
ዓይናለም ደበበ
እንደዛሬው የዘመናት ጠላቶቻችን በፈተሉት የሴራ ፖለቲካ ተተብትበን መላቅጡ እጠፋበት አረንቋ ውስጥ ከመዘፈቃችን በፊት ሀገራችን ኢትዮጵያ በእርግጥም በዓለም መንግሥታት ዘንድ ታፍራና ተከብራ የኖረች ሀያል ሀገር ነበረች። መሪዎቿም ከቅርብ ግዜ ወዲህ ባሉት ዘመናት እንደተመለከትናቸው መሪዎች በገቡበትና በወጡበት ሁሉ ለምፅዋት እጃቸውን የሚዘረጉ ምንዱባን ከመሆናቸው በፊት በዓለም ላይ ተከስተው ዓለምን አንቀጥቅጠው ለገዙ ታላላቅ መሪዎች ዓርዓያ ለመሆን የቻሉ ባለፀጋ መሪዎች ነበሩ። ምንም እንኳ አንዳንዶቹ ለመቀበል ቢያዳግታቸውም ዲዮዶር የተባለው ጥንታዊ የሮማ ፀሀፊ እንደፃፈው:- ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ከታችኛው የአባይ ተፋሰስ ሀገራት የላቀ ስልጣኔና ገናና ስም ነበራት። ከዚህም የተነሳ ግብፅን አስራ ስምንት የኢትዮጵያ ነገሥታት ገዝተዋል። ከነዚህ ግብፅን ከገዙ የኢትዮጵያ ነገሥታት መካከል ከክርስቶስ ልደት በፊት በ 751 ዓ.ዓ አካባቢ የነገሠው ንጉሥ ፒያንኪ ፪ኛ አንዱ ሆኖ በታሪክ መዝገብ ላይ ተጠቅሶ ይገኛል።
በሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ በዘመነ መሳፍንት ተፈጥሮ እንደነበረው የተበታተነ አወቃቀርና ደካማ አስተዳደር በጥንት ግዜ ግብፃውያን በአንድ ፈርኦን ለመመራት ያልቻሉበት ግዜ ነበር። በዚያን ግዜ ግብፆች በየአካባቢውና በየአውራጃው አንደኛው መስፍን በአንደኛው ላይ እየተነሳ እርስ በእርሳቸው ይዋጉ ነበር። ከዚህ የእርስ በእርስ ውጊያ በኋላም ተፍነክታ (ተውኔክህት) የተባለው መስፍን አይሎ ብዙሃኑን መሳፍንት አንበርክኮ ለአጭር ግዜም ቢሆን ፈርኦን መሆኑን አወጆ መንበሩ ላይ ተቀምጦ ነበር። እያደር ግን የተፍነክታን ፈርኦንነት ለመቀበል ያዳገታቸው ግብፃውያን መሳፍንት ሕዝባቸውን እየቀሰቀሱ ጦራቸውን እያደራጁ ለውጊያ መነሳሳት ጀመሩ። እኚህ መሳፍንቶች የአባት አያቶቻቸውን ግፍና በደል ዘንግተው በግዜው የራሱን ሀገረ መንግሥት በተረጋጋ ሁኔታ እየመራ ከነበረው የኢትዮጵያ ንጉሥ ፒያንኪ ፪ኛ የጦር እገዛ እንዲደረግላቸው ጥያቄ ማቅረብም ጀመሩ። ታድያ ፒያንኪም ከግብፃውያን መሳፍንት ‘ፌዝ ያዘለ አስገራሚ’ ጥያቄ ላይ ተነስቶ ግብፅን የመግዛት ምኞት አደረበት። ፑአርማና ኡአሜሪስኪን በተባሉ ጠንካራ የጦር አለቆቹ ታግዞም ፒያንኪ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ምኞቱን እውን አድርጎ የአባት አያቶቹን በደል ሽሮ ግብፅን ያዘ።
ከዚህ ቀደም ብሎ የነበሩ የግብፅ ፈርኦኖች ኢትዮጵያን ወረው ሲያበቁ ‘ኢትዮጵያውያንን አስገበርን!’ በማለት ፈንታ ‘ምስኪኖቹን አስገበርን!’ ይሉ ስለነበር ንጉሥ ፒያንኪ ከልቡ ላይ እንደ እቶን የሚንቀለቀል ቁጭት ነበረበት። ቢሆንም ግን የበቀል እርምጃን በመውሰድ ግብፃውያኑን ከመቅጣት ይልቅ ማስጠንቀቅን ይመርጥ ነበር። “እናንተ በሞት የምትኖሩ ደካሞች ምስኪኖች፣ መዝጊያችሁን ሳትከፍቱ ትንሽ ግዜ ያለፈ እንደሆነ በማደርገው እልቂት በራሳችሁ ፈራጆች ትሆናላችሁ … ለሕይወት የከፈትሁላችሁን መዝጊያ አትዝጉ … ሞትን አትምረጡ። ሕይወትንም አትናቁ” እያለም ያሳስብም ያስጠነቅቅም ነበር።
በሰላም ለሚማረክ ጠላት ንጉሥ ፒያንኪ ሩህሩህ ነበርና አንዳችም ነፍስ በከንቱ ማጥፋትን ፈፅሞ አይመርጥም ነበር። የሚወጋውን ከተማም ሆነ አካባቢ ሳይመክርና ሳያስጠነቅቅ ውጊያ አይጀመርም ነበር። ለጦር አለቆቹም ከዚህ አሰራር ውጪ አንዳች ነገር እንዳይፈፀም ጥብቅ ትዕዛዝ ያስተላልፍ ነበር። ይህ ሁኔታ ንጉሥ ፒያንኪ ዓላማውን ለማሳካት በሚያደርገው ትንቅንቅ የቱን ያህል ሰብዓዊ ለመሆን ይጥር እንደነበረ የሚያስረዳ ነው። ግብፃውያኑም ቢሆኑ በራቸውን ከፍተው ሀብትና ንብረታቸውን ለግርማዊነቱ በማቅረብ ከፊቱ ተደፍተው “…የሁለቱ ዓለሞች (የኢትዮጵያና የግብፅ) ጌታ እንደመሆንህ እንሆ ገንዘቦችህ ናቸው ። ዓለምን የምትገዛ ጌታ ነህ።” እያሉ ይቀበሉት ነበር። እርሱም እንደ ግብፃውያኑ ልማድ ሁሉ ከቤተ መቅደሳቸው እየሄደ ለመሥዋዕት የሚያደርጉትን ኮርማ በሬና ዳክዬ እንዲሁም ሌላም የሚያስፈልጋቸውን ስጦታ ሁሉ ይሰጣቸው ነበር። ፒያንኪ የግብፃውያኑን ባህልና አምልኮ በማክበሩም በመንግሥቱ የተቃና አስተዳደርን ለመመስረት በቅቷል።
ንጉሥ ፒያንኪ በዚህ ሁኔታ ሰላም ለሚሹት ፍቅር እየሰጠ ጠብ ለሚሹት ደግሞ ነበልባል ክንዱን እያቀመሰ አያሌ የግብፅ ከተሞችን ተቆጣጥሯል። በአመራር ብስለቱ ከርሱ በኋላ በዓለም ላይ ለተከሰቱ ሀያል መሪዎች ጭምር ዓርዓያ ለመሆን በቅቷል ። ከእውቁ የግሪክ ፈላስፋ አርስጣጢለስ (አሪስቶትል) ዘንድ የተማረው ታላቁ እስክንድር እንኳ ከአራት መቶ ሃምሳ ዓመት በኋላ የፒያንኪን የጦር አመራር ጥበብ በመከተል በዓለም ላይ ታላቅ ገድልን ለመፈፀም በቅቷል። ይህንን የፒያንኪን የጦር አመራር ጥበብ የተከተለው ታላቁ እስክንድር የዓለምን አንድ ሦስተኛ ያህል በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ችሏል።
ያም ሆኖ ግን ፒያንኪ የግብፅን ከተሞች ጨርሶ አልያዘም ነበር። ምንም እንኳ አስፈሪ የነበረው ንጉሥ ነምሩድ ለፒያንኪ ቢገብርም በሰሜን ግብፅ የሚገኘውና የግብፅ ፈርኦን ነኝ! ብሎ የተቀመጠው ተፍነክታ ገና አልገባም ነበር። ታላቋ የፈርኦኖች ከተማ መምፊስም አልተያዘችም ነበር። የመምፊስ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ከተማዋ ጦሩን ያስጠጋውን ፒያንኪን ንቀው በራቸውን ለመክፈት ባለመቻላቸው ብዙ ሰው ካለቀ በኋላ ፒያንኪ ከተማዋን ለመቆጣጠር ቻለ። አብዛኛው የግብፅ መሳፍንትና መኳንንት ለፒያንኪ መገበራቸውን እና አያሌ ከተሞችና አውራጃዎች በርሱ መያዛቸውን ባለበት የግብፅ ሰሜናዊ ስፍራ ሆኖ የሰማው ተፍነክታም ከዚያ በኋላ ፒያንኪን ለመከላከል የማይቻል መሆኑን ተረዳ። በመሆኑም ምህረት እንዲደረግለት መልዕክተኛ ላከ።
“…በነበልባል ፊት መቆም አልችልም። በግለትህ ተሸነፍሁ … ወደ ባሕር ደሴት ሸሸሁ … በእውነቱ ምስኪን ነኝ። በወንጀሌ ጥፋት ውስጥ አትጣሉኝ… ፍርሃትን በልቤ አሳደርህ፣ ሽብርም በአካሌ ውስጥ ተነዛ። በመጠጥ ቤት ውስጥ አልቆምም። በገናዬንም ለጨዋታ አያመጡልኝም። በራበኝ ግዜ ከደረቅ ዳቦ በቀር አልበላም። ሲጠማኝም የምጠጣው ውሃ ብቻ ነው። ስምህን ከሰማሁበት ቀን ዠምሮ ፍርሃት በአጥንቶቼ ውስጥ ዘለቁ። አእምሮዬ ተቃጥሏል። ልብሶቼ ተበጣጥሰዋል… ሸሽቼ ተደብቄያለሁ…” በማለትም ተማፀነ።
ጠላትን ማንበርከክ የሚያስደስት ተግባር ቢሆንም እንኳ የግብፅ ፈርኦን ነኝ ያለው ንጉሥ እንዲህ ባለ የፍርሃት ቆፈን ተሸብቦ በመገኘቱ ግን ፒያንኪን አላስደሰተውም ነበር። ይልቁንም አሳዝኖት ነበር። ቢሆንም ግን ‘ጎልማሳ በሚስቱ ንጉሥ በመንግሥቱ’ ሆኖበት ነገሩ ፒያንኪ ርህራሄውን ገታ አድርጎ ከዚያ በኋላ ተፍነክታ ክህደት ላለመፈፀሙ ማስተማመኛ እንዲሆን በትልቁ ሊቀ ካህን በፔታምኔስቶ መሀላ እንዲፈፅምና በጦር አለቃው በፑአርማን አማካኝነት የጦር መሳሪያውን እንዲያስረክብ አደረገ። ተፍነክታም ከፒያንኪ ለተላኩት መልዕክተኞቹ ወርቁንም ብሩንም፣ ልብሱንም ጌጡንም ሁሉ ባንድነት ጨምሮ አስረከባቸው። “የንጉሡን ትዕዛዝ አልጥስም። ከቃሉም እልፍ አልልም እሱም ሳይፈቅድ ማናቸውንም ሹም አልጎዳም። እንደ ንጉሡ ቃልና ትዕዛዝ እፈፅማለሁ” በማለትም ተፍነክታ በቤተ መቅደስ መሀላ ፈፀመ። ከዚያ በኋላ በግብፅ ምድር ላይ ፒያንኪን ለመቃወም የተነሳ መስፍን አልነበረም። ኢትዮጵያዊው ፒያንኪ ፪ኛ ፈርኦንን አሸንፎ ግብፅን በማስገበሩም ስሙ በዓለም ላይ ናኘ። ፒያንኪ ግብፅን ከማስገበሩ በፊት ሃያ አንድ ዓመት እንዲሁም ግብፅን ካስገበረ በኋላ አስር ዓመት በድምሩ ለሰላሳ አንድ ዓመት ያህል ገዝቶም ሞተ።
ምንጭ:- ኑብያ የኢትዮጵያ ታሪክ (ናፓታ – መርዌ) ከተክለጻድቅ መኩሪያ በቸር ያቆየን