በቀን 20 ብር በመስጠት የነገ አገር ተረካቢ ትውልድን እናግዝ
በአገራችን ግብረ ሰናይ ስራዎች ውስጥ ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ አገር በቀል ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር፣ የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ።
በወይዘሮ ሙዳይ ምትኩ አማካኝነት በ1992 ዓ.ም የተመሰረተው ይህ ድርጅት፣ ላለፉት 25 ዓመታት ህፃናትን፣ ሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን ከጎዳና ተዳዳሪነትና ከልመና በማውጣት ረገድ አርዓያ የሚሆን ተግባር ሲያከናውን ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት ማህበሩ ከ1,250 በላይ እናቶችንና ህፃናትን በስሩ አቅፎ የጤና፣ የምግብ፣ የአልባሳትና የመጠለያ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ድርጅቱ ካሉት ልዩ መገለጫዎች መካከል አንዱ ለትምህርት የሚሰጠው ትኩረት ነው። በማዕከሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከነርሰሪ እስከ ኬጂ 3 ድረስ ነፃ ትምህርት የሚሰጥ ሲሆን፣ ከዚያ በላይ ያሉ ተማሪዎችን ደግሞ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ሙሉ ወጪያቸውን በመሸፈን ለነገዋ ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል።
ሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር ላለፉት ሩብ ክፍለ ዘመናት ምንም ዓይነት ቋሚ የውጭ ፈንድ ሳይኖረው፣ በሀገር ውስጥ በጎ አድራጊዎች ድጋፍና ተረጂዎቹ በሚያመርቷቸው የሸክላ፣ የሽመናና የስፌት ውጤቶች ሽያጭ ራሱን እያስተዳደረ የሚገኝ ድርጅት ነው።
እናቶች በሙያ ሰልጥነው ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ረገድም ውጤታማ ስራዎችን አከናውኗል።
ማህበሩ ትልቅ ስኬቶችን ቢያስመዘግብም፣ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የቤት ኪራይ ተግዳሮት ከፊቱ ተደቅኗል።
በየወሩ 270 ሺህ ብር ለኪራይ የሚያወጣ ሲሆን፣ በተከራየበት ቦታ ላይ በየጊዜው የሚደርስበት የመልቀቅ ጥያቄ በስሩ ያሉ ወገኖችን ለከፍተኛ መበተን ስጋት ዳርጓቸዋል።
ይህንን ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአያት በሻሌ አካባቢ የተረከበው 2 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ መጠለያ፣ ትምህርት ቤትና የጤና ማዕከል ለመገንባት በዝግጅት ላይ ይገኛል።
“ግንባታውን ለማጠናቀቅ 250 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል። ይህ ሲጠናቀቅ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል” ሲሉ የማህበሩ መስራች ገልጸዋል።
ማህበሩ በቀን 250 ሺህ ብር ለምግብ ወጪ እያደረገ የሚገኝ በመሆኑ፣ በጎ አድራጊ ኢትዮጵያውያን “በቀን 20 ብር በመስጠት” የነገ አገር ተረካቢ ህፃናትን ስፖንሰር እንዲያደርጉና በግንባታው ሂደትም አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ ቀርቧል።
ለበለጠ መረጃና ድጋፍ ለማድረግ፦
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፦ 1000743960697
ስልክ፦ 0902526252 / 0937989898 / 0911718205
አድራሻ፦ ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፊትለፊት
