የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ልጅ፣ ሰምሃል መለስ ዜናዊ በቅርቡ በትግራይ የወጣውን አዲስ አዋጅ “የደርግን ስርአት የሚያስታውስ አዋጅ” ስትል የሰላ ትችት አቀረበች።
ከ #ትግሃት ሚዲያ ጋር በቅርቡ ቃለምልልስ ያካሄደችው ሰምሃል መለስ፣ አዲሱ አዋጅ ህግ በሚያውቁ ሰዎች ይቅርና ማንበብና መጻፍ በሚችሉ ሰዎች እንኳን ተጽፏል ብላ ለማመን እንደምትቸገር ገልጻ “ብዙ ችግር ያለበት አዋጅ ነው፤ ሌላው ቀርቶ ሀሜትን እንኳን የማይፈቅድ የደርግ ዘመን ህግ ነው” ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።
የህወሓት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ያነሷቸውን አስተያየቶች በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላት ሰምሀል፣ የፈትለወርቅ መግለጫ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንዴት እንደሚታረም የመፍትሄ አቅጣጫ ከማቅረብ ይልቅ የሷና የቡድኗን ስልጣን ማጠናከርን ብቻ ታሳቢ ያደረገ አሰልቺ ዲስኩር ስትል ገልጻዋለች።
አሁን ያለው የአለም ሁኔታም ሆነ ዲፕሎማሲ እንዴት እንደሚሰራ ፈትለወርቅ ጨርሶ አልገባትም ስትል የምትሟገተው ሰምሃል፣ ዲፕሎማሲ ማለት ለሚወጡብህ የተቃውሞ መግለጫዎች መልስ መስጠት ማለት አይደለም ከዛ ይልቅ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተገንዝቦ የማሻሻያ እርምጃዎችን ይዞ መቅረብ ነው ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።
ቀደም ባሉ ጊዜያት በህወሓት ዙሪያ ብዙ ምሁርና አሰላሳይ ልሂቅ ነበር የምትለው ሰምሃል አሁን ግን ያ ሁሉ አቅም ተበትኖ ፓርቲው እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ ማየት እንደሚያሳፍራት በቁጭት ገልጻለች።
አውራምባ ታይምስ [መቐለ]
