በኬንያ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በጸጥታ አካላት እና በተቃዋሚዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የአራት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ ከ30 በላይ የሚሆኑት ደግሞ መቁሰላቸው ተገለፀ።
የኬንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኪፕቹምባ ሙርኮመን ባሰጡት መግለጫ፣ “ሕገ-ወጥ የሁከት ተቃውሞ” ሲሉ በጠሩት ድርጊት ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ 348 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እና ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ አራቱ ሰዎች እንዴት ሕይወታቸው ሊያልፍ እንደቻለ በዝርዝር ባይገልጹም፣ የአይን እማኞች ግን ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃል በናይሮቢ የነበሩ የፖሊስ አባላት በተቃዋሚዎች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ተናግረዋል።
በተቃውሞው ሳቢያ በርካታ ተጓዦች በከተማዋ ዳርቻዎች እና መነሻዎች ላይ ለእንግልት የተዳረጉ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች በዋና ዋና መንገዶች ላይ ጎማዎችን በማቃጠል እና በተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ቢያንስ ሁለት መኪናዎችን ማቃጠላቸውን ተከትሎ የከተማዋ መሃል ሙሉ በሙሉ ጭር ብሎ ውሏል።
በኬንያ ባለፈው ዓርብ የተመዘገበው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛው የተባለ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት የናፍጣ ዋጋ በ23.5 በመቶ እንዲሁም የቤንዚን ዋጋ በ8 በመቶ ከፍ ብሏል።
የኬንያ መንግሥት ለዚህ የዋጋ ጭማሪ በምክንያትነት የጠቀሰው የኢራን ጦርነትን እና በዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት ላይ ያሳደረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ቢሆንም፣ በሸማቾች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለማቃለል ሲባል ታክስ መቀነሱን አስታውቋል።
ምንጭ ኤፒ
