አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2026 የፕሪፎንቴይን ክላሲክ – ዩጂን ዳይመንድ ሊግ እና በአሜሪካ የፒችትሪ የጎዳና ሩጫ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸንፈዋል።
በአሜሪካዋ ዩጂን በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ የሁለት ማይል ርቀት ውድድር አትሌት አለሺኝ ባወቀ በቀዳሚነት አጠናቅቃለች፡፡
አትሌቷ ውድድሩን በበላይነት ያጠናቀቀችው የወቅቱ ፈጣን የሆነ ሰዓት 9 ደቂቃ ከ20 ሴኮንድ ከ02 ማይክሮ ሴኮንድ በማስመዝገብ ነው፡፡
ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሒሩት መሸሻ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ውድድሯን ጨርሳለች፡፡
በዚሁ ርቀት የተሳተፉት አትሌት ማርታ አለማየሁ 4ኛ፣ አትሌት የኔዋ ንብረት 7ኛ እንዲሁም አትሌት አሳየች አይቼው 8ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቅቀዋል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ የነጻነት ቀን ክብረ በዓል አካል ሆኖ በተካሄደው በ57ኛው የፒችትሪ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ በ31:02 በሆነ ሰዓት በመግባት ውድድሯን በበላይነት አጠናቅቃለች።
ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት መልክናት ውዱ 2ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሯን ጨርሳለች፡፡
