ከጥቂት ወራት በፊት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቺቺኒያ ያልተጠበቀ ጉብኝት አድርገዋል። ከ13 አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቺቺኒያ የተገኙት ፕሬዝዳንቱ ወደ ዩክሬን ለመዝመት ከተሰለጠኑ ወታደሮችም ጋር መገናኘታቸው ተሰምቷል። ፑቲን በዚሁ ወቅት ‹‹እንደናንተ አይነት ወንዶች ይዘን በፍጹም በማንም አንሸነፍም›› ማለታቸውም መነጋገሪያ ኾኖ ነበር። ከዚህም ባሻገር ፑቲን ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ራምዛ ካዲሮቭ የተበረከተላቸውን የቅዱስ ቁርአን ሥጦታ ስመው ሲቀበሉ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስልም በማኅበራዊ ሚዲያዎች በስፋት ተሰራጭቶ ነበር፡፡ በዛሬው የግዮን ‹‹ዓለም አቀፍ›› ዓምዳችንም ስለዚህ አስገራሚና ሞገደኛ የቺቹኒያ ፕሬዝዳንት፣ ፖለቲካውን እና ከሩሲያ ጋር ያለውን መስተጋብር እናስቃኛችኋለን፡፡
በየጊዜው በሚሰነዝራቸው አስተያየቶቹም ኾነ እና በሚፈጽማቸው ድርጊቶቹ በዓለማችን በሞገደኛ ፖለቲከኛነቱ በስፋት የሚታወቅ፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የመላው አውሮፓ እና አሜሪካ መንግሥታት ሥሙን በተደጋጋሚ የሚያብጠለጥሉት ሰው ነው ፤ የቺቺኒያው መሪ ራምዛን ካዲሮቭ፡፡
‹‹የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዓለማችን ተስተካካይ የሌለው ምርጥ የአመራር ጥበብን የተካነ ሰው ነው፡፡ ይኽንን ዓለም ሊያውቅለት ይገባል፡፡ ፑቲን የዓለማችን ፕሬዝዳንት ነው›› በማለት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ምሥክርነቱን የሚሰጠው የቺቺኒያው ፕሬዝዳንት ራምዛን ካዲሮቭ ሩሲያ የዩክሬንን ጦርነት በድል እንደምታጠናቅቅም በእርግጠኝነት ይናገራል፡፡
ራምዛን ካዲሮቭ አነጋጋሪ ተግባራትን በመፈጸም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሞገደኛ ስብዕና እንዳለው ካሳመኑ በርካታ ተግባራት መካከል አንዱ በ2011 ግሮዝኒ በሚገኘው የእግር ኳስ ስታዲየም ራሱ በተጫዋችነት የተካፈለበት የእግር ኳስ ግጥሚያ ነበር፡፡
ጨዋታው ታዋቂ እና የቀድሞ የሶቭየት ሕብረት ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በአባልነት የሚገኙበትና ፕሬዝዳንት ካዲሮቭ አምበልነት የሚመራው የእግር ኳስ ቡድን በአንድ በኩል፣ በዓለም ከፍተኛ ዝና እና ታዋቂነት ያተረፉ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ማለትም፣ ሮናልዶ፣ ሮማርዮ፣ ዱንጋ፣ ቤቤቶ፣ ካፉና ሌሎችም የብራዚል ዜግነት ያላቸው ተጨዋቾችን በአባልነት ያቀፈው የእግር ኳስ ቡድን ወደ ቺቺኒያ ተጋብዞ የተካሔደ ሲኾን፣ ብዙ ሺህ የእግር ኳስ ተመልካቾችም የታደሙበት ነበር፡፡
ማርች 8 ቀን 2011 በግሮዝኒ ብሔራዊ ስታዲየም በተካሔደው የቡድኖቹ ግጥሚያ ላይ የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት ራምዛን ካዲሮቭ ሁለት ጎሎች ቢያስቆጥርም በጨዋታው የእርሱ ቡድን 6 ለ 4 በኾነ ውጤት ከመሸነፍ ግን አልዳነም፡፡
በቺቺኒያ በኩል የጀርመኑን እውቅ የእግር ኳስ ተጨዋች ሉተር ማትያስን በውሰት አስመጥቶ ያጫወተው ራምዛን ካዲሮቭ፣ የእግር ኳስ ግጥሚያው በዓለም አቀፍ ደረጃ በእርስ በእርስ ጦርነት የምትታወቀው ሀገሩን ገጽታ ለመቀየር እንደተጠቀመበት አስታውቋል፡፡
ሞገደኛው የቺቺኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት በሜይ 26 ቀን 2015 በታዋቂ የፊልም ዳይሬክተር እና የዓለማችን እውቅ የፊልም አክተሮች በሚካፈሉበት የሆሊውድ ፊልም ላይ በመሪ ተዋናይነት ለመሥራት ከስምምነት ላይ መድረሱን በመግለጽም ‹‹Who ever doesn’t understand will get it›› የተሰኘ ፊልም ላይ በመሥራት የሀገሩን የፊልም ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት እንደሚጠቅም አስታውቆም ነበር፡፡
ሰውየው የተለያየ ሙያ ውስጥ በመሳተፍ የማይችለው ነገር የለም እንዲባል ይፈልጋል የሚሉት ተቺዎቹ፣ በ2016 በሀገሩ ቴሌቭዥን ጣቢያ ‹‹ቻናል ዋን›› ላይ ‹‹ዘ ቲም›› የተባለ የሪያሊቲ ሾው በማዘጋጀት እና በዝግጅቱ ላይ የሚታደሙ ዜጎችንም ከመላው ሩሲያ በመጋበዝ በዚህ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይ እንዲወዳደሩ፣ ‹‹በውድድሩ የሚያሸንፈውን ግለሰብም የቺቺኒያ ስትራቴጂክ ዴቨሎፕመንት ኤጀንሲ ዋና ኃላፊ አድርጌ ሾመዋለሁ›› ሲል አስገራሚ ማስታወቂያ ጭምር አስነግሮ ነበር፡፡ በርግጥም በራምዛን ካዲሮቭ በተዘጋጀው የቴሌቭዥን የሪያሊቲ ሾው ውድድር አሸናፊ የኾነው የዱስዳርስዶፍ ተወላጁ ፊሊን ቫሪንቺንዋም የፕሬዝዳንቱ ረዳት የኤጀንሲው ዳይሬክተር ተደርጎ ተሹሟል፡፡
በ2020 በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተሰጠ ከፍተኛ ወታደራዊ ሹመት የሜጀር ጀነራልነት ማዕረግ የተሰጠው ራምዛን ካዲሮቭ፣ በሩሲያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሥር የሚገኘው ‹‹የሩሲያ ብሔራዊ ዘብ›› አዛዦች አንዱ ኾኖ ሀገራዊ ግዳጁን እየተወጣ መኾኑን በማኅበራዊ ገጽ ላይ ለንባብ ባበቃው ጽሑፍ አስታውቋል፡፡
በሩሲያ የዩክሬን ጦርነት እንደተቀሰቀሰ የቺቺኒያው ፕሬዝዳንት ራምዛን ካዲሮቭ፣ በዩክሬን ላይ ጂሃድ ወይም ‹‹ቅዱስ ጦርነት›› ያወጀ ሲኾን፣ በብዙ ሺህ የሚጠጋ የቺቺኒያ ተዋጊ ወታደሮችን በሩሲያ ጦር ኃይል እዝ ሥር በማሰለፍ በጦርነቱ የተፈለገው መሥዋዕትነት ተከፍሎ ሩሲያ ድል እንድታደርግ ጽኑ እምነቱ መኾኑን በመገናኛ ብዙኃን በመቅረብ ጭምር መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ፕሬዝዳንት ራምዛን ካዲሮቭ የዩክሬን ኃይሎች በአሜሪካ እና በእንግሊዝ መንግሥታት አይዞህ ባይነት ሩሲያን ለመቅጣት የገቡበት ጦርነት ‹‹ለዜጎች እልቂትን፤ ለኢኮኖሚያቸውም ውድመትን የሚያመጣ ነው፡፡ ሁለቱ መንግሥታት ማለትም እንግሊዝ እና አሜሪካ የሰይጣን ጉዳይ ፈጻሚዎች ናቸው፡፡ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ደግሞ የእነርሱ ተላላኪ ነው፡፡ እርሱን አንገቱን ቆርጦ ላመጣ በበሊዮን የሚጠጋ የገንዘብ ሽልማት እና አምስት ኪሎ ወርቅ እሸልማለሁ›› ሲልም በጀብደኝነት ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡
ከጋዜጠኞች ጋር ፈጽሞ የማይግባባው ሞገደኛው ቺቺኒያዊው ፕሬዝዳንት፣ የሩሲያው የተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሚ ሲኾን፣ ለአብነት እንኳን በኢንስታግራም ገጹ ሦስት ሚሊዮን ተከታዮች አሉት፡፡ በተጨማሪም በፌስቡክ 760 ሺህ 860፣ በትዊተር ወይንም በአሁኑ ኤክስ 331 ሺህ ተከታዮች ብሎም በሩሲያው ቪኬ ሶሻል ኔትወርክ ደግሞ 500 ሺህ ተከታዮች ያሉት ፔጅ ባለቤት እንደኾነ፣ አብዛኛውን ጊዜውን በእነዚህ የበይነ መረብ የዜና አውታራት የሚያገኘውን መረጃ ለመንግሥታዊ አስተዳደሩ እንደ ግብኣት እንደሚጠቀምም ሲናገር ይደመጣል፡፡
ሞገደኛው የቺቺኒያ ፕሬዝዳንት፣ የቺቺኒያ ወጣቶች እና ታዳጊዎች በማርሻል አርት እና በካራቴ ስፖርት ታንጸው ማደግ እንዳለባቸው እንደሚያምን በመግለጽ ሦስቱን ልጆቹን የማርሻል አርት ስፖርት እንዲሰለጥኑ ማድረጉን ለሕብረተሰቡ በመግለጽ የእርሱን አርአያ በመከተል የሪፐብሊኩ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ሥልጠና ማዕከላት እንዲልኩ ጥሪ አድርጎ የሪፐብሊኩን የማርሻል አርት ፌዴሬሽ በበላይነትም በመምራት ላይ ይገኛል፡፡
***
በ1996 ከመድኒ ሙሳየቭና ካዲሮቫ ጋር ትዳር የመሠረተው ፕሬዝዳንት ካዲሮቭ፣ ከዚህ ትዳሩ ዐሥራ ሁለት ልጆችን ያፈራ ሲኾን፣ ልጆቹ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተምረው እና ሰልጥነው ሀገራቸውን እያገለገሉ እንደኾነም ይነገራል፡፡
አንደኛዋን ልጁን የቺቺኒያ ባሕል ሚኒስትር ምክትል ሚኒስትር አድርጎ የሾመው ፕሬዝዳንት ራምዛን ካዲሮቭ፣ የቺቺኒያ ፕሬዝዳንት ኾኖ ለሁለተኛ ዙር የሥልጣን ዘመን ከተመረጠ በኋላም ሁለተኛ ሚስት አግብቶ ነበር፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት በ2021 ደግሞ በቺቺንያ ታዋቂ ዘፋኝ እና ዳንሰኛ የኾነችውን አሚናት አክማዶቫን ሦስተኛ ሚስት አድርጎ ማግባቱን፣ ሦስቱንም ሚስቶቹን በእኩል ዐይን እንደሚያይ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በመቅረብ ስለ ቅዱስ ጋብቻ ትምህርት ሲሰጥ ይታወቃል ፤ ሞገደኛው የቺቺኒያ ፕሬዝዳንት፡፡
በምዕራቡ ዓለም መንግሥታት እንዲሁም በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አስጠባቂ ተቋማት ክፉኛ የሚብጠለጠለው የቺቺኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት፣ ላለፉት 19 ዓመታት በቺቺኒያ ሪፐብሊክ ቁልፉን ሥልጣን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እና በፕሬዝዳንትነት ሀገሩን በመምራት ላይ ይገኛል፡፡
ራምዛን ካዲሮቭ የአባቱን ታሪክ የሚያወሳ ‹‹ባዝድ ኦን ላይት›› የተባለ ርዕስ ያለው መጽሐፍን በመላው ቺቺኒያ እና በሰሜን ካውከስ ክልላዊ አስተዳደር ግዛቶች በሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የታሪክ ትምህርት ክፍል አጋዥ መጽሐፍ ኾኖ እንዲያገለግል አድርጓል፡፡
በአባቱ አክማድ ዓብዱልካሚዶቪች ካዲሮቭ ሕይወት እና ሥራ ላይ በሚያወሳው መጽሐፍ ውስጥ ያሉ ታሪኮችን ከአጸደ ሕጻናት ጀምሮ ለሚማሩ የቺቺኒያ ተማሪዎች በየቀኑ ለሦስት እና አምስት ደቂቃዎች በመተረክ ሀገራቸው በነማን ያላሰለሰ ጥረትና ትግል ለዚህ መብቃቷን እንዲያውቁ፣ ይኽም ተማሪዎቹ የአክማድ ካዲሮቭን መንገድ ተከትለው እንዲድጉ ያግዛል ሲል ተናግሯል፡፡
በቺቺኒያ በአሁኑ ወቅት፣ ከሦስት መቶ በላይ አውራ ጎዳናዎች በአክማድ ካዲሮቭ ሥም የተሰየሙ ሲኾን፣ በዋና ከተማዋ እምብርት የሚገኘው አደባባይም በአባቱ ሥም የሚጠራ ነው፡፡ በግሮዝኒ ከተማ የሚገኘው ታላቁ መስጂድም በቺቺኒያው የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት አክማድ ካዲሮቭ ሥም የተሰየመ ነው፡፡
በ1990ዎቹ አጋማሽ ከሩሲያ ለመገንጠል ይካሔድ በነበረው የመጀመሪያው የቺቺኒያ ጦርነት ወቅት ዋናው የጦር መሪ በመኾን የተዋጉት እና በወቅቱም የሪፐብሊኩ ዋና ሙፍቲ የነበሩት አክማድ ካዲሮቭ በሩሲያውያን ዘንድ በጦረኝነታቸው ይታወቃሉ፡፡
በ1999 በተቀሰቀሰው በሁለተኛው የቺቺኒያ ጦርነት ወቅት የሞስኮ አቋምን በመደገፍ ከሌሎች የቺቺኒያ ተገንጣይ ቡድኖች ጋር ከፍተኛ ፍልሚያ በማካሔድ ከሞስኮ በሚያገኙት ዘርፈ ብዙ እገዛ አካባቢውን እርሳቸው የሚመሩት ጦር ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጠረ፡፡ በጁን 2000 ደግሞ የአካባቢው አስተዳደር ፕሬዝዳንት መኾናቸውን አወጁ፡፡
ለሁለት ዓመት የጊዜያዊ አስተዳደሪነት ሥልጣን ተቆጣጥረው የነበሩት ተቀዳሚ ሙፍቲ አክማድ ካዲሮቭ፣ በኦክቶበር 5 ቀን 2003 በይፋ የቺቺንያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ኾነው ሥልጣናቸውን በሩሲያ መንግሥት ሙሉ ድጋፍ ተቆናጠጡ፡፡
ከአንድ ዓመት በኋላ በሜይ 8 ቀን 2004 በቺቺንያ ዋና ከተማ ግሮዝኒ የድል በዓልን በማክበር ላይ እያሉ በአሸባሪዎች በተሰነዘረ የቦምብ ጥቃት እርሳቸው እና ረዳቶቻቸው ተገደሉ፡፡
የፕሬዝዳንቱ ልጅ እና የአሁኑ ፕሬዝዳንት ራምዛን ካዲሮቭ በወቅቱ ዕድሜው 28 ዓመት ነበረ ሲኾን፣ የአባቱ (የፕሬዝዳንቱ) ዋና የጥበቃ ቡድን መሪም ነበር፡፡
የፕሬዝዳንቱ መገድልን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሟቹ ፕሬዝዳንት ልጅ ራምዛን ካዲሮቭ ዕድሜው 30 ዓመት እስኪሞላው ድረስ በተጠባባቂ ፕሬዝዳንትነት ሀገሪቱን እንዲመራ ሰየሙት፡፡ የቺቺኒያ ራስ ገዝ ፓርላማም ይኽንኑ የፑቲን ውሣኔ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ፡፡
በ2007 በይፋ የቺቺኒያ ፕሬዝዳንትነት ሥልጣንን ሙሉ ለሙሉ የተቆናጠጠው ራምዛን ካዲሮቭ በሩሲያውያን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ አስገራሚ እና ሞገደኛ ያስባለውን ተግባር በመፈጸም ሥሙ ሲብጠለጠል ይሰማል፡፡
ፕሬዝዳንት ራምዛን ካዲሮቭ በ1990ዎቹ እና በ2000 ድረስ ባሉ ዐሥር ዓመታት በቺቺኒያ እና በመላው ሰሜን ካውከስ አካባቢዎች የነበረውን የእርስ በርስ ጦርነት ይመሩ የነበሩት የጦር አበጋዞች እና ይመሯቸው የነበሩ ተዋጊዎች ያካሔዱት ፍልሚያ እና የጦርነት ታሪክን በሚገባ ላጤነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴሌቭዥን ተመልካቾች እና በፊልም አፍቃሪያን ተወዳጅነትን ያገኘው ‹‹ጌም ኦፍ ትሮንስ›› ከተሰኘው ተከታታይ ፊልም ጋር የሚቀራረብ ታሪክን ማሳለፋችንን ይገነዘባል በማለት ይናገራል፡፡
በኦክቶበር 5 ቀን 1976 የተወለደው ሞገደኛው የቺቺኒያ ፕሬዝዳንት ራምዛን ካዲሮቭ በሩሲያ ጦር ኃይል ውስጥ የጀነራል ማዕረግ ያለው፣ ስለ ጦርነት እና ስለ ዘመናዊ የውጊያ ጥበብ በቂ ዕውቀት ያለው ተዋጊ እንደኾነ ይነገርለታል፡፡
በቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ክትትል፣ አባቱ በአሸባሪዎች የቦምብ ጥቃት ከተገደሉ ማግሥት ጀምሮ በቺቺኒያ ከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ተቆናጥጦ የሚገኘው ራምዛን ካዲሮቭ፣ በ2005 ኦገስት ወር ላይ በዋና ከተማዋ ግሮዝኒ የከተማዋ አንድ አካባቢ የነበሩ ጭርንቁስ መንደሮችን በማፈራረስ በስፍራው ላይ በመላው አውሮፓ በስፋቱ እና በትልቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው መስጂድን አስገንብቷል፡፡
ራምዛን ካዲሮቭ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለቺቺኒያ ተወላጆች ‹‹ሀገራችን በጥቂት ዓመታት ውስጥ የበለጸገች፣ ዘመናዊ እና ፍጹም ሰላማዊ ሀገር እንደምትሆን እርግጠኞች ሁኑ፡፡ ይኽ የሁላችንም ምኞት እውን ይኾን ዘንድ ቺቺኒያውያን ሁሉ በአንድነት ቁሙ›› የሚል አነቃቂ ንግግር ያደርግም ነበር፡፡
ሀገሪቱን መምራት እንደጀመረ በመላዋ የቺቺንያ ግዛት የሸሪዓ ሕግ በሥራ ላይ እንዲውል ያደረገው፣ በሀገሪቱ ቁማር እና ውርርድ የሚካሔድባቸው ቦታዎችን የዘጋውና በሪፐብሊኩ የአልኮል መጠጥ መጠጣትም ኾነ ማምረትን የከለከለው ራምዛን ካዲሮቭ ሕብረተሰቡ በስፖርት ሰውነቱን ያዳብር ዘንድ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን በማስፋፋት በርካታ አኩሪ ውጤቶችን ማስመዝገቡም ነው የሚነገርለት፡፡
ሞገደኛው የቺቺኒያ ፕሬዝዳንት ራምዛን ካዲሮቭ በዋና ከተማዋ ግሮዝኒን የሚያቋርጠው የሱናዛ ወንዝ ተፋሰስ አዋሳኝ በኾነ 120 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ የጫካ ቤተ መንግሥት አሰገንብቷል፡፡ ቤተ መንግሥቱ አንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል፣ ሙዚየም እና የተለያዩ የመዝናኛ ማዕከላትን የያዙ ሕንጻዎች ያሉት ሲኾን፣ አጠቃላይ የተገነባበት ወጪም 1.5 ሚሊዮን ሩብል ወይንም በ54 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መኾኑ ነው የሚነገረው፡፡
ፕሬዝዳንት ራምዛን ካዲሮቭ በመላዋ ቺቺንያ በግብረ ሰዶም (ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት) የሚጠረጠሩ ሰዎች ከተገኙ ማንኛውም ዜጋ በድንጋይ ወግሮ የመግደል መብት እንዳለው በይፋ ያወጀ፣ ይኽን መሰል ተልካሻ ማንነት ያለው የየትኛውም ሀገር ዜጋ በቺቺንያ ሲንቀሳቀስ ከተገኘም ተመሳሳይ ቅጣት እንደሚጠብቀው በማሳወቁ፣ በአውሮፓ ሕብረት እንዲሁም በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ከፍተኛ ውግዘት እና ተቃውሞ የተሰነዘረበት ሰው ነው፡፡
የ46 ዓመቱ የቺቺኒያ ፕሬዝዳንት በዓለም አቀፍ ደረጃ የመገናኛ ብዙኃን ሚናን አስመልክቶ አስተያዩን ሲሰጥም ‹‹ሚዲያው የሁለቱ የሳጥናኤል ጉዳይ አስፈጻሚዎች ማለትም የእንግሊዝ እና የአሜሪካ የእርኩሰት መገልገያ ነው፡፡ ሊቢያን፣ ሶርያን፣ የመንን እና ኢራቅን ካፈራረሱ ጦረኞች ይልቅ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ለፈጸሙት ጥፋት ጂሃድ ሊታወጅባቸው እና ሊቀጡ ይገባል›› የሚል አቋም እንዳለው ሞገደኛው የቺቺኒያ ፕሬዝዳንት ራምዛን ካዲሮቭ በብዛት ይናገራል፡፡ ‹‹የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙኀን ሰዎች እርስ በርስ እንዲተላለቁ የሚጋብዙ ዘገባዎችን ይሠራሉ›› የሚለው ካዲሮቭ፣ ‹‹ሰዎች በዘገባዎቹ የተነሳ ጦር ተማዘው ሲተላለቁም ያለ ሀፍረት ዜና ይሠራሉ፡፡ ከእልቂቱ በኋላ እጃቸው በሰው ልጆች ደም የተጨማለቀ መሪዎችና ፖለቲከኞች ሲጨባባጡና ሲሳሳሙም እንዲሁ ለዘገባ ይጣደፋሉ፡፡ ይኽን መሰል ሙያዊ ሥነ ምግባር ያለው ጋዜጠኝነት አውዳሚ እና አደገኛ ነው›› ሲል ራሱ በሚያዘጋጀው የቴሌቭዥን ሪያሊቲ ሾው ላይ ጭምር በመናገር ዓለምን ‹‹እንመራለን›› የሚሉትን የአውሮፓ እና የአሜሪካ ብዙኀን መገናኛ ተቋማት እርባና ቢስነታቸውን በግላጭ ተናግሯል፡፡
