የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በገንዘብ ዘርፍ እየታየ ያለውን ዓለም አቀፍ ለውጥ ተከትሎ “የማዕከላዊ ባንክ ዲጂታል ገንዘቦችን” በተመለከተ ጥናት በማድረግ ላይ መሆኑን አስታወቀ።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ዲጂታል ግብይቶች በእጅጉ እያደጉ ቢሄዱም፣ ጥሬ ገንዘብ አጠቃቀም ሙሉ በሙሉ አይጠፋም የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
“ምናልባትም ዲጂታል ግብይቶች በጥልቀት የሚሰፉበት እና በከፍተኛ ደረጃ የሚያድጉበት፣ ነገር ግን ለጥሬ ገንዘብ ግብይቶችም ምቹ ሁኔታ የሚኖርበት ባለ ሁለት ገፅታ መዋቅር ሊኖር ይችላል ብለን እንጠብቃለን” ያሉት ገዢዉ፣ “በእኛ ሀገር ከፍተኛ መጠን ያለው መደበኛ ያልሆነ ኢኮኖሚ፣ የገጠሩ ዘርፍ እና ሌሎችም አሉን። ስለዚህ የገንዘብ ግብይቶች ይቀጥላሉ ብዬ እጠብቃለሁ” ብለዋል።
እዮብ ተካልኝ ፤ በተለይም ወደ አዲሱ የፋይናንስ ዓለም በሚደረገው ሽግግር፣ ማዕከላዊ ባንኮች በዲጂታል ዘመን ለገጠማቸው ከባድ ፈተናዎች እውቅና ሰጥተዋል።
“ማዕከላዊ ባንኮች አሁን የማዕከላዊ ባንክ ዲጂታል ገንዘቦች ምን እንደሆኑ መረዳት አለባቸው.. ያ ገንዘብ የተለየ መልክ ሊይዝ ይችላል፣ ግን አሁንም ያ ገንዘብ ይኖራል” ብለዋል። በጉዳዩ ላይ ብሔራዊ ባንክ ጥናት እያካሄደ መሆኑን አረጋግጠው።
