እስከ አምስት ዓመት እስራት የሚያስቀጡ የመረጃ ነጻነት አዋጅ ጸደቀ

Date:

ለ15 ዓመታት በስራ ላይ ከቆየው “የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ” የመገናኛ ብዙኃንን የሚመለከተው ክፍል ተለይቶ ሌላ ራሱን የቻለ ህግ እንዲወጣለት የተደረገው በ2013 ዓ.ም ነበር። የመረጃ ነጻነትን የሚመለከተው ቀሪው ክፍል በተመሳሳይ መልኩ አዋጅ ቢዘጋጅለትም፤ ለፓርላማ የሚቀርብበት ሂደት ተጓትቶ ቆይቷል። 

ከዓመታት ጥበቃ በኋላ የመረጃ ነጻነትን ለመደንገግ የተዘጋጀው የአዋጅ ረቂቅ፤ ከሁለት ወራት በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ተደርጓል። ምክር ቤቱ መጋቢት 29፤ 2018 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የቀረበለትን ይህን የአዋጅ ረቂቅ፤ በዝርዝር እንዲታይ ለፓርላማው የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶት ነበር።

ቋሚ ኮሚቴው የአዋጅ ረቂቁን ለፓርላማ ለተወካዮች ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አምስት የሚደርሱ ውይይቶችን ካደረገ በኋላ የውሳኔ ሃሳብ አዘጋጅቷል። በረቂቅ አዋጁ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን እና አዳዲስ ድንጋጌዎችን ያካተተው የውሳኔ ሃሳብ፤ ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 18፤ 2018 በተካሄደ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ከቀረበ በኋላ አዋጁ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል። 

በረቂቅ አዋጁ ላይ የተደረጉት ማሻሻያዎች፤ በመግቢያው ላይ ከተቀመጠው የአዋጁን ዓላማዎች ከሚያብራራው ክፍል ጀምሮ “ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች” እስከተዘረዘሩበት ድረስ ያሉትን የሸፈኑ ናቸው። ከእነዚህ ማሻሻያዎች መካከል ከመረጃ አሰጣጥ ጋር የተያያዙ እስከ አምስት እስራት የሚያስቀጡ የጥፋት አይነቶች ይገኙበታል።  

“የመረጃ ነጻነት አዋጅ” የተዘጋጀው “ማንኛውም ሰው በመንግሥት አካል እጅ የሚገኝ መረጃን የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማሰራጨት ነጻነት በማረጋገጥ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን፤ እንዲሁም በህገ መንግሥቱ እና ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች የተረጋገጠውን የመረጃ ነጻነት ይበልጥ እውን ይሆን ዘንድ ለማድረግ ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ” እንደሆነ በረቂቅ ህጉ ላይ ተገልጾ ነበር። ዛሬ በጸደቀው አዋጅ ላይ “ከመንግሥት አካላት” በተጨማሪ “በግል ድርጅቶች ይዞታ ስር የሚገኝ መረጃን” መጠየቅ እንደሚቻል ተደርጎ ተስተካክሏል። 

በረቂቅ ደረጃ በነበረው አዋጅ “ማንኛውም የመንግስት አካል ፕሮጀክት ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ከፕሮጀክቱ ጋር የተያያዙ ፍሬ ነገሮች፤ ለጠቅላላው ሕዝብ ወይም ጥቅማቸው ለተነካባቸውና ሊነካባቸው ለሚችሉ ወገኖች፤ ከፕሮጀክቱ ጋር የተያያዙ ፍሬ ነገሮች መረጃን ከ30 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አትሞ ማውጣት ወይም ለሕዝብ ማሳወቅ እንደሚገባ” ተደንግጎ ነበር። በአዲሱ ማሻሻያ ይህ ድንጋጌ ተሻሽሎ “የማንኛውም የመንግስት ፕሮጀክት አፈጻጸም እና ውጤት መረጃን” እንዲያካትት ሆኗል።

ይህ አገላለጽ የተካተተው “የመንግስት አካል የፕሮጀክቱን ፍሬ ነገር ጨምሮ የፕሮጀክቱን ዝርዝር አፈጻጸም፣ ተጠቃሚዎችን እና ያስገኘውን ውጤት መረጃ ለጠቅላላው ህዝብ ይፋ ማድረግ እንዳለበት ማመላከት ተገቢ በመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ በአዋጁ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ሰፍሯል። የመረጃ ነጻነት፤ በመንግስት አካላት የሚከናወኑ “ቁልፍ እና መሰረታዊ ተግባራትን” የሚመለከቱ “የህዝብ ጥቅም መረጃዎችን ወይም ሰነዶችን” በተለያዩ የማሰራጫ ዘዴዎች “ለህዝብ ይፋ ማድረግን” የሚያካትት እንደሆነም በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ተብራርቷል።

የአዋጅ ረቂቁ አንድ መረጃ ጠያቂ “የማባዣ ወጪ ክፍያ” የማይፈጽምባቸውን ምክንያቶች ዘርዝሮ ነበር። “የህዝብ ጥቅምን የሚመለከት መረጃ” የሚጠይቅ አካል ይህንን ክፍያ መክፈል እንደማይጠበቅበትም በረቂቁ ላይ ተቀምጧል። በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ይህ አገላለጽ “በመገናኛ ብዙሃን የሚጠየቅ የህዝብ ጥቅም መረጃ” በሚል እንዲሻሻል መደረጉ ተገልጿል። 

ማስተካከያው የተደረገው “መገናኛ ብዙሃን መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ የሚሰሩ በመሆኑ፤ መረጃ ለማግኘት ክፍያ ሊጠየቁ እንደማይገባ ማመላከት ተገቢ በመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ተብራርቷል። የውሳኔ ሃሳቡ በረቂቅ አዋጁ በተካተቱት “ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች” ላይም በርከት ያሉ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አመልክቷል። 

ማሻሻያዎቹ ያተኮሩት በድንጋጌዎቹ ስር በተዘረዘሩት የወንጀል ቅጣቶች ላይ ነው። በአዋጅ ረቂቁ ላይ ከመረጃ ጋር በተያያዘ ጥፋት የፈጸመ ግለሰብ “በወንጀል ህግ ወይም አግባብነት ባለው ሌላ ህግ ተጠያቂ” እንደሚሆን ተደንግጎ ነበር። ይህ የአዋጁ ክፍል የገንዘብ እና የእስር ቅጣቶችን በማካተት እንደተሻሻለ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ተገልጿል።  

በዚህ መሰረት በአዋጁ የተረጋገጠን መረጃ የማግኘት ነጻነትን ለመጣስ በማሰብ፤ ሆን ብሎ መረጃን ወይም ሰነድን ያጠፋ፣ ያበላሸ፣ የቀየረ፣ የደለዘ፣ የደበቀ ወይም ያፋለሰ የበላይ ወይም የመረጃ ኃላፊ አልያም ይህንን ድርጊት ያዘዘ አካል፤ ጥፋቱ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ እስራት ወይም በመቶ ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንደሚቀጣ ተደንግጓል። ድርጊቱን የፈጸመው ኃላፊ በእስራት እና በገንዘብ ቅጣት እንደሚችልም በማሻሻያው ላይ ሰፍሯል። 

እነዚህ ቅጣቶች መረጃ ወይም ሰነድ “በተንኮል በከለከለ” ወይም “ሐሰተኛ ሰነድ በሰራ” ኃላፊ ላይ ተፈጻሚ ይሆናሉ። ሙስናን ወይም ሌላ ህገ ወጥ አሰራርን፣ የስራ አፈጻጸም ብቃት ጉድለትን በሚስጥር እንዲያዝ በማድረግ የወንጀል ጥፋቱ በፍርድ የተረጋገጠበት ኃላፊ ይኸው ቅጣት ይጠብቀዋል። የግለሰብ ወይም የመንግስት አካል ወይም የድርጅት ቅሌት ለመሸፈን መረጃ (ሰነድ) በሚስጥር እንዲያዝ ማድረግም ተመሳሳይ ቅጣት ያስቀጣል።

ሆን ብሎ የተሳሳተ ወይም ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ (ሰነድ) ለጠያቂ የሰጠ፣ ያለ በቂ ምክንያት የተቋሙን ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ ያልፈጸመ የበላይ ኃላፊ፣ የመረጃ ኃላፊ ወይም ሰራተኛ ላይ የሚጣሉ ቅጣቶችም በማሻሻያው ተዘርዝረዋል። ይህ ጥፋት መፈጸሙ በፍርድ ቤት ከተረጋገጠ፤ እንደ ጥፋቱ ክብደት ከሶስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከ25 ሺህ ብር በማያንስ ሆኖም ከ100 ሺህ ብር ማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ አሊያም በሁለቱም እንደሚቀጣ በጸደቀው አዋጅ ላይ ተደንግጓል።

በአዋጁ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለመረጃ ጠያቂዎች ከአንድ ጊዜ በላይ በተደጋጋሚ ምላሽ ያልሰጠ፣ ሚስጥር መሆኑን እያወቀ የመከላከያ እና የሀገር ደህንነት መረጃን የሰጠ ኃላፊ ወይም ሰራተኛ፤ ተመሳሳይ የቅጣት እርምጃ እንደሚወሰድበትም በጸደቀው አዋጅ ላይ ተቀምጧል። 

ሌላው በጸደቀው አዋጅ ውስጥ እንዲካተት የተደረገው፤ የበላይ ኃላፊን፣ የመረጃ ኃላፊን እና ሰራተኛን በአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከ25 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም ሁለቱንም ቅጣቶች ሊያስቀጡ የሚችሉ ድርጊቶች ናቸው። ከእነዚህ ድርጊቶች ውስጥ የመረጃ ጥያቄን ወይም በቃል የቀረበ የመረጃ ጥያቄን በቅጽ ላይ ለመሙላት ፈቃደኛ ያለመሆን እና ግልባጩን አለመስጠት ይገኝበታል።

እያወቀ ሀሰተኛ ወይም የተዛባ መረጃ (ሰነድ) ለተቋሙ የሰጠ ኃላፊም ሆነ ሰራተኛ ጥፋቱ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ፤ እንደየአግባብነቱ በአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከ25 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም በሁለቱም ይቀጣል።

መረጃ (ሰነድ) አትሞ የማውጣት ግዴታን አለመወጣት እንዲሁም ለአካል ጉዳተኛ ሊነበብ፣ ሊታይ ወይም ሊደመጥ በሚችል አግባብ መረጃ (ሰነድ) ተደራሽ ለማድረግ ምክንያታዊ እርምጃ የመውሰድ ግዴታን አለመወጣትም ለእነዚህ ቅጣቶች ይዳርጋል። እያወቀ ሀሰተኛ ወይም የተዛባ መረጃ (ሰነድ) ለተቋሙ የሰጠ ኃላፊም ሆነ ሰራተኛ ጥፋቱ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ተመሳሳይ ቅጣት እንደሚጣልበት በጸደቀው አዋጅ ላይ ተደነግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተላለፈ ማስጠንቀቂያ

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኢምባሲ በሀገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እየተከታተለና...

በበጀት አመቱ 22.9 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየተሠራ ነው

ከታቀደው 22 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ኩንታል እስካሁን  20...

በቬንዝዌላ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ የ32 ሰዎች ህይወት አልፏል

በቬንዙዌላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን 7.2 እና 7.5...

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ “ሉሲ” ላገኟት ፕሮፌሰር የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጠ

የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ፥...