‹‹ስኬቴን የምለካው መንፈሰ ጠንካራ ስላደረገኝም ጭምር ነው››

Date:

ኢየሩሳሌም አበራ

ይኽ የኢየሩሳሌም አበራ አነሳሽ ታሪክ ነው፡፡ ታሪኳ አነሳሽ ተብሎ ለመተረክ ያበቃው ግን በብዙ የሕይወት ውጣ ውረድ እና ስንክሳር ውስጥ በቆራጥነት ጸንታ በመቆሟ ነው፡፡ ኢየሩሳሌም የተወለደችው በመለስተኛዋ የይርጋለም ከተማ ነው፡፡ ይቺን ምድር ከተቀላቀለች በኋላ የነበሩት የመጀመሪያ የታዳጊነት ዘመናቷ በብዙ ብሩህ ተስፋ እና ሕልሞች የተሞሉ ነበሩ፡፡ በዚህም ሳቢያ ትከታተለው የነበረውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በማቋረጥ ወደ ሀዋሳ እንድታቀና እና ሕይወት ያቀረበችላትን ዕድሎች ተጠቅማ ራሷን ለማሻሻል ፈለገች፡፡

ኢየሩሳሌም በሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ ተቀጥራ ሥራ ስትጀምር ግን ቀላል የማይባሉ ፈተናዎች ገጠሟት፡፡ የሚከፈላት አነስተኛ ደምወዝ እንኳንስ ቤተሰቦቿን ልታግዝበት ለመኖር ከሚያስፈልጋት ወጪ ጋር በፍጹም ሊጣጣም ባለመቻሉ ተግዳሮቱ የምትቋቋመው አልኾነ አለ። እናም የእርሷንም ኾነ የቤተሰቧን ኑሮ ለመደጎም ተጨማሪ ሥራ መሥራት እንዳለባት ውሣኔ ላይ ደረሰች፡፡ አለቃዋ በጠቆማት ተጨማሪ ሥራዎች ላይ ተሠማርታም ገቢዋን ለማሳደግ ሞከረች፡፡ ኾኖም የቻለችውን ጥረት ብታደርግም ኑሮዋን ለመቀየር የሚያስችል ዐቅም መፍጠርም ኾነ ገቢ ማመንጨት ሳይኾንላት ቀረ፡፡

በዚህ መሃል ግን የሕይወቷን አቅጣጫ ሊቀይር የሚችል አጋጣሚን አስተዋለች፡፡ ይህም መቅደስ በተባለችው የቅርብ ጓደኛዋ ሕይወት ላይ የተፈጠረውን ትልቅ ለውጥ ያጤነችበት ነበር። መቅደስ የደረሰችበት ስኬት በፈጠረባት ተነሳሽነትም፣ ኢየሩሳሌምም ወደ ተሻለ ሕይወት ሊመራት የሚችለውን መንገድ ለማግኘት ወሰነች። በሌላ አነጋገር መቅደስ የተከተለችውን ህይወትን የመለወጥ መንገድ ተጠቅማ የራሷን ሁኔታ የምትቀይርበትን መንገድ ለማግኘት ቆርጣ ተነሳች።

ይኽ ውሣኔዋም ኢየሩሳሌምን ለሰዎች ለውጥ በጎ ልብ ካለው አንድ አማካሪ ጋር እንድትገናኝ በሩን ከፈተላት፡፡ አማካሪውም ለሕይወቷ ጠቃሚ ምክር እና ድጋፍ ለገሣት። እርሷም ከአማካሪው ያገኘችውን አዲስ እውቀት በመታጠቅ የወደፊት ሕይወቷን ሊያቃና የሚችል ጉዞ ጀመረች። ኾኖም በዚህ ሒደት፣ ባሰበችው የስኬት ሃዲድ ላይ እንዳትገሰግስ እንቅፋት የሚኾኑ ችግሮች በሕይወቷ ውስጥ መከሰታቸው አልቀረም፡፡ ባላሰበችው አጋጣሚ አስከፊ የሆነ የጾታዊ ጥቃት ሰለባ ሆነች፡፡ ይኽም ላስቀመጠችው ስኬት ደንቃራ መኾኑ አልቀረም፡፡

እርሷ ግን በሚገርም ጥንካሬና ጀግንነት ያጋጠማትን ፈተና ከመወጣት አልቦዘነችም። ሕይወቷን ሊያመሰቃቅል ካደፈጠባት የአዕምሮ መታወክ አጋጣሚ አምልጣ፣ ከደረሰባት ጉዳትም በከፍታ የተቀናጀ የወጣቶች ፕሮጄክት በኩል ያገኘችውን የሥነልቦና ድጋፍ ተጠቅማ ከመውደቅ ተርፋ ለመቆም በቃች፡፡ ይህ ሊሆን የቻለውም ኢየሩሳሌም እንዲህ ካለ ተግዳሮት ማምለጥ ከሚፈጥረው ስሜት ማገገም እና መልሶ የማደግን አስፈላጊነት በመገንዘብ የሥነልቦና ምክር እና መመሪያ ሊሰጧት ከሚችሉ ባለሙያዎች ተገቢውን ድጋፍ በመጠየቋ ነው። በእነሱ እርዳታም፣ የተፈጠሩባትን ውስብስብ ስሜቶች እና ክፉ የሕይወት አጋጣሚዎች ያሳደሩባትን ተጽዕኖዎች በማራገፍ ከበፊቱ የበለጠ ጠንካራ እና ብርቱ ኾና መቆም ቻለች።

ፈጣኗ ኢየሩሳሌምም በማያወላውል ጽናት የቀድሞ ሥራዋን ትታ ወደ ሥራ ፈጣሪነት ገባች። የራሷን የቡና መሸጫ ኪዮስክ በማቋቋም ሕይወቷን መልሳ የምትገነባበት እና በአዲሱ ነፃነቷ መጽናኛ የምታገኝበት አስተማማኝ የሥራ መስክ ፈጠረች። ይኽንን በማድረጓ በገዛ ሕይወቷ ላይ ከፈነጠቀችው ተስፋ ባልተናነሰ፣ ተመሳሳይ ፈተናዎች ለሚገጥማቸው ሌሎች ወገኖቿም የተስፋ አብርኾት መኾን ቻለች።

በዚህም ዛሬ ላይ ኢየሩሳሌም በእያንንዱ ሰው ውስጥ ምን ያህል ብርታት፣ ጥንካሬ እና ገደብ የለሽ ዕምቅ አቅም ለመኖሩ በተምሳሌትነት የምትታይ ሰው ኾናለች። ከችግር ወደ አሸናፊነት የተምዘገዘገው የስኬት ጉዞዋ የሚለካውም፣ በቁሳዊ ስኬቶች ብቻ ሳይሆን በመንፈስ ጥንካሬ እና መውጫ መንገድ ለመቅረጽ ባላት ድፍረት መኾኑንም ብዙዎች አስታውሰው ብዙ እንዲማሩባት ምክንያት ኾናለች።

ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 218 ሕዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በ2026 የዓለም ዋንጫ ላይ ለተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖች የሚጫወቱ ወንድማማቾች

የ2026 የፊፋ የዓለም ዋንጫ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ምርጥ ተጫዋቾችን...

ኢንፊኒቲ ለቤትና ለመኪና መግዣ ብድር እየሰጠ እንደሚገኝ አስታወቀ

ኢንፊኒቲ ኃላፊነቱ የተወሠነ መሠረታዊ የቁጠባ እና ብድር ኀብረት ሥራ...

የአዲሱ የወንጀል ህግ ስነ-ስርዓት የእርማት ስራዎች ሳይጠናቀቁ በሥራ ላይ እየዋለ ነው

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላለፉት 64 ዓመታት...

ናይጄሪያው ዩናይትድ ካፒታል በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የውጭ ኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድ አገኘ

​የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በሀገሪቱ የካፒታል ገበያ ታሪክ ለመጀመሪያ...