የኢትዮጵያ የወርቅ ወጪ ንግድ በያዝነው ዓመት 5.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስገኝ ሲገለጽ ይህም ከ2010 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር የ5,000 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን የማዕድን ሚኒስቴር አስታውቋል።
የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሃና ብርሃኑ “ኢትዮጵያ ታከናውናለች” በተሰኘው ብሔራዊ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ገለጻ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ውስጥ የማዕድን ዘርፉ ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ያበረከተው አስተዋጽኦ ከ0.8 በመቶ በታች መሆኑን አስታውሰዋል።
አክለውም መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2030 የማዕድን ወጪ ንግድ ገቢን ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማድረስ እና ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አምስት ቀዳሚ የማዕድን አምራች ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ እቅድ ማስቀመጡን ገልጸዋል።
ኢንጂነር ሃና ብርሃኑ በመድረኩ ያነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች ምንድን ናቸው ?
– በየዓመቱ ለከሰል (coal) ምርት ታወጣ የነበረውን 300 ሚሊዮን ዶላር በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል።
– የሲሚንቶ ምርት ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ከነበረበት 8 ሚሊዮን ቶን አሁን ላይ በዓመት ወደ 14 ሚሊዮን ቶን አድጓል።
– በአዲስ አበባ-ጂቡቲ ኮሪደር ላይ ያሉ ሦስት ጋዝ መሙያ ማደያዎች ተገንብተዋል።
– ከ1,500 በላይ የከተማ አውቶቡሶችን ከናፍጣ ወደ ጋዝ የመቀየር ሥራ እየተሰራ ነው።
– የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) በዓለም ላይ ካሉ ያልተነኩ ግዙፍ የፖታሽ ክምችት ባለበት አፋር ክልል ላይ የማልማት ፈቃድ አግኝቷል።
– ባለፉት 30 ዓመታት ምንም እሴት ሳይጨመርበት እንዲሁ ይላክ በነበረው ታንታለም የተሰኘውን ማዕድን በሀገር ውስጥ እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ መንግስት ከአሜሪካ ኩባንያ ጋር ድርድር ላይ ይገኛል።
– በየዓመቱ የብረት ምርትን ከውጪ ለማስገባት የሚወጣውን 1 ቢሊዮን ዶላር ለማስቀረት ያለመ ለመገንባት ስምምነት ተፈርሟል።
– የ40 ሚሊዮን ያህል አርሶ አደሮች ፍላጎት ለማሟላት በየዓመቱ ለማዳበሪያ ግዢ ከ2 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይደረጋል። መንግሥት የ40 በመቶ ድርሻ ያለው የማዳበሪያ ፋብሪካ በሚቀጥሉት 29 እስከ 30 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ ሙሉ ለሙሉ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ይሸፍናል።
@TikvahethMagazine
