ግጭት የጥፋት ምንጭ እንዳይሆን ብዙ መሥራትን ይጠይቃል!

Date:

ከእሸቱ ደስታ

ግጭት አንደኛው ወገን የሌላኛውን ወገን ድርጊት ባሕሪ፣ እሴትና አጠቃላይ አመላካከት ከራሱ ጋር ተፃራሪ ነው ብሉ ሲያምን የሚከሰት ነገር ነው፡፡

ግጭቶች በሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ ከዚህም አልፎ በአንድ አገር ማህበራዊ፣ ኢኮናሚያዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ላይ የሚያደርሱት ወይም የሚያስከትሉት ተፅዕኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ ግጭቶችና ድህነት ቁርኝት አላቸው፡፡ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እጥረት ሽሚያንና ውጥረትን በተለያዩ ወገኖች መካከል ይፈጥራል፡፡ በዚህ የተነሳ ግጭት ሊነሳ ይችላል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት ሂደት ውስጥ አያሌ የግጭት ታሪኮችን ያሳለፈች ሲሆን በተለይ ባለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የተከሰቱት ግጭቶች በደረጃም በቁጥርም ከፍተኛ ሆነው ታይተዋል፡፡ መነሻ ምክንያቶቻቸውም የተለያዩና ውስብስብ ናችው፡፡ በሐሳብ ያለመግባባት የተነሳ በግለሰቦች መካከል የሚፈጠር ግጭት አለ፡፡ ያልተጣጣሙ ወገኖች፣ ተፃራሪ የሆነ ሐሳብ ያላቸው ግለሰቦች፣ ብሔረሰቦች ወይም ሕዝቦች የሚፈጥሯችው አካላዊና መንፈሳዊ ግጭቶችም ይኖራሉ፡፡

የተለያዩ ባለሙያዎች ለግጭት የተለያየ ደረጃ ይሰጣሉ፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው ከግጭት በፊት፣ ሁለተኛው ግጭት ራሱ፣ ሦስተኛው ከግጭት በኋላ፣ አራተኛውና የመጨረሻው ውጤት የሚለውን ይወስዳል፡፡

በዚህ መጣጥፍ የምናተኩረው በአብዛኛው በአካላዊ ግጭት ላይ ነው፡፡ በአገራችን ከቤተሰብ እስከ መንደር፣ ከጎሳ አስከ ነገድና ሕዝብ የዘለቁ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ የራሳችን ውጤት ናቸው፡፡ በተለይ የጎሳ ግጭት ሊከሰት የሚችለው በኢኮኖሚ ባልዳበሩና ኋላቀር ባህል በሚከተሉ ሕብረተሰቦች አካባቢ ነው፡፡ እነዚህም በአብዛኛው ከብት አርቢዎች ሲሆኑ ሥርዓታቸውን የሚያከብሩት ራሳቸው አውጥተው በሚጠቀሙበት ሕግ መሠረት ነው፡፡ እንደዘመናዊ መንግሥት ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት ጦር ሰራዊት የሚባል ነገር የላቸውም፡፡ አኗኗራቸው ከቦታ ቦታ ስለሚያዘዋውራቸው የግጦሽ መሬትም ሆነ ውሀ ያጋጫቸዋል፡፡ በጋብቻ ጊዜ ለምሳሌ ወጣቶች በርከት ያለ ጥሎሽ መስጠት ካለባቸውና ቤተሰቦቻቸው ያንን ማድረግ ካልቻሉ ያጎራባች ጎሳ ከብት ይዘርፋሉ፡፡ ሴት ልጅ ጠልፈው ማግባትም አለ፡፡ እነዚህ እንግዲህ ዓለም አቀፍ ባሕሪም ያላቸው ናቸው፡፡ በአንድ አገር ወይም ቦታ ተወስነው የሚቀመጡ አይደሉም፡፡

እነደነዚህ ዐይነት ግጭቶች በአብዛኛው በታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች የሚዳኙ ናቸው፡፡ ችግሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣና የሚታወቅ ስለሆነ ይፈታል፡፡ ፖለቲካዊ ምክንያት የለውም፡፡ በፊት እንዲህ ይሁን እንጂ ሁልጊዜ አይደለም፡፡

ቅኝ ገዢዎች ከመጡ በኋላ ወይም ድንበር ዘለል የማእድን ሀብት አግበስባሽ ድርጅቶች እንዲህ ዐይነቱን በጎሳዎች መካካል የሚካሄድ ግጭትን ይጠቀሙበታል፡፡ አንዱን ጎሳ በሌላው ላይ በማስነሳትና በማጋጨት የአካባቢውን ማእድን የመቆጣጠር ዓላማ አላቸው፡፡

ከዚህ ከፍ ብሎ የሚመጣው ደግሞ የድንበር ግጭት ነው፡፡ በሶማሊያና በኢትዮጵያ፣ “ባድሜ ይገባኛል/አይገባኝም” በሚል፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል የተካሄደውንም ግጭት ማስታወስ ይቻላል፡፡

ግጭት ኢኮኖሚያዊም ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የታሪክ ቋጠሮ ሆኖ የሚኖርበት ጊዜ አለ፡፡ ትንሿ  ነገር የኋላ ታሪክ ትቀሰቅሳለች፡፡ ችግሩ የተከሰተው ከመቶ ዓመታት በፊት ሆኖ እና ተመዝግቦ ሊሆን ይችላል፡፡ የአካባቢው ሕዝብ ግን ከትውልድ ትውልድ እየተነገረው ሲተላለፍለት ስለመጣ ያውቀዋል፡፡ ሕብረተሰቡ በኢኮኖሚ እራሱን እየቻለ ሲመጣ በእንደነዚህ ዐይነቶቹ ችግሮች ላይ ተወያይቶ ስምምነት ላይ ሲደርስ ያቆማቸዋል፡፡ አልፎ አልፎ ልዩ ልዩ ዘዴዎችን ለምሳሌ ጋብቻን በመጠቀም ሲያረግበው ይታያል፡፡

በታሪክ ወደኋላ ሄደን በምናይበት ጊዜ ለግጭት መንስኤ የሚሆኑት ነገሮች ድብቆች ናቸው፡፡ ምክንያት የሆኑ ፋይሎችን አናያቸውም፡፡ የሚጋጩትን ብቻ ነው የምናየው፡፡ እንዲህ ዐይነቶቹ ክስተቶች በአህጉራችን አፍሪካ ለምሳሌ በኮንጎ፣ በኡጋናዳ፣ በሱዳንና ደቡብ ሱዳን እንዲሁም በማዕከላዊ አፍሪካ ልዩ ተልእኮ ወይም ጥቅም ባላቸው ዓለም አቀፍ የተለያዩ ድርጅቶች አማካይነት ተቀስቅሰው ይታያሉ፡፡ ጦር መሳሪያ አቃባዮቹ፣ የመገናኛ መሣሪያ ሰጪዎቹ እና አሰልጣኞቹ እነዚህ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች ሲሆኑ ተመልሰው ደግሞ ዳኛ ሆነው አስታርቃለሁ፣ እቀጣለሁ ብለው ይመጣሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ የዓለም የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሚባል ተቋቁሞ አፍሪካውያን እየቀረቡ ሲዳኙ ከበስተጀርባቸው ሆነው እነርሱ እርስ በእርስ እንዲተላለቁ ያደረጓቸው ኃይሎች አይታዩም፡፡ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሰዎች ተፈርዶባቸው እንዲታሰሩ ወይም እንዲሞቱ በማድረግም ችግሩ አይቆምም ወይም አይፈታም፡፡ ምክንያቶቹ እነሱ በሆኑ ይቆም ነበር፡፡ ሌሎች ስለሆኑ እና ለእነሱ መፍትሔ እስካልተሰጠ ድረስ ትግሉ ይቀጥላል፡፡ የአፍሪካን የወርቅና የአልማዝ ማእድናት እንዲሁም ነዳጅ ለመቀራመት ሲሉ መሰረታቸው ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ፣ ከፈረንሳይና የመሳሰሉት ኩባንያዎች ናቸው ይህን በመስራት ላይ የሚገኙት፡፡ መዘዞቹም አውጋዦቹም እነሱ  ስለመሆናቸው ግን በይፋ አይነገርም፡፡ ሚዲያዎች ራሳቸው አያነሱትም፡፡

አሁን ባለው የአለም ሁኔታ አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች ድንበር ዘለል ኩባንያዎች ያቋቋሟቸው ደፈጣ ተዋጊዎች ሰለባ ሆነዋል፡፡ እነርሱም በግላቸው ጥፋት የለባቸውም ለማለት አይደለም፡፡ ዋናዎቹ ግን ተደብቀዋል፡፡ እነዚህን ለመቆጣጠር እስካልተቻለ ድረስ አፍሪካ ውስጥ ያሉት ግጭቶች ማቆሚያ ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡

ሌላው በአገራችን የማእከላዊነት ጉዳይ በራስ ቋንቋ የመናገር፣ በአስተዳደር የራስን ሰው መመደብ የሚለው ለግጭት መፍትሄ ሰጪ ሊሆን አይችልም፡፡

አስቀድሞ ተጓዳኝ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር አድርጊያለሁ ማለት ብቻ አይበቃም፡፡ እውነተኛውን ሥልጣን ለሕዝብ ማስረከብ ይገባል፡፡ ሕዝብ የፈለገውን ይመርጣል ያልፈለገውን ያወርዳል፡፡ ይህን ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ ችግር አይፈታም፡፡ እንደገና እነዚያ በሕዝብ የተመረጡ ሰዎች አካባቢውን ለመጥቀም መልካም ፍላጎት ቢኖራቸውም የእውቀት ማነስ ሊኖርባቸው ስለሚችል ማሰልጠን ይገባል፡፡ የመንግሥት አስተዳዳሪነት ብቃት እንዲኖራቸው ይህ አቅም ግንባታ የሚባለው ነገር መሰራት ይኖርበታል፡፡

ግጭት የእድገት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ሁሉ የጥፋትም ምንጭ ሊሆን ይችላል፡፡ በዓለም ታሪክ ሥርዓትን ለመለወጥ ሲባል የእርስ በርስ ጦርነቶች ተደርገዋል፡፡ ግዛት ለማስፋፋት በሚልም እንዲሁ ጦርነቶች ተካሂደዋል፡፡ እነዚህ ወደ እድገት ወይም መሻሻል ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የእነዚህም ተቃርኖ ሊኖር ይችላል፡፡ በታሪክ የሰለጠነ ሕዝብ ያልሰለጠነውን ድል ያደርገዋል፡፡ ወደፊት የሚያራምድና ወደኋላ የሚመልስ አለ፡፡ የሕዝብን የኢኮኖሚ ሕይወት ለማሻሻል ያላቀደ ሕይወቱን በተሳካ ሁኔታ እንዲመራ የማያደርግ ግጭት አስካሁን ድረስ ይቆረቁዛል፡፡

በአገራችን ያለው ውሃ ጥቅም ሳይሰጥ መሬቱም እርሻ ላይ ባለመዋሉ የመጣው ልማት ሳይሆን ረሀብ ነው፡፡ ተቃራኒ የሆነ አዎንታ ነው ያላቸው፡፡ ለሀገር እድገት ሲባል ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲኖር ከተፈለገ ለግጭት ባሕሪያት መፍትሔ መፈለግ አለበት፡፡ የግጭቱንና የካባቢውን ባሕሪ በትክክል መርምሮ ማወቅ ለአገዛዝ ሥርዓቱ ወይም ለተወሰነ ቡድን በሚጠቅም መልኩ ብቻ ሳይሆን ሀገርን በሚያሳድግ ሕዝብን አስተባብሮ ለልማት በሚያስቆም መልኩ የሚያነሳሳ መፍትሔ እስከተሰጠ ድረስ ማደግ ይቻላል፡፡

የመሬት ጥበት የለብንም፡፡ ሕዝባችን ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ አብሮ የመኖር ባሕል ያዳበረ ነው፡፡ ለዚህም ነው የብሔር ብሔረሰቦች ማንነት ሰርፆ መግባት ያልቻለው፡፡ ዛሬ በዘር፣ በጎሳ እያልን ልናጋጨው የምንፈልገው ታሪኩን ባለማወቅ ነው፡፡ ማንነቱን ጠንቅቆ ባለማወቅ የተነሳ ነው የሚሉ ተማራማሪዎች አሉ፡፡ ነፍሳቸውን ይማረውና የዶ/ር ኃይሌ ወልደሚካኤል የጥንት ምርምር 90 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተቀላቀለ ነው ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን የጠበቀ  ነው፡፡ ያንን ማንነት ከተቀበለ ቆይቷል፡፡ ያን ማንነት ተውና አዲስ ያመጣንልህን ልበስ ቢባል አይለብስም፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ነፃነቷ አደጋ ላይ በወደቀ ጊዜ ሁሉም ብሔረሰብ ሞቶላታል፣ ደምቶላታል ይሄ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን በሚሰራጭ ፕሮፓጋንዳ ሊታጠፍ አይችልም፡፡ ለጊዜው ውዥንብር መፍጠር ይቻላል፡፡ እየቆየ ሲሄድ ግን ይቀራል፡፡

እንግዲህ በአገራችን ግጭትን ለመከላከልና ለማስወገድ የመንግሥት ሓላፊነት ብቻ አድርጎ መውሰድ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል ተብሎ አይገመትም፡፡ በዚህ ረገድ ይህንኑ የተረዳውና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አካል የሆነው ኢንሼቲቭ አፍሪካ ካሉት ፕሮግራሞች አንዱ በሰላም ግንባታና በግጭት መከላከልና ማስወገድ ዙሪያ ላይ ያተኮረ የተግባር እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህም ይበል የሚያሰኝ ሥራ ነው፡፡ ሌላው በአገራችን የሚገኙ ሕዝባዊና የሙያ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በግልም ኾነ በቅንጅት ተከታታይነት ያለው የግጭት መከላከልና ማስወገድ ተግባር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይኽ ሲሆን ብቻ ነው በአገራችን የግጭት መንስኤዎቸ ስንኮፍ ነቅሎ ማውጣት የሚቻለው፡፡  

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...