የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሶማሊኛ ቋንቋ ያዘጋጀው የልጆች መጽሔት በጅግጅጋ ከተማ በደመቀ ሥነ-ሥርዓት ተመርቋል ።
ይህ አዲስ መጽሔት ትውልድን በእውቀትና በመልካም ሥነ-ምግባር ለመቅረጽ ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በምርቃቱ ላይ የተገኙት የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሁመድ መጽሔቱ የዲጂታል ሚዲያ በልጆች ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
መጽሔቱ በተለይ የልጆችን የማንበብ ባህል በማሳደግ፣ ስለ ሀገራቸውና ስለ ክልላቸው ታሪክ እንዲሁም ባህል በቂ እውቀት እንዲጨብጡ በማድረግ ረገድ ትልቅ ፋይዳ አለው።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መሳፍንት ተፈራ እንደተናገሩት፣ “ኡበድሰን” ልጆች በእውቀት ታንጸው እንዲያድጉ ከማገዙም ባለፈ፣ ማኅበራዊ ሚዲያ በሕፃናት ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
ድርጅቱ በተለያዩ ቋንቋዎች ከሚያሳትማቸው የልጆች መጽሔቶች መካከል አንዱ የሆነው “ኡበድሰን”፣ ነገ አገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ውጤታማ የሥራ ውጤት መሆኑ ተመላክቷል።
