የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ በእስራኤል እና አሜሪካ ላይ ድል ተቀዳጅተናል አሉ።
ኻሜኒ አሜሪካ በቀጥታ ጦርነት ውስጥ የገባችው “የጽዮናዊው አገዛዝ ሙሉ በሙሉ እንደሚወድም ስለተሰማት ነው፤ ነገር ግን አሜሪካ ምንም አላተረፈችም” ሲሉ ነው የተናገሩት።
ጠቅላይ መሪው አገራቸው በድል አድራጊነት ወጥታለች ያሉ ሲሆን፤ ለአሜሪካ ጥቃት “አጸፋውን ምላሽ እንደሰጠችም ነው የገለጹት።
አክለውም “በጽዮናዊው አገዛዝ ላይ ስለተጎናጸፍነው ድል እንኳን ደስ አላችሁ” ሲሉ ለህዝባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ኻሜኒ አሜሪካ በአገራቸው ጥቃት ከፈጸመች እንዲሁም ከእስራኤል ጋር የነበረው ግጭት ከቆመ በኋላ ባስተላለፉት የመጀመሪያ መልዕክት ነው ይህንን ያሉት።
የኢራን ህዝብ አንድነቱን በማሳየት “ህዝባችን አንድ ድምጽ ነው ያለው” የሚል መልዕክት አስተላልፏል” ሲሉም ለህዝቡ ምስጋና አቅርበዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራንን “እጅ እንድትሰጥ” መጠየቃቸውን የጠቀሱት ኻሜኒ አስተያየታቸው “ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት አንደበት በጣም ትልቅ ነው” በማለት ተችተዋል።
ኻሜኒ አክለውም “እንደ ኢራን ላለ ታላቅ አገር እና ህዝብ እጅ ስጡ ማለት ስድብ ነው፤ እጅ መስጠት የሚለው ቃል በመዝገበቃላችን ውስጥ የለም” ብለዋል።
ትራምፕ በዚህ አጋጣሚ አንድ እውነት እንደገለጡ የጠቀሱት ኻሜኒ አሜሪካውያን የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክን መቃወም ገና ከጅምሩ ሲቃወሙ መቆየታቸውን ነው ሲሉም አክለዋል።
BBC Amharic
