ትራምፕ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ቁልፍ የአሜሪካ አጋር ሀገራት መሪዎች ከቴህራን ጋር የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል ሲሉ ለማክሰኞ ታቅዶ የነበረው ወታደራዊ ጥቃት እንዲራዘም እንደጠየቋቸው ገልጸዋል።
ሆኖም ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ ዩናይትድ ስቴትስ መጠነ-ሰፊ ጥቃት ለመሰንዘር በተጠንቀቅ ላይ መሆኗን አስጠንቅቀዋል።
ይሁን እንጂ ተቀባይነት ያለው ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ፣ የአሜሪካ ጦር ኃይሎች ለ“ሙሉ እና ለመጠነ-ሰፊ ጥቃት” በተጠንቀቅ እንዲቆዩ መመሪያ መሰጠቱን አክለው ገልጸዋል።
ሰኞ ዕለት የመድኃኒት ዋጋን በተመለከተ በተዘጋጀ መግለጫ ላይ ለተገኙ ጋዜጠኞች ትራምፕ ሲናገሩ፦ “አንድ መፍትሄ ላይ የመድረስ በጣም ጥሩ ዕድል ያለ ይመስላል። በቦምብ ሳናወድማቸው ይህንን ማድረግ ከቻልን እኔ በጣም ደስተኛ እሆናለሁ” ብለዋል።
ይህ መግለጫ የወጣው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ቀደም ሲል ‘ትሩዝ ሶሻል’ (Truth Social) በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “የኳታሩ አሚር ታሚም ቢን ሀማድ የሳዑዲ አረቢያው አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን አል ሳዑድ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፕሬዚዳንት መሐመድ ቢን ዛይድ ለነገ ታቅዶ የነበረውን በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ላይ የሚሰነዘረውን ወታደራዊ ጥቃት እንድንገታው ጠይቀውኛል።” የሚል ሀሳብ ካሰፈሩ በኋላ ነው፡፡
ትራምፕ አክለውም የባህረ ሰላጤው ሀገራት መሪዎች “በአሁኑ ወቅት ከባድ ድርድሮች እየተካሄዱ መሆናቸውን” እንደነገሯቸው እና አሁንም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል እምነታቸውን እንደገለጹላት ተናግረዋል።
ትራምፕ የቀረበው የውል ረቂቅ ኢራን የኑክሌር መሣሪያ እንዳታገኝ የማያወላውል እገዳን የሚያካትት መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ጉዳይ ለማንኛውም ስምምነት ዋነኛ ቅድመ-ሁኔታ መሆኑን አስገንዝበዋል።
“ይህ ስምምነት፣ በዋናነት፣ ኢራን የኑክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት ማድረግን ያካትታል!” ሲሉ አክለዋል።
ትራምፕ ለባህረ ሰላጤው መሪዎች ካላቸው “ክብር” የተነሳ የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴዝ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዦች ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄነራል ዳንኤል ኬን እና የአሜሪካ ወታደራዊ አዛዦች ለጊዜው ከታቀደው ዘመቻ እንዲቆጠቡ መመሪያ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
