ስለሺ መንገሻ – ከ1934 እስከ 2018 ዓ.ም
ሠሎሞን ለማ ገመቹ.
ግዮን መጽሔ :- ይህን የጓድ ስለሺ መንገሻን ማንነት የሚመለከት ጽሑፍ ሳዘጋጅ ‹‹አንቱ›› ከማለት ይልቅ ‹‹አንተ›› ማለቱን መርጬአለሁ፡፡ ይህን ምርጫ ያደረኩትም ስለ እሱ ማንነት፣ ባሕሪይና ተግባር… የማደርገውን ገለጻ ‹‹እሳቸው…›› እያልኩና ከዘልማዳዊ የአክብሮት ቃል ጋር እየተሟገትኩ ወደፊት ለመቀጠል መሞከሬ፤ ብዕሬን ያነሳሁበትን ዋንኛ ጉዳይ አያቀናልኝም፣ አያሰምርልኝም፣ ስሜቴንም ፈታ አያደርግልኝም ብዬ በመገመቴ ነው፡፡
ሌላው ስለ ስለሺ ያቀረብኩትን ጽሑፍ ‹አንተ›› እያልኩ ማስኬዱን የፈለኩበት ምክንያት፤ ግለሰቡ የነበረውን ማኅበረሰባዊ የክብር ሥፍራ በፍፁም በመዘንጋትም ይሁን ባለማስተዋል አይደለም፡፡ ይልቁንም አንተ ብዬ ስለ ጓድ ስለሺ መንገሻ በዚህ መጽሔት የሠፈረውንና ምግባረ-መልካምነቱን የሚያመለክተውን ጽሑፍ የቀመርኩት፤ ለባለጉዳዩ ያለኝ ቀረቤታ ለራሴ ብቻ ሳይሆን ለአንባቢውም ሩቅ ሆኖ እንዳይሰማው በሚል ደግ እሳቤ ነው፡፡ አንተ… እያሉ ግለሰቡን የሚመለከተውን ጽሑፍ መዘወሩም፤ ለአንባቢውም ይሁን ለጸሐፊው የማንበብንም ይሁን የመፃፍን ለቀቅ፣ ፈታ ያለ ነፃነት የሚያጎናጽፍ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን… ለግለሰቡ ካለኝ የበረታ አክብሮትና ወንድማዊ ስሜት አንጻር፤ ይህን ጽሑፍ በመጀመሪያ ደረጃ ነጋሪ መደብ አንተ እያልኩ መቀጠሉን መርጬአለሁ፡፡
በእኔ መረዳትና ግንዛቤ፤ ጓድ ስለሺ መንገሻ ለብዙዎች የወንድምነትን፣ የአባትነትን ያህል ቀርቦ በማኅበረሰብ ውስጥ የኖረ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ፤ እሱን የሚመለከተውን ጉዳይ ‹‹እሳቸው…›› እያሉ ማስኬዱ፤ የቅርብን፣ የራስን ሰው… ከነበረው የበዛ ትኅትና፣ የሃገር አፍቃሪነት፣ የወገን ወዳድነት ባሕሪ መሰጠቱ አኳያ ሲመዘን ወይም ሲለካ፤ ስለ እሱ በአንቱታ ደረጃ የሚቀርበው ወደ መሠረታዊ ማንነቱ እውነት ያጋደለ ጽሑፍ፤ የመንገር፣ የማስረዳት፣ የማሳወቅ፣ የመመስከር ጉልበቱን፣ ውበትና ጣዕሙን ያጣል የሚል ግንዛቤ በመውሰዴም፤ እነሆ ስለ ምግባረ-መልካሙ ኢትዮጵያዊ የሚያወሳው ጽሑፌ አንተ… እያለ በመተረኩ ሂደት ቀጥሏል፡፡
ጓድ ስለሺ መንገሻ ከዛሬ ሰማንያ አራት ዓመታት በፊት ነበር የተወለደው፡፡ በቀድሞ አርሲ ክፍለ ሃገር፣ ሶዴ በሚባል ወረዳ፣ ‹‹ሃሰን ዳቦ›› ተብላ በምትጠራ ቀበሌ ውስጥ በምትገኝ አንዲት የገጠር መንደር፡፡ እና እሱ በወርሃ ኅዳር ሦስተኛ ቀን 1934 ዓ.ም ወደዚህ ዓለም መጣ፡፡ የወላጅ አባቱ የባሻ መንገሻ መቼአምኜህ የአብራክና የእናቱ የወይዘሮ ደማ አለሚ የማኅፀን ፍሬ ሆኖ፡፡ ዳኸ፡፡ አደገ፡፡ ተመነደገ፡፡ በአባት እናቱ እንክብካቤ በጨዋነት ተይዞ እንደ ዘመኑ የዕድሜ ዕኩዮቹ የቤተ-ክህነቱን ትምህርት እየተከታተለ… የታዳጊነት ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ከቤተ-ክህነት ትምህርቱም በመቀጠል ዘመናዊ ዕውቀትን ለመቅሰም ይችል ዘንድ ከአርሲ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አመራ፡፡ መደበኛ ትምህርቱን በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ሲከታተል ከቆየም በኋላ በአፍለኛ የወጣትነት ዕድሜው እናት ሃገር ኢትዮጵያን በውትድርና ሙያ የማገልገል ፍላጎቱ የሕይወት ምህዋሩ ኮንፓስ… በክብር ዘበኛ ባልደረብነት የውትድርናን ኑሮ ለቀጥል ወደሚችልበት አቅጣጫ መራው፡፡
በወርሃ መስከረም 1955 ዓ.ም የኢትዮጵያ አንድነት ዘመን ሠራዊት ባልደረባ ከሆነ ወዲህ፤ እስከ የካቲት ወር 1966 ዓ.ም ድረስ፤ በኦጋዴን፣ በጅጅጋ፣ በቀብሪ-ደሐርና በሌሎችም ግንባሮች ግዳጆቹን ሲወጣ፣ ከእሱ የሚጠበቀውን የውትድርና በተለይም በወታደራዊ ስፖርት ዘርፍ፤ በመረብ-ኳስና በቅርጫት ኳስ… ውድድሮች በተጫዋችነትና በአሰልጣኝነት ተሳትፎ ሲያደርግ ቆየ፡፡
በየካቲት ወር 1966 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት መቀስቀስ ማግስት፤ ከየጦር ክፍሉ በውክልና ተጠርተውና ተመርጠው… የጦር ኃይሎች፣ የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባበሪ ኮሚቴ (ደርግን) ለመመስረት ከተሰባሰቡት አብዮታዊያን መኮንንኖች፣ የበታች ሹሞችና ወታደሮች መካከል፤ የነበረበትን የክብር ዘበኛ ጦር በመወከል አንደኛው ሆኖ ተገኘ፡፡ በሂደትም ባሳየው የነቃ ተሳትፎ ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም የተመሰረተው የአስተባባሪው ኮሚቴ ወይም የደርግ ዋንኛ አባል ሆኖ በድምፅ ብልጫ ተመረጠ፡፡ ዕድል፣ ዕጣ-ፈንታውና ኮከቡ በመኖር መንገዱ ላይ ቆማ የሚጓዝበትን መንገድ የተለመችለት በመሆኑ፤ ስለሺ መንገሻ እንደ ሌሎቹ 107 የደርግ አባላት ሁሉ፤ ሃገሩን፣ ወገኑን፣ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ብሎም አብዮታዊ ኃላፊነትን የመወጣት አደራን መቀበልና ከእሱ የሚጠበቀውን የዜግነት ድርሻ የመወጣቱን ግዳጅ … ሳይወድ ብግድ ተቀበለ፡፡
በ1968 ዓ.ም ወደ ሃገረ ሃንጋሪ ተጉዘው የፖለቲካ ንቃተ-ሕሊና ማዳበሪያ ትምህርት ከተከታተሉትና በሰርተፍኬትም ተመርቀው ወደ እናት ሃገር ኢትዮጵያ ከተመለሱት ‹‹አብዮታዊያን ጓዶች›› መካከል አንደኛው የሆነው የመቶ አለቃ ስለሺ መንገሻ፤ በቅድሚያ ለአንድ ዓመት ያህል ማለትም ከ1969 እስከ 1970 ዓ.ም ባለው ጊዜ የአርሲ ክፍለ ሃገር የደርግ ዋንኛ ተጠሪ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በመቀጠልም ከ1970 እስከ 1971 በነበሩት ጊዜያት በደርግ ዋና ተጠሪነቱ በትግራይ ክፍለ ሃገር ውስጥ ሠርቷል፡፡
ከፍ ሲል ከተገለጹት አገልግሎቶቹና የመንግሥታዊም ይሁን የድርጅታዊ የኃላፊነት ሥራዎቹ በተጨማሪ፤ ጓድ ስለሺ መንገሻ ከ1971 እስከ 1980 ዓ.ም በነበሩት ጊዜያት ውስጥ የአርሲ ክፍለ ሃገር አስተዳዳሪ፣ የክፍለ ሃገሩ የኢሠፓአኮ 1ኛ ጸሐፊና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፤ እንዲሁም የአርሲ ክፍለ ሃገር ዋና አስተዳዳሪና በኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የክፍለ ሃገሩ አንደኛ ፀሐፊ ሆኖ ሠርቷል፡፡ ከ1980 እስከ 1983 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ወራት አጋማሽ በነበሩት ጊዜያትም፤ ጓድ የመቶ አለቃ ስለሺ መንገሻ በትግራይ ራስ ገዝ አስተዳደር የኢሠፓ አንደኛ ጸሐፊ ሆኖም እያገለገለ ቆይቷል፡፡
በወህኒ በነበረበት ዓመታት የሕግ ሙያን አጥንቶ በዲፕሎም ለመመረቅ የበቃው፣ ከወህኒ ከወጣም በኋላ በተለያዩ የግል ተቋማት በአስተዳደርና በምርት ክፍል ኃላፊነት የሠራው፣ ከወህኒ የተፈቱ የደርግና የኢሠፓ አባላት እንዲሁም በወታደራዊው መንግሥት ዘመን በተለያዩ የሃገርና የሕዝብ አስተዳደር ቦታ… ሲያገለግሉ የነበሩ ዜጎች መስከረም 23 ቀን 2003 ዓ.ም ያቋቋሙት የሰው ለሰው መረዳጃ ዕድር መሥራችና ሊቀመንበር ሆኖ ያገለገለው ባለ መልካም ምግባሩ ስለሺ መንገሻ፤ አንገቱን እንዳቀረቀረ ከጨዋነቱ ጋር ከዚህ ዓለም የተለየው፤ ታኅሣሥ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ነበር፡፡ የቀብሩ ሥነ-ሥርዓትም የተፈፀመው በአዲስ አበባ ከተማ በሳሊተ-ምህረት ክርስቶስ ሰምራ ቤተክርስቲያን ታኅሣሥ 19 ቀን በጣም ጥቂት ወዳጆቹና በአጋጣሚ ማረፉን የሰሙ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ነው፡፡
ስለሺ መንገሻ ከ1969 እስከ 1983 ዓ.ም መጀመሪያ ጊዜ ድረስ ለእናት ሃገር ኢትዮጵያና ለወገኖቹ መሻሻልና መለወጥ ሲል በቅንነት ባበረከተው አስተዋጽዖ፤ እንዲሁም ሕዝብን አወያይቶ፣ በአክብሮት መንፈስ አግባብቶና አሳምኖ፣ ብሎም አስተባብሮ ባከናወናቸው የሃገራዊ ኃላፊነቶቹ ወሳኝ ተግባራት፤ በተለይም የሠይድ ባሬ ወራሪ ሠራዊት የኢትዮጵያን ግዛት በእጁ ለማድረግ ሰፊና ጥልቅ ወረራ በፈፀመበት ጊዜ፤ የእናት ሃገር ጥሪውን ሰምቶ አደባባይ የወጣውን፣ ለመዝመት! ለመሰለፍና ለመሰየፍ የተዘጋጀውን ኢትዮጵያዊ የሃገሩ ተከላካይና ጠባቂ ኃይል ሆኖ በወታደራዊ አቋም እንዲደራጅ በማድረግ፣ በትግራይ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጎሣና በቋንቋ… ለመከፋፈል የተነሱትን አስገንጣይ ገንጣይ ወንበዴዎች ለመፋለም፤ የትግራይ ክፍለ ሃገር ወጣቶች በታሪክ ውስጥ አንፀባራቂ የኢትዮጵያ አንድነት መከታነት ስም በነበረው የዘንዶ ተዋጊ ሠራዊት አባል እንዲሆኑ በማድረግ… እና በሌሎችም መሰል ተግባራት በተወጣው ይህ ቀረሽ የማይባል የኢትዮጵያዊነቱ ሚና፡- የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ የክብር ኮከብ አንደኛ ደረጃ ሜዳይ፣ የየካቲት አብዮት 1ኛ ደረጃ የክብር ኒሻን ለመሸለም የበቃ ነው፡፡
በጥቅሉ ስለሺ መንገሻ ከ1968 ዓ.ም እስከ 1983 ዓ.ም በነበሩት ዓመታት፤ በሃገረ ኢትዮጵያ በቀድሞ አርሲ እና ትግራይ ክፍለ ሃገራት በደንብ ይታወቃል፡፡ በተለይ ሕዝቡ እሱን የሚያውቀው በተግባቦቱ፣ በዝምታው፣ በታታሪ ሠራተኛነቱ፣ በይበልጥም ሰዎችን በዕኩልነት፣ በወንድማዊነትና በአሰላሳይ አባታዊ ስሜት የሚመለከት ሰው በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ምግባረ-መልካምነቱ ተወዶ እንዲከበር አድርጎታል፡፡ የእሱ ተወዶ ተከባሪነት… በዜጎች ዘንድ ብቻ አይደለም፡፡ በፀጥታ የሚሠራ፣ ከሕዝብ ጋር ለመቀራረብና ተቀራርቦም አስፈላጊዎቹን የልማት ተግባራት ለማከናወን፤ ሕዝባዊ ፣ መንግሥታዊ፣ ሃገራዊ ሥራዎች ፍሬያማ በሚሆኑበት ደረጃ እንዲተገበሩ በማድረግ ክህሎቱ… የደርግ አባላት፣ የኢሠፓ አባላት፣ የክፍለ ሃገር አስተዳዳሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ ወዛደሮች፣ ገበሬዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች ስሙን በመልካም ያነሱታል፡፡ ስሙን አንስተውም ብቻ አያበቁም፡፡ ወደው የሚያከብሩት ሰው መሆኑን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባራቸው ጭምር ይገልጹለታል፡፡
ስለሺ መንገሻ፤ ከፍ ብሎ ይመራል፡፡ ያስተባብራል፡፡ ዝቅ ብሎ ይወያያል፡፡ ምክር፣ ለመፍትኄ ይጠቅማሉ ያላቸውን ሐሣቦች ይጠይቃል፡፡ ሐሣብ ያዋጣል፡፡ በነፃነት ስሜት በሕዝቡ መሀል ይመላለሳል፡፡ ከወጣቶች ጋር በእስፖርታዊ ውድድር ይሳተፋል፡፡ ሳቅ ጨዋታ በሚኖበት ሥፍራ በቁጥብ ፈገግታውና በደርባባ የአስተዋይነቱ ገጽታው ታጅቦ በወገኖቹ መሀል ተቀምጦ የዚያ ሳቅ ጨዋታ ደስታ ተጋሪ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከዚያም ወደ እናት ሃገር ሥራው ያልፋል፡፡ አዎ!…. እሱ በዘመነ-ደርግ ‹‹መማር፣ መማር፣ አሁንም መማር›› የሚለውን መፈክር ‹‹መሥራት፣ መሥራት፣ አሁንም መሥራት›› ወደሚለው መርህ በተግባር የለወጠ የኢትዮጵያ ልጅ ነበር፡፡
በመጋቢት ወር 1978 ዓ.ም በአሰላ ከተማ የታተመው ‹‹መንደር ምሥረታ በአርሲ›› የተሰኘው መጽሔት በገጾቹ ላይ ካሰፈራቸው መልዕክቶች መካከል፡- ‹‹ዛሬ አርሶ አደሩ በመንደር ተሰባስቦ ለወደፊት ትግሉና ድሉ ምቹ ሁናቴ እንደፈጠረ ሁሉ፤ ከአሁኑ የበልግ ወቅት አንስቶ ለእርሻው ሥራ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በምርት የራሱን ሕይወትና የሃገሩን ኢኮኖሚያዊ ዕደገት ማዳበር እንዲችል ብሎም አካባቢውንና ራሱን ከማንኛውም የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ጥቃት እንዲከላከል፤ የፓርቲ የመንግሥትና የማኅበራት በአጠቃላይም የክፍለ ሃገሩ ሕዝብ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለብን ላስገነዝብ እወዳለሁ፡፡…›› የሚለውን የመቶ አለቃ ስለሺ መንገሻን ቃል አስፍሯል፡፡
ስለሺ መንገሻና በወቅቱ ከአጠገባቸው የነበሩት በልማት ላይ ልዩ ትኩረት ያደረጉ የተግባር ሰዎች፤ የመንደር ምሥረተናውን ዓላማ ለማሳከት፤ ሕብረተሰቡን አስተባብረው ባደረጉት የተግባር እንቅስቃሴ፤ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ፤ በአርሲ ክፍለ ሃገር በሚገኙት የጭላሎ፣ የአርባጉጉ እና የጢቾ አውራጃዎች፡- 231 የመሠረተ ልማት ጣቢያዎችን፣ 124 የባሕል አዳራሾችን፣ 44 የመዝናኛ ሥፍራዎችን ወይም ማዕከሎችን፣ 17 የአፀደ-ሕፃናት ማለትም የመዋዕለ ሕፃናት ተቋሞችን፣ እንዲሁም 102 የተጣራ ውሃ ማመንጨት የሚችሉ የውሃ ኩሬ ግንባታዎችን ሥራ ለፍሬ አብቅተዋል፡፡ ከነዚህ ተግባራት በተጓዳኝ 570 ኪሎ ሜትር የሸፈነ የጥርጊያ መንገድም በአርሲ ክፍለ ሃገር መሥራት የቻሉ ሲሆን፤ 46.28 ካሬ ኪሎ ሜትር በሚሸፍን ቦታ ላይም ለአፈር ጥበቃና እንክብካቤ ብሎም ለእርሻው ሥራ ዋስትና ሊሰጥ የሚችል የእርከን ሥራም አከናውነዋል፡፡
እንደመውጫ፡- ‹‹በጣም ቅን፣ ንፁህ፣ በሙስና ወይም በምዝበራና ብኩንነት የማይታወቅ፣ ሕዝባዊ የሆነ ሰው ነው ጓድ ስለሺ መንገሻ፡፡ ጥሩ አስተዳደሪ፣ ተግባቢ፣ በአስተዋይነት ለሃገር ለውጥና ዕድገት ከሠሩ የደርግ አባላት መካከል አንደኛው ነው፡፡ በሁሉም ዘርፍ ልዩ የሆነና የምስጉን ባሕሪ ባለቤት፡፡ ‹እኔ አንደኛ የፓርቲ ጸሐፊ ነኝ …› ብሎ የማይኮፈስ ጥሩ ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ ከሕዝቡ የማይለይ፣ አነሳሱን የሚያወቅ፣ አስቀድሞ የነበረበትን ቦታ ያልረሳ ታማኝኛ ጨዋ ወገናችን ነበር፡፡ በሕይወቱ መጨረሻም በእጅ ላይ ለራሱ መታከሚያ ሊሆነው የሚችል ጥቂት ብር ዕንኳን ያልነበረው፤ በደርግ አባልነቱም እንደ ጓዶቹ ሁሉ ለሃያ ዓመታት ከአራት ወራት በወህኒ ከቆየ በኋላ ለሃገሩና ለወገኑ በደግነት፣ በታታሪነትና በጨዋነት መንፈስ ለኢትዮጵያ እንዳልሠራ፤ በኢትዮጵያ ሰዎች መካከል በባይተዋርነት ኖሮ ያለፈ ሰው ነው…. ጓድ ስለሺ መንገሻ›› ብለውኛል፤ ይህን ጽሑፍ ለመከተብ ከመነሳቴ በፊት በስልክ ያነጋገርኳቸው በደርግ የአስተዳደር ዘመን በምክትል ሚኒስቴር ማዕረግ የፕሬዝደንት መንግሥቱ ኃይለማርያም የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ እና በሙያቸውም ዕውቅ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ጓድ ፋሲካ ሲደልል፡፡
አባሪና ልዩ ማስታወሻ፡- ብዙዎቹ የደርግ አባላት ዛሬ በሕይወት የሉም፡፡ በ1983 አጋማሽ ጓድ ገዛኸኝ ወርቄ ከነ ልጁ በሰሜን ጎንደር ራሱን ሰውቷል፡፡ ‹‹እሱ (ገዛኸኝ) አቶ አሰፋ ጫቦ እንዳሉት (ነፍሳቸውን ይማረውና) ‹‹በቆመለት ዓላማ መሠረት ለኢትዮጵያ አንድነት ክብርና ነፃነት የመጨረሻውን ጽዋ ነው…›› የተጎነጨው፡፡ በዚህ እየተገባደደ ባለው ዓመትም ስለሺ መንገሻ እና ኮሎኔል አሸብር አማረ ከዚህ ዓለም አጠቃላይ ድካም አርፈዋል፡፡ ባለፉት ዓመታትም እነ ጓድ ደበላ ዲንሣ፣ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ፣ ፍስሐ ደስታን ጨምሮ ሌሎችም በተፈጥሮ የመኖር አለመኖር ሕግ መሠረት ወደማይቀርበት ሥፍራ ሄደዋል፡፡ ጓድ ተካ ቱሉ እና ካሣዬ አራጋው በወህኒ ቤት ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ዛሬ ማለትም.. ይህ ጽሑፍ እየተረቀቀ ባለበት ጊዜ (በ12/9/2018) ከደርግ አባላት መካከል እነ ማን በሕይወት ቀሩ?… ለሚለው የሚከተለው መልስ ነው፡፡ ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ጄነራል አዲስ ተድላ፣ ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህ፣ ሻለቃ ደጀኔ ወንድማገኝ፣ የመቶ አለቃ ግርማ አድማሱ፣ የመቶ አለቃ በጋሻው አታላይ፣ ማስተር ቴክኒሺያን ገሠሠ ወልደኪዳን፣ ጓድ ውብሸት ደሴ፣ የመቶ አለቃ በጋሻው ጉርሜሣ…አሉ፡፡ ክቡራንና ክቡራት የግዮን መጽሔት ታዳሚያንና ሌሎችንም አንባቢ ኢትዮጵያውያንን ያሰንብትልኝ!
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 23 ግንቦት 2018 ዓ.ም
