አይኤምኤፍ እና ኢትዮጵያ የ468 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ የሚያስገኘውን የባለሞያዎች ደረጃ ስምምነት ላይ ደረሱ
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያጋጠማት ያለውን ተለዋዋጭና አሳሳቢ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ሁኔታ ለመቋቋም እና የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ስትል፣ የጀመረችውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አጠናክራ እንድትቀጥል በጥብቅ አሳሰበ።
ይህ ማሳሰቢያ የወጣው በኢትዮጵያ መንግሥትና በአይ ኤም ኤፍ የባለሙያዎች ቡድን መካከል በተደረገው የ4 ዓመቱ የተራዘመ የብድር አቅርቦት ፕሮግራም አምስተኛ ግምገማ ላይ ስምምነት መደረሱን ተከትሎ ነው።
ይህ በቅርቡ በድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው ስምምነት፣ ኢትዮጵያ የ468 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ እንድታገኝ የሚያስችላት ሲሆን፣ ይህም የሀገሪቱን አጠቃላይ የብድር አቅርቦት ወደ 2.65 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ያደርገዋል።
