ሴቶችን በቤት ውስጥ በማገዝ  መልካም ማህበረሰብ መፍጠር ተጀምሯል

Date:

በቤት ውስጥ የሚሠሩ ተግባራትን ተከፋፍሎ በመሥራት ሴቶችና እናቶችን መደገፍ እንደሚቻልና ይህም የአኗኗር ለውጥ እያመጣ እንደሆነ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች ፣ ከ ኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት (Newa) እና ከኦክስፋም ኢትዮጵያ ጋር በትብብር ባዘጋጁት የማህበረሰብ ውይይት እና ስልጠና ላይ እንደተገለጸው  በሥልጠናው ሴቶችን ቤት ውስጥ ማገዝ የጀመሩ ወንዶች ለውጥ ማምጣታቸው ተነግሯል።

ለ6 ወራት በየካ ክፍለ ከተማ ለወረዳ 10 እና 12 ነዋሪዎች ሥልጠናው የተሰጠ ሲሆን በሥልጠናው የማሳረጊያ እና የዕውቅና ሥነ ሥርዓት ላይ የማህበሩ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ፌቨን አርአያ እንዳሉት የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች ከሚሠራቸው ተግባራት አንዱ የማይከፈልባቸው የቤት ውስጥ ሥራዎች ላይ እናቶችን በማገዝ ለውጥ ማምጣት ነው።

እንደ ሥራ አስፈፃሚዋ ገለፃ ማህበሩ በተመረጡ ወረዳዎች ላይ ይህን የማይከፈልበት የቤት ውስጥ ክብካቤ ሥልጠና ሲሰጥ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችልም ታምኖበት ነው።

ከየካ ክፍለ ከተማ ብቻ ለ180 ነዋሪዎች ሥልጠናው የተሰጠ ሲሆን ሥልጠናውም 6 ወር የወሰደ ነበር።

ሥልጠናው ፕሮፌሽናል በሆኑ የማህበረሰብ  ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን አንዱ የትምህርት ክፍለ -ጊዜ ሁለት ሰዓታት ይወስዳል። እንደዚሁም ስልጠናውን ቀለል ለማድረግ በቡና እና በዳቦ ሥነ ሥርዓት እንደሚካሄድ ከአሠልጣኞች አንዷ የሆኑት ወይዘሪት ቃልኪዳን ፍርድአወቅ  ተናግረዋል።

ሥልጠናውን ሴቶችም ወንዶችም በተለያየ ቦታ የሚወስዱ ሲሆን ከፍተኛ ትምህርት ከቀሰሙት ሠልጣኞች አንዷ ሜሮን ገንቢ በሥልጠናው ከእርሷ ባለፈ ባለቤቷ ለውጥ እንዳመጣ ትናገራለች።

” በፊት ቤት ውስጥ ብዙ ኃላፊነት ስለነበረኝ በከፍተኛ ድካም ውስጥ ነበርኩ። ከስልጠናው በኃላ ግን ሁላችንም የቤተሰብ አባላት ሥራ የተከፋፈልን በመሆኑ  ብዙ ነገር ቀላል ሆኖልኛል ” በማለት ምስክርነት ሰጥታለች።

በመርሀ ግብሩ ላይ የታደሙ ወንዶችም እንጀራ ከመጋገር አንስቶ ቤት ውስጥ መታገዝ በሚገባቸው ጉዳዮች ሚስቶቻቸውን እያገዙ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች በዕለቱ የእናቶች ቀንን በማስመልከት ልዩ ልዩ መሰናዶዎችን ያቀረበ ሲሆን የዕለቱ ታዳሚዎችም  ይህን ላስተባበሩት የተቋሙ ባለሙያዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች ይህን የሥልጠና መርሀ- ግብር እንዲሳካ ላገዙት የዕድሮች ምክርቤት፣ የወረዳ 10 እና 12 አመራሮች፣ እና ወጣቶች   የዕውቅና ስጦታ አበርክቷል።

በተለይም ደግሞ በሥልጠናው ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ሚስቶቻቸውን ያገዙ፣ አርአያ የሆኑ 15 ባሎችም የዕውቅና ስጦታ እንደተበረከተላቸው  ለማወቅ ተችሏል።

በተጨማሪም የመርሀ ግብሩ አሰልጣኞች፣በዕምነት ጌትነት፣ ቃልኪዳን ፍርድአወቅ፣ ሜሮን መኒሳ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች(ኢሰመተ) በየካቲት 8 ቀን 2013 የተመሰረተ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን  በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ኤጀንሲ በመዝገብ ቁጥር 5398 በይፋ ተመዝግቦ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ነው።

ኢሰመተ የጾታ እኩልነትን ማሳደግ እና የኢትዮጵያን ሴቶች እና ልጃገረዶች መብት በማስረጃ በተደገፈ ውትወታ ለማድረግ መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ ያለመ ድርጅት ነው። የኢሰመተ ተልዕኮ የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ እና ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ለማብቃት የህግ ክፍተቶች፣ አድሎአዊ ህጎችና አሰራሮች፣ ፖሊሲዎችን እና ጎጂ ማህበራዊ ልማዶች እና ተግባራትን እንዲሁም ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃትን እንዲወገዱ መስራት ነው።

ስትራቴጂያዊ አካሄዱም በምርምርና ማስረጃ ፣ በንቅናቄ ግንባታ፣ በውትወታ፣ የሴቶችን እና የተቋማትን አቅም በማጎልበት እና ግንዛቤን በማሳደግ ነው።

የዚህን መርሀ -ግብር የሚድያ ማስተባበር እና የይዘት ዝግጅት ዕውን ያደረገው ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን (ዕዝራ እጅጉ) እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአህጉሪቱን የርስ በርስ ንግድ ልውውጥ 250 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቀደ

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ዋና ፀሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ...

በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች ክፍያ መፈጸም አይጠበቅባቸውም

አሜሪካ እና ኢራን በተስማሙበት የመግባቢያ ሰነድ መሠረት በሆርሙዝ ወሽመጥ...

እስራኤል ጦሯ በደቡብ ሊባኖስ እንደሚቆይ አስታወቀች

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ እንደተናገሩት፤ በአሜሪካ እና በኢራን...

ኧረ ፋታ ስጡን?!

መንግስት ግን" ምን ሁኑ ?" ሊለን ነው :: አጀንዳ...