ሕወሃት በትግራይ ክልል በድጋሚ ሊቀሰቀስ የሚችለውን አስከፊ ጦርነት ለማስቆም ዲፕሎማቶችና አጋር አገራት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቀረበ።
ድርጅቱ ለዓለማቀፉ ኅብረተሰብ በጽሁፍ ባስተላለፈው መልዕክት፣ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የተፈራረሙትን ሁለቱን ወገኖች ወደ ጠረጴዛ ለማምጣት ንቁ ሚና እንዲጫወቱ የጠየቀ ሲሆን፣ እራሱም ቢሆን ቀውሱን ለመፍታት በሚያስችል ፖለቲካዊ ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መኾኑን ገልጧል።
ሕወሃት አክሎም፣ ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚለው ስጋት መላ ምት ሳይሆን እውን ለመኾን የተቃረበና ከተከሰተም ቀጠናዊ የመሆን እድሉ ከፍተኛ መሆኑን አስጠንቅቋል።
የመከላከያ ሠራዊት የትግራይን ድንበሮች መክበቡ በሕዝቡ ዘንድ ከባድ ጭንቀት መፍጠሩን የገለጸው ሕወሃት፣ በምዕራብ ትግራይ ያለው “ሕገወጥ” አስተዳደርና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ የፌደራል መንግሥቱ አጋሮች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሠቶችን መፈጸም መቀጠላቸውንና አዳዲስ መፈናቀሎችም እያጋጠሙ መሆኑን ከስሷል።
