ከሚያስብሉኝ ሴት ገጣሚያን መካከል ከቀደሙት ፊርማዬ ዓለሙ(ነፍስ ኄር) እና ዓለምፀሐይ ወዳጆ ሲሆኑ ካልቀደሙት ደግሞ ረድኤት ተረፈ እና ምልዕቲ ኪሮስ የሚባሉት ናቸው። (የዓለምፀሐይማ ንግግሯ ራሱ የሆነ የዜማ ሥነ ምት አለው ልበል? ግናስ ተዋናይም አይደለች….) ብቻ አራቱ ሲያነቡ ውቃቢዬ ይወዳቸዋል። ውቃቢ ከወደደ ደግሞ የጆሮ ኩክን ከማጽዳት በስተቀር ምን አማራጭ አለ። ምንም። ስለዚህ ጣትን ወደ ጆሮ ቀዳዳ፣ ለኩክ ጠረጋ. . . (ግን አሁን ሳይሆን ሲያነቡ ይደርሳል)፤ የሆኖ ሆኖ ሌላ እስኪመጻልኝ፥ እነሱ ይምጹብኝ።

ግና! ግን፤ ደሞ ወዲህ… ግጥሟ በሌሎች ሲነበብና በራስ አፍ ሲያነቡት በግጥሞቿ እንደ ተዓምር ቃል እግዚኦ! የምታስብለኝ ከቀደሙት እስከ አልቀደሙት የእሷን ያህል ሴት ገጣሚ የለም የምልላት ሴት ገጣሚ ግን መቅደስ ጀምበሩና መቅደስ ጀምበሩ ብቻና ብቻ ናት።(ያው እስካነበብኳቸው የሴት ገጣሚያን ግጥሞች አንጻር፤) ዛዲያ የመቅደስ ያህል የለም ማለቴን ያለመነ ‹‹ንባስል››ን፤ ማመን የፈለገ ደግሞ ‹‹ሙጋ››ን ማንበብ ይችላል። (ከሌሎች ጋር ያሳተመችው ‹‹እኛና 170 ግጥሞች››ም አለ።) ያነበበም ለምሥክርነት ይቆማል። የዋስ ቃል ይሰጣል። (ደሞም ይተቻል።)

፠ ፠ ፠

በቤተክርስቲያን መቅደስ ውስጥ ታቦት እንዳለ ሁሉ በመቅደስ ጀምበሩ ውስጥ ደግሞ ተውባ ያልገለሞተችው ወይዘሪት ግጥም አለች።

ከሴት በይበልጥ ወንድ ገጣሚ የበዛው። የመብዛቱን ያህል ብዙ ደኅና ወንድ ገጣሚ ያልታጣው ሴት መግጥም(መገጠሚያ) ሆና ነው፣ ብልም፤ እንደ ጥላ ካላለፉ፣ እንደ ጤዛ ካልረገፉ ሴት ገጣሚያን መካከል ግን ምዕራቡን ትቶ ምሥራቁን ላዬ ሰው አንዷ መቅደስ ጀምበሩ ናት። ኦ! የጀምበር ልጅ መቅደስ።

ግጥም ላይ ጥናትና ምርምር ያደረገው ብርሃኑ ገበየሁ(ረ/ ፕሮፌሰር) እንዲህ ይላል ስለ መቅደስ ጀምበሩ፡-

   ‹‹በመቅደስና በባህሏ መካከል ያለውን ጥብቅ ትስስርና የገጣሚዋን ታላቅ ኪናዊ ተውህቦ ከሚያስረግጡ ሥራዎቿ አንዱ፣ ነባሩን የጥቃት ማስታመሚያ፣ የወኔ ማባበያ፣ የመከፋት፣ የመሸነፍ ህመም ማሰላሰያ ቀረርቶ የዘመናዊው ሰው ምሁራዊ ህመም፣ መገለጫ ለሆነው ተብሰልስሎት መያዣነት መገልገሏ ነው።›› ይልና አከል አድርጎም ‹‹መቅደስ የግጥምን አድባር፣ የግጥምን ቆሌ የምትጠራው ‹‹አለቀሰ ብዕር፣ ብዕር አለቀሰ›› እያለች ነው። ይህ ምናባዊ ስንቅን ከባህል ባህር የመጥለቅ ዝንባሌዋም ሳትወድ የግድ ምስሎቹዋን፣ አገላለጾቹዋንና ቋንቋዋን ካደገችበት ባህር እንድትዘርፍ እንዲሁም ግጥሞቿ ቀያዊ ለዛና ቃና እንዲሰማባቸው ያደርጋል። በዚህ ረገድ፣ ከትውልዷ ገጣምያን መካከል መንፈስና ባህል የምትጋራው ከወንድዬ ዓሊ ነው።›› (መድበለ ጉባኤ፤ ዘመናዊ የአማርኛ ሥነ ግጥም፤ አንዳንድ ነጥቦች)

፠ ፠ ፠

…ያልታደለ የግጥም አንባቢ የመቅደስ ጀምበሩን ጥሩ ግጥሞቿን አግኝቶ ሳያነብ አነበብኩ ይላል፤ ብዬ ከፍ ባለ አድናቆት አድናቆቴን መግለጤ በስሜት ሳይሆን በምክንያት ነው። ምክንያቴ ደግሞ ግጥሟን ማንበቤ። ይህን ጽሑፍ የምታነቡም የመቅደስን ግጥም አንብቡ። ዛዲያ የመቅደስን ግጥም ሲያነቡ እንደ አንቡላንስ ሹፌር ማፍጠንና መፍጠን አያስፈልግም። ያው ከተነበበ በኋላ ግጥሟ ማንዘርዘሩና መንዘሩ ስለማይቀር ኃይል ቆጥቡ ብዬ ነው።

ልጅ እያለን የወታደር ብስኩት ጠንካራ ነበር። ወይንም የኛ ጥርስ ደካማ ነበር። አንዳንዴ ያንዱ ጥንካሬ የሌላኛው ድክመት ማነስ ሆኖ ስለሚገኝም ይሆናል። ይህ አይነት ጠባይ ግን በመቅደስ ጀምበሩ ግጥም በተለይ ‹‹በንባስል›› መድበል አይታይም። እንዲያውም ማጣጣም ለቻለ በይበልጥ ጣዕም አለው። እሷም ‹በንባስል› መግቢያ… ‹‹ሥነ ግጥም የጠንካራ ስሜት ቅጽበታዊ ነፀብራቅ ነው፤ ለዚህም መንስኤ የሚሆነው በአጽዕኖት ተሰብስቦ የተቀመጠና የሰከነ ስሜት ሲኖር ነው›› እንድትል ግጥሞቿ የቆይቶ ጣዕምና ምሥጢር ደግሞ በግልብ ብሶት፣ በእልህ እሮሮ፣ በከንቱ ማማረር፣ ባጉል ድርቅና፣ ባልሰከነ ትኩስ ስሜት ብቻና በከሸፈ በዕለት ፍልስፍና ስላልተገኙና ስላልተገጠሙ ነው። ይልቅ እንደቡና ሰክኖ ስለተቀዳ ነገን – ትናትናን – ዛሬን ይዋጃሉ። ያወያያሉ። ያጨዋውታሉ። አቦል፣ ቶና፣ በረካ እያሉ. . .

፠ ፠ ፠

ቅድመ ትውስታ

በካፊያ ምች ‹‹የዕድሜ ልክ ልክፍቴን ያኔ አስለከፈችኝ›› እንዲል ተፈሪ ዓለሙ። መቅደስ ጀምበሩንም የተለከፍኳት ‹‹የአማርኛ ሥነ ግጥም፤ ንድፈ-ሃሳብ፣ ማብራሪያ፣ ትንታኔ›› በተሰኘው በብርሃኑ ገበየሁ መጽሐፍ ውስጥ ተቀንጭቦና ተቆንጽሎ በቅጸላ አጻጻፍ በተጻፈው ‹‹ያፈረስኩት ጎጆ›› በተሰኘ ግጥም ውስጥ ባሉት እንዲህ በተሰኙ ሥንኞች ነው. . .

                              ‹‹ያፈረስኩት ጎጆ…እሱ ተስተካክሎ ራሱን ቀልሶ

                                 የናቅሁት ትዳሬ ቢንቀኝ መልሶ

                                 ምጥ እንደያዛት ሴት…ጭንቄ እየተነሣ

                                 ሰዓት በጨመረ

                                 እንደሞት ፍርደኛ…አካሌ እየሳሳ

                                 ቀን በተቆጠረ

                                 መነሻ እንደሌለው…ወድቆ እንደተረሳ

                                 ቀለሜ ረገፈ..ቅስሜ ተሰበረ።›› ….በተባሉ በእነዚህ ውስን ስንኞች ነበር፤ አጀብ! ይበል! ያልኩት። ይሰመርበት በተቀነጨበ የግጥም ሥንኝ ነው። ከዚያ በኋላም ስለ መቅደስ ጀምበሩ ማሰስ፣ መዳሰስ ጀምርኩ። ግና አገኛት ዘንድ እሩቅ ሆነች፤ ጎግል ግን ‹‹እኛ እና 170 ግጥምች››ን ከሌሎች ገጣሚያን ጋር ማሳተሟን ጠቆመኝ፤ ከዚያ ውጭም አላውቅልህም አለኝ፤ (ከእኔም አፈላለግ አለመቻልም ይሆናል) … እኔም እንደ ፊርማዬ ዓለሙ በአጸደ ሥጋ እንደሌለች ደምድሜ መጽሐፏን ማሰስ ጀምርኩ( ግን ከ‹እኛ እና 170 ግጥሞች› እንጂ ‹ንባስል›ና ‹ሙጋ› የተባሉ መድበሎች እንዳሏት አለማወቄም ሳይዘነጋ።) ከሌሎች ጋር ያሳተመችውን መድበልም በየመጽሐፍት ቤቱ ብጠይቅ ላገኘው ባለመቻሌ በተለከፍኩባት ‹ያፈረስኩት ጎጆ› ቅንጭብ ሥንኝ እያብሰለሰልኩ ሳለሁ፣ ከጊዜ ሂደት በኋላ ግን ከአንድ መጽሐፍ ምረቃ ዝግጅት ላይ ‹ግጥም የምታቀርብ መቅደስ ጀምበሩ› የሚል ማስታወቂያ አየሁ፤ ለመጽሐፉ ምረቃ ብዬ ሳይሆን እሷን ብዬ ከዝግጅቱ ሄድኩ። እውነትም ‹ሙታለች› ያልኳት ራሷ መቅደስ ጀምበሩ ናት። እሠይ!

በዝግጅቱ መድረክ ላይም ግጥም አቅርባ ስትጨርስ ጠብቄ ከተቀመጠችበት በመሄድ መግደርደሬንና ማፈሬን ትቼ አናገርኳት፤ ትህትናዋ አጀብ! እርጋታዋ ያረጋ ነበር። ነበር ብቻ ሳይሆን በሌላ ቀን ስንገናኝና በስልክ ስናወጋም ያረጋግጥኩት ውሸት የሌለው እውነት ነው።

….. ከጊዜ በኋላም መጽሐፍቶቿን ፈልጌ እንዳጣሁ ስነግራት፤ ያለበት ቦታም ካለ እንድትጠቁመኝ አክዬ ሳናግራት ሁለት መድበሎቿን ራሷ ሰጠችኝ፤ አነበብኳቸው፤ የተለከፍኩባት ግጥም ‹‹ያፈረስኩት ጎጆ››ም ንባስል ውስጥ እንዳለች አወቅኩ፤ (ንባስል፡- ማለት ምን ማለት ነው የምትል ሳተና ካለህ፤ እንዲህ እልሃለሁ፡- ንባስል ያገሬ ገበሬ አዲስ ቀፎ ከመስቀሉ በፊት ቀፎው ንብን እንዲስብ፣ እንዲጠራ ቀፎውን የሚያጥንባት የቅጠል አይነት ቅጠል ናት።) ይህም መቅደስ ጀምበሩ ንባስል የመጀመሪያ ሥራዋ ስለሆነች ‹ንባስል መጽሐፌ ብትስብልኝ፣ ብትወደድልኝ፣ አንባቢን ብትጠራልኝ፣ ብታገኝ፣ ብትነበብልኝ› ለማለት ነው። እውነትም ንባስል። ሳቢ። ተወዳጅ። ጠሪ።

፠ ፠ ፠

ግጥሞቿን በሰፌድ ለዝክር እንደቀረበ ቆሎ እየዘገንኩና እየቆነጠርኩ አንባቢያዊ ዳሠሣን ላደርግ ሻትኩና ለብቻዬ ያደረግኳቸውን የማጣጣም ስሜቶቼን በዳሠሣ ሥም ስሞ መሸጥ ስለመሰለብኝ ተውኩት። (አልያም አቅም ተስኖት ለአቅመኛ ጠቆመው ብላችሁም አስቡት።)

፠ ፠ ፠

የኔ ሀዲስነት ብሉይን አለመካድ ነውና አንድ ቀን እህልውኃ ከፈቀደ ከወንድዬ ዓሊና ከመቅደስ ጀምበሩ ጋር ምግባር ባልጎደለው ጉባይ ላይ ለመዋጋት ሳይሆን ለቅኔ ዘረፋ ‹‹ዘራፍ›› እንደምል ሁላችን እስካለን ተሥፋ አለኝ።

እስተዚያው ግን ይህን ጽሑፍ እንዲህ ልቋጭ፦ ከ‹ብርአንባር ሰበራ› ባለው ጭንቅና እህህታ እንዲሁም በልጅ መውለድ መኃል ያለው የጩኸት ምጥ ካለፈ በኋላ የሚገኘው ሀሴት፣ ደሥታና እረፍት ማለት የመቅደስ ጀምበሩን ግጥም ማንበብ ማለት ነው። ምክንያቱም ግጥሞቿ በጭንቅ፣ በእህህታ፣ በምጥ፣ የተገኙ ናቸውና።

                                                                                                  ብቻ መኖር መልካም!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!! በክርስቲያኖች ዘንድ ጥምቀት...

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...