የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደዉ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከአፍሪካ ተቋማት በስተቀር የውጭ ታዛቢዎች ፈቃድ አለማግኘታቸውን ገለጹ።
ምርጫ ቦርድ የሰባተኛውን አገራዊ ምርጫ አጠቃላይ የቅድመ ምርጫ ሥራዎችንና የድምፅ መስጫ ቀን አስመልክቶ፣ ማክሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ይህ የተገለጸው።
መግለጫውን የሰጡት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ የአፍሪካ ኅብረትና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) በሰባተኛው እገራዊ ምርጫ ለመታዘብ እንደሚመጡ የሚገልጽ ዝርዝርና ሙሉ ሪፖርት ቦርዱ ደርሶታል ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችን በሚመለከት ፈቃድ የሚጠየቀውም ሆነ የሚሰጠው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሆኑንና ሁለቱ የአፍሪካ ተቋማት ለመታዘብ እንደሚመጡ የተነገራቸውና ሪፖርታቸው የተላከላቸውም በውጭጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እንደሆነ፣ ቦርዱም ለተቋማቱ የታዛቢነት ባጅ ለመስጠት ዝግጅት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “እነዚህ ትልልቅ ተቋማት ከሚቀጥሎት ሁለት ቀናት በኋላ ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ!›› ብለዋል፡፡
ከሁለቱ ተቋማት ውጪ ሌሎች ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ፈቃድ ስለመጠየቃቸውም ሆነ ስለመፈቀዱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ሆኖም የአውሮፓ ኅብረት በታዛቢነት እንደማይሳተፍ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከልማት አጋሮች ለምርጫ ቦርድ የተደረገን የገንዘብ ድጋፍ በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡት የቦርዱ ሰብሳቢዋ ወ/ሮ ሜላትወርቅ፣ በተባበሩት መንግሥታት (ተመድ) አማካይነት አየርላንድ፣ ስፔን፥ ኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ እንግሊዝና ጃፓን የተወሰነ የገንዘብ ድጋፍ እንዳደረጉላቸውና በዚህም መሠረት ሰባት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
ከአውሮፓ ኅብረትም የምርጫ ማስፈጸም ሥራ በሚያከናውን ኤከስ በተሰኘ ተቋም አማካይነት ለቦርዱ ድጋፍ እንደሚደረግ፣ ድጋፉ ግን ስምምነት ላይ በተደረሰባቸው የሥራ ዕቅዶችን መሠረት በማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል::
ሆኖም በአውሮፓ ኅብረት በኩል የተደረገውን የድጋፍ ገንዘብ ለማወቅ ምርጫው ሲጠናቀቅ እንደሚታወቅ አስረድተዋል።
በዘንድሮ ምርጫ 55 የአገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለመታዘብ ፈቃድ ጠይቀው ቦርዱ እንደሰጣቸው፣ ድርጅቶቹም ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ የራሳቸውን ምልከታ አድርገው መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች በሪፖርት ማቅረባቸውን ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይደርስ ክትትል የሚያደርገው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባደረገው ክትትል ላይ ያቀረበውን ሪፖርት በመውሰድ፣ ክፍተት የታዩባቸው አካባቢዎች የትኞቹ እንደሆኑ በመለየት ማስተካከል እንዲቻል ቦርዱ በግብዓትነት እየተጠቀመበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሪፓርተር
