በሳዑዲ ዓረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ወደ 200 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሞት ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ሚድል ኢስት አይ የዜና ምንጭ የአገሪቱን ባለሥልጣናትና ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጠቅሶ ዘግቧል።
በእስር ላይ የሚገኙት እነዚህ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች፣ ይዘቱ ምን እንደሆነ በውል የማያውቁትንና በዓረብኛ ቋንቋ የተጻፈ የጥፋተኝነት ሰነድ በፖሊስ እንዲፈርሙ እንደሚገደዱ በሚስጥር ለጋዜጣው ተናግረዋል። ይህ አስጨናቂ ሁኔታ በስደተኞቹና በቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ስጋትና ድንጋጤን ፈጥሯል።
እንደ ዘገባው ማብራሪያ፣ ካሚስ ሙሻይት በተባለው እስር ቤት ውስጥ ብቻ 58 ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች ታስረው የሚገኙ ሲሆን፣ ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ደግሞ ከትግራይ ክልል የሄዱ ሦስት ኢትዮጵያውያን ላይ የሞት ቅጣት ተፈጽሞባቸዋል።
የዜና ምንጩ የነዚህን ሕይወታቸው ያለፈውን ፍርደኞች ስም ጭምር በዘገባው አካቶ ይፋ አድርጓል። ድርጊቱ በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ ያሉ ዜጎቻችንን ለመታደግ አስቸኳይ የዲፕሎማሲና የሰብአዊ መብት ጥረት እንደሚያስፈልግ አመላካች ሆኗል።
