‹‹በድርጅታችን ድጋፍ በርካታ ትምህርት ቤቶች ውጤታማ ኾነዋል››ዜናዬነህ ግርማ

Date:

ከተመሠረተ ከ10 ዓመታት በላይ የኾነው የ‹‹ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን›› መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ዜናዬነህ ግርማ ይባላሉ፡፡ወጣቶችን በማኅበራዊ ልማት ውስጥ እንዲሁም በባህላቸው የታነፁ እና አቅም ያላቸው የለውጥ አራማጅ እንዲሆኑ በማብቃት ረገድ ውጤታማ ተግባራትን ያከናወኑ ሰው ናቸው፡፡ የሥራቸውን አድማስ ወደ ተለያዩ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደር በማስፋትም ወጣቶች በክህሎትና በእውቀት ተደግፈው እንዲሁም የለውጥ ሐዋርያ ብቁ ኾው የሚወጡባቸውን ድጋፎች በድርጅታቸው በኩል አከናውነዋል፡፡ ለዚህ ትጋተቸው እሳቸውም ኾኑ ተቋማቸው በርካታ ሽልማቶችንና እውቀውናዎችን አግኝተዋል፡፡ለመኾኑ ድርጅታቸው ማን ነው? ያለፉት በርካታ ዓመታት ጉዞውና ውጤታማነቱስ እንዴት ይገለጻል? ስንል የሚከተለውን ቆይታ ከእርሳቸው ጋር አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!

ግዮን፡- በቅድሚያ ራስዎን ለአንባቢያን በማስተዋወቅና በድርጅቱ ውስጥ ያለዎትን የኃላፊነት ድርሻም በመግለጽ ቢጀምሩ?

ዜናዬነህ፡- ዜናዬነህ ግርማ እባላለሁ፡፡ የ‹‹ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን›› መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ነኝ፡፡ ድርጅታችንን በዋና ዳሬክተርነት ላለፉት 10 ዓመታት አገልግያለሁ፡፡

ግዮን፡- ድርጅቱ ከተመሠረተ ምን ያህል ዓመት ኾነው? ሥያሜውስ ምንን የሚገልጽ ነው? ራዕይና ተልዕኳችሁስ?

ዜናዬነህ፡- ድርጅታችን የተመሠረተው ከ10 ዓመታት በፊት ነው፡፡ ከተመሠረተ ጊዜ አንስቶ ለወጣቶች የተለያዩ ችግሮችን በመፍታት እንዲሁም መልካም አጋጣሚዎችን በማመቻቸትና በመደገፍ ይታወቃል፡፡ በተለይም ክልላዊና ሀገር አቀፋዊ በኾነ ደረጃ የወጣቶች ችግሮችን ለመፍታት ተቋማ አደረጃጅቱን አስተካክሎ  ወጥ በኾነ መንገድ  ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡በርካታ ውጣ ውረዶችንም አሳልፎ አሁን ላለበት ስኬት ደርሷል፡፡ሥያሜው በቀጥታ ስንተረጉመው ‹‹የወጣቶች እና የባሕል ልማት ፋውንዴሽን›› የሚል ትርጉም አለው፡፡ ወጣቶች የለውጥ አራማጅ እንዲኾ ፣ የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ ፣ በባሕላቸው እና በማንነታቸው ታንፀው ለሀገር ጥሩ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ የሚሠራ ተቋም መኾኑን ለመግለጽ ነው፡፡ የድርጅቱ ዓርማ የጎጆቤት ቅርፅ ሲኾን ወጣቶች ሀገራቸውን (ቤታቸውን) በጋራ መጠበቅ የሚያሳይ ኾኖ ሥሙ የወጣበት መንገድ የአብዛኛውን ወጣት የሚወክለና ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ወጣቶች ባሕል፣ ማንነትና የራሳቸው መገለጫ አላቸው፡፡ ተቋማችንም ወጣቶች ወደፊት ሁለንተናዊ ስብዕና ተላብሰው ራሳቸውንም ሀገራቸውንም እንዲያገለግሉ የሚቀረፁበት ተቋም ነው፡፡ ራዕያችንም በማኅበረሰባችን ውስጥ የለውጥ አራማጅ የኾኑ፣ አቅም ያላቸውና የበቁ ወጣቶችን ማየት ሲኾን ፤ ተልዕኳችን ደግሞ ወጣቶች በትምህርት፣ በባሕል ልውውጥ እና በማኅበራዊ ተሳትፎ ላይ ያላቸው ሚና እንዲዳብር በማድረግ፣ ከሕብረተሰባቸው ጋር የመተሳሰር አቅም እንዲኖራቸው መርዳት ነው፡፡

ግዮን፡- ድርጅታችሁ የሚያከናውቸው ሥራዎች በዝርዝር እንዴት ይገለጻሉ?

ዜናዬነህ፡- ከድርጅታችን ዋና ዋና ሥራዎች መካከል ቀዳሚው ዘላቂ አካባቢያዊ ሥነ ምሕዳር መፍጠር ነው፡፡ ሁለተኛው፣ ለወጣቶች ሠፊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እና መተዳደሪያ (ጥሪት) መፍጠር ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ መሠረታዊ የኾኑ ማኅበራዊ ግልጋሎቶችን ማድረስ ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ትምህርት ፣ ጤናና የመሳሰሉት ነገሮች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም የወጣቶች የአመራር ብቃት በማጎልበትና ተሳትፎዋቸውን በማሳደግ ማለትም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን የሚያጎላ ወይም የሚያበቃ ሥራ መሥራት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተቋማችን በሰብዓዊ መብትና በሰላም ዙሪያም ይሠራል፡፡ ማኅበራዊ ኢንተርፕራይዞችንም ለማስፋፋት እንጥራለን፡፡ በተለይም አካባቢያዊ ፣ ኢኮኖሚያው ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ተፅዕኖ ሊያመጡ የሚችሉ ሁኔታዎች ላይ በትኩረት እንሠራለን፡፡

ግዮን፡- የድርጅታችሁ የገቢ ምንጭ ምንድነው?

ዜናዬነህ፡- አብዛኛው የገቢ ምንጫችን በአጋሮች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በተለይ ውጭ የሚገኙና የእኛን ሐሳብ የሚደግፉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይደግፉናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የአባላት መዋጮም አለ፡፡ በቅርቡ የጀመርናቸው የገቢ ማስገኛ ሥራዎችም አሉ፡፡ አንዳንድ አገልግሎቶችን በመስጠት ገቢ የምናገኝበትን መንገድም እያመቻቸን ነው፡፡ ለምሳሌ ከአረንጓዴ ልማት ጋር በተያያዘ በተለይ በከተማ ግብርና ወጣቶች የአትክልትና ፍራፍሬ ሥራ ይሠራሉ ፤ ችግኞችን ያፈላሉ፡፡ ይሄንንም ሲያከናውኑ የተወሰነ የመገልገያ ግብዓት እናቀርብላቸዋለን፡፡ እነርሱም ከተገኘው ገቢ ራሳቸውን በመደጎም ድርጅቱንም አስተዳደራዊ ወጪዎችን በመሸፈን ይረዳሉ፡፡ ይህን ሥራ እኛም ወደ ፊት በሥፋት ዘላቂ በኾነ መንገድ የምንገፋበትና  ይኾናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በ2020 በአካባቢ ጥበቃ ላይ ለ4 ተከታታይ ዓመታት በሠራናቸው ጉልህ አስተዋፅዖዎች ከእንግሊዝ ሀገር በዓለም አቀፉ የብርቲሽ ካውንስል የወጣቶች የንቁ ዜጋ ኔትወርክ (አክቲቭ ሲቲዝስን ግሎባል ኔትወርክ) ሽልማት አግኝተናል፡፡ ወጣቶቹ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ለተከታታይ ዓመታት ላበረከቱት አስተዋፅዖና በአመራር ቁርጠኝነት ለተገኘው ውጤት እንደ ተቋም የተሰጠ እውቅ ነው፡፡

ግዮን፡- መንግሥት ለሲቪል ማኅበራት ያወጣው ሕግ እንዴት ያዩታል?

ዜናዬነህ፡- የሲቪል ማኅበረሰብ ሕግ ጉድለቶቹ ውስን ናቸው፡፡ ሕጉ ተሻሽሎ ከወጣ በኋላ በተለይ ክልል ላይ ያሉ የሲቪል ማኅበራት በርካታ ስለኾኑ ተገቢ የኾነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት አልተሰጣቸውም ብዬ አምናለሁ፡፡ በሌላ በኩል የሕጉ ጠንካራና መልካም ጎን የሚባለው በሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ዙሪያ ላይ እና በሰላም ግንባታ ድርጅቶች እንዲሠሩ የሰጠው መብት መልካም የሚባል ነው፡፡ እንዲሁም የሲቪል ካውንስል መቋቋሙና በተቋሙ በኩል ድምጻችንን እንዲሰማ መደረጉም መልካም የሚባል ነው፡፡ የካውንስሉ መቋቋም በደንብ እንድንሠራና ተጠያቂነትን እንድናሰፍን ረድቶናል ብዬም አስባለሁ፡፡

ግዮን፡- ድርጅታችሁ በሚሠጣቸው ሥልጠናዎችና እገዛዎች ምን ያህል ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል?

ዜናዬነህ፡- በርካታ ውጤታማ ድሎችን አስመዝግበናል፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት የኢትዮጵያ ወጣቶች የለውጥ ሐዋሪያ ኾነው በተለይ በሥልጠና እና በባሕል ልውውጥ መርሐ ግብሮች የማኅበራዊ ተሳትፎና የዕድገት ለውጦች እንዲያዳብሩ በርካታ ሥራዎች ሠርተናል፡፡ በዚህም ረገድ ድርጅቱ ተልዕኮውን በአግባቡ ያሳካበት ሂደቶች ናቸው፡፡ይህ ውጤት በቁጥር ይቀመጥ ቢባል ባለፉት 10 ዓመታት ከ100ሺህ ያላነሱ ወጣቶች በማኅበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ሲቪክ ዘርፎች ለመሳተፋቸው አስረጂ ይኾናል፡፡ እነዚህ ወጣቶች ለችግር የማይንበረከኩና ለሀገራቸው ልማትን የሚያመጡ ንቁ ዜጎች ናቸው፡፡ ይሄም ለሀገሪቱ ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና የራሱን ሚና ተጫውቷል ብለን እናምናለን፡፡ ድርጅታችን በጎ ፈቃደኞችን ጨምሮ በአሁኑ ጊዜ ከ70 በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት፡፡ ጊዜያዊ የወጣቶች በጎ ፈቃደኞች (ኢንተር) ጊዜያዊ የኮንትራት ሠራተኞች ጋር ሲደመር ደግሞ ከ100 በላይ ይኾናሉ፡፡

ግዮን፡- አድራሻችሁ የት ይገኛል?

ዜናዬነህ፡- በሀገሪቱ 4 ንዑሳን የክልል ከተሞች ላይ የቅርንጫፍ ቢሮዎች አሉን፡፡ ሀዋሳ ከተማ ላይ የደቡብን ቅርንጫፍ የሚመራ የሚያስተባብር አለን፡፡ በተጨማሪም ዲላ፣ ወሊሶ እና ሻሸመኔ ከተሞችም ላይ ሌሎች ቢሮዎች አሉን፡፡ በ6 ክልሎችና በ 2 የከተማ አስተዳደሮች ደግሞ የፕሮጀክት ተግባራዊ ስምምነት ውሎች አሉን፡፡ ከ10 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከ13 በላይ የመምህራን ኮሌጆች ጋር በአጋርነት እንሠራለን፡፡ ላለፉት 10 ዓመታት ወደ 50 የሚጠጉ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በተለይ በሳይንስ ዘርፍ ሴቶች ጎልተው እንዲወጡ እንዲሁም የመምህራንን አቅም ለማጎልበት የበኩላችንን ሠርተናል፡፡ በሥርዓተ ፆታ እኩልነት ላይ በርከት ያሉ ጥናቶችንና ተግባራትን አከናውነናል፡፡ በዘላቂ ሰላም ግንባታ ዙሪያና በወጣቶች በጎ ፈቃደኝነት ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሠርተናል፡፡ባልናቸው ክልሎች ውስጥም በርከት ያሉ ወጣቶች በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ተጠቃሚ የሚኾኑበትን ሁለገብ የእድገት መሠረት በማድረግና በንቃት ማሳተፍ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት ሠርተናል፡፡

ግዮን፡- በድርጅታችሁ ድጋፍ ምክንያት የተሻለ ቦታ ላይ የደረሰ ግለሰብ ወይም ተቋም ካለ ቢነግሩን?

ዜናዬነህ፡- በእኛ ተቋም ድጋፍ በርካታ ትምህርት ቤቶች ውጤታማ ኾነዋል፡፡ ለምሳሌ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በሰፊው ደግፈናል፡፡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች በተለይም በእንድብር፣ ወልቂጤና በተጨማሪም በአዲስ አበባም 5 ክፍለ ከተሞች ውስጥ ባሉ 20 ትምህርት ቤቶች፣ በሐዋሳ 8 ትምህርት ቤቶች፣ በኦሮሚያ ክልልም በ6 ዞኖች እንዲሁ ከ20 በላይ ትምህርት ቤቶች ጋር በመሥራት ውጤታማ እንዲኾኑ አድርገናል፡፡

ግዮን፡- ድርጅታችሁ በሲቪክ ማኅበራት ሥር ተመዝግቧል? ተጠሪነታችሁስ ለማን ነው?

ዜናዬነህ፡- እኛ የተመዘገብነው በፌደራል የሲቪክ ማኅበራት ባለሥልጣን ሥር ነው፡፡ በ2019 እንደ አውሮፓውያን ዳግም ምዝገባ ሲደረግ ተመዝግበናል፡፡ ከ2020 ጀምሮም የምንመራበትን መግባቢያ ሠነድ በመቅረፅ እንደዚሁም ሌሎች ተያያዥ ሕጎችን ተከትለን እየሠራን ነው፡፡

ግዮን፡- ድጋፍ የሚያደርጉላችሁ ዓለም አቀፍ ተቋማት ምን ዘርፍ ላይ የሚሠሩና የት የት የሚገኙ ናቸው?

ዜናዬነህ፡- ከእኛ ድርጅት ጋር የሚሠሩ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሲኾኑ ሀገር በቀሎችንም ያካትታል፡፡ለምሳሌ ኢኒሼቲቭ አፍሪካ (የስውዲሽ አለም አቀፍ ድርጅት)፣ ከአውስትራሊያ እና ከፊላንድ ኤንባሲዎች ጋር እንሰራለን፡፡ከዚህም በተጨማሪ የዩኑስኮ ዩኒሴፍ፣ ዩኤንዲፕ፣ በተባበሩት መንግሥታት አለምአቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አብረውን ይሠራሉ፡፡ብሪትሽ ካውንስል ፣የአውሮፓ ህብረት፣ ዩኤስኤአይዲ፣ አምሬፍ ሄልዝ አፍሪካ ኢልሪ እና የመሣሠሉት በሙሉ አጋሮቻችን ናቸው፡፡ከእነዚህ ሁሉ በላይ ግን የእኛ ዋናዎቹ አጋሮች ወጣቶች ናቸው፡፡ ወጣቶች ያላቸውን አቅም፣ ሀብትና ችሎታ በነፃነት ይዘው አብረውን ይሠራሉ፡፡ ወጣቶች ጠንካራ አዕምሯዊ ብቃት ሲኖራቸው በራስ መተማመናቸውን ጨምረው ለመብቶቻቸው የሚታገሉ ለሀገር የሚጠቅሙ ይኾናሉ፡፡ በሌላ በኩል ወጣቶችን አብቅተው የሚያወጡ ተቋማትና ድርጅቶችም በሀገራችን ውስጥ መኖራቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ ለምሳሌ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ ዩንቨርሲቲዎች እና መሰል ሥፍራዎች ወጣቶችን በማብቃት በኩል የሚሰሩ ናቸው፡፡

ግዮን፡- ለተቋማችሁ ከመንግሥት የሚደረግ ድጋፍ አለ?

ዜናዬነህ፡- ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት ስድስት ክልሎች ላይ የመሥራት የፕሮጀክት ትግበራ ውል ስምምነት አለን፡፡ የሥራ ፈቃድም አግኘተናል፡፡ ይህን ከመሳሰሉ ሁኔታዎች አንፃር እስካሁን ከመንግሥት እያገኘን ያለነው ድጋፍ በጣም ጠንካራ ነው፡፡ እኛ በየሩብ ዓመቱ ሥራዎቻችንን እናስጎበኛለን ፤ እናስገመግማለን፡፡ የተለያየ የመወያያ መድረክ እናመቻቻለን፡፡ የጎደለንን ነገር ይሞሉልናል፡፡ እኛም የምንፈልገውን ነገር በነፃና በግልፅ እንጠይቃለን፡፡ ስለዚህ እስካሁን ከመንግሥት በኩል ያጋጠመን የከፋ ችግር የለም፡፡ መንግሥትም ይህ እንዳይገጥመን በየጊዜው ክትትል ያደርጋል፡፡፡ በአጠቃላይ ሥራዎቻችን በመንግሥት በኩል ቅቡልነት አግኝተው ድጋፍ እየተሠጠን ነው፡፡ ለምሳሌ በመንግሥት የተገነቡ በሀዋሳ ፣ ዲና እና ሻሸመኔ 11 የሚኾኑ የወጣት ማዕከላትና የጤና ተቋማት  ከእኛ ጋር አብረው በመኾን ምቹ የኾነ የወጣቶች የማኅበራዊ ግልጋሎት ይሰጣሉ፡፡ በሌላ በኩል የጤናው ዘርፍ ከጤናው ተቋማት ጋር፤ የትምህርቱ ዘርፍ ከትምህርት ጋር ተቋማት ጋር፤ የሥራ እድል ፈጠራ  ፤ ከሥራ እድል ፈጠራ ተቋማት ጋር በቀጥታ በመገናኘት እንሠራለን፡፡ በየአገልግሎት ማዕከላችን እየመጡም ሥራዎቻችንን ይጎበኛሉ፡፡

ግዮን፡- የድርጅታችሁ የአጭርና ረጅም ጊዜ እቅድ ምንድነው?

ዜናዬነህ፡- በየዓመቱ የምናቅደውን ዕቅድ ለሲቪል ማኅበራት ባለሥልጣን እናስገባለን፡፡ በዚያ መሠረት ነው ሥራዎቻችንን የምናከናውነው፡፡ ሥራዎቻችን ከፍ ሲል እንደ ዘረዘርኩት በሰላም፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚዊያዊ ልማት፣ በሰብዓዊ መብት እና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ነው፡፡ በቅርቡ ግን ለቀጣዩ 10 ዓመት የምንመራበትን ፍኖተ ካርታ ቀርፀን ጨርሰናል፡፡ አዳዲስ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተሞክሮዎችን አካተን ለመሥራት ተዘጋጅተናል፡፡ ድርጅታችን የራሱ የኾነ ቢሮ ከፍቶ ከዚህ በፊት ተደራሽ ያልኾነባቸው አካባቢዎች ላይ ለመሥራት አቅደናል፡፡ ይህን በቀጣይ 2017 ዓ.ም አጋማሽ ለአጋሮቻችን የምናሳውቀው ይኾናል፡፡

ግዮን፡- በሥራችሁ ውጤታማነት ያገኛችሁት ሽልማት አለ? ለእናንተ የተለየ የኾነው ሽልማትስ የቱ ነው?

ዜናዬነህ፡- ባለፉት 10 ዓመታት ድርጅታችን በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ በቅርብ ያገኘናቸውን ሽልማቶች ለመጥቀስ ያህል፡-   በቅርቡ በባንኮክ ላይ በተካሄደ አለም አቀፍ የትምህርት ጉባኤ የ‹‹ግሎባል ስቲዚንሺፕ ኢዱኬተር›› ወይም አለም አቀፍ የዜግነት አስተማሪ ሽልማት አግኝተናል፡፡ ላለፉት 10 ዓመታት በትምህርት ተደራሽነት ላይ ጥራትና ፍትሀዊነት  ላመጣናቸው አመርቂ ውጤቶች የተበረከተልን ሽልማት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም በማኅበራዊ ኢንተርፕራይዝ ለሠራነው ሥራ በሴኔጋል ሽልማት አግኝተናል፡፡ እንደሁም በቅርቡ በሕንድ ሀገር በ2023 በማሕበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶች ላይ ላመጣነው የላቀ የሥራ አፈፃፀም ሽልማት ከሕንዱ የባላቪካዛ የማኅበራዊ ድርጅት ሽልማት አበርክቶልናል፡፡በተጨማሪ እንደግለሰብ በስዓዊነት ላይ በተሠራው ሥራ የክብር ዶክሬት አግኝቻለሁ፡፡

ግዮን፡- ‹‹ከፍታ ለወጣቶች›› የሚባል ፕሮጀክት አላችሁ፡፡ ምን ምን ሥራዎችን ታከናውኑበታላችሁ? ውጤታማነቱስ እንዴት ይገለፃል?

ዜናዬነህ፡- ‹‹ከፍታ ለወጣቶች›› ትልቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ ከዩኤስአይዲ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍና በሌሎች አጋሮች ድጋፍም የሚተገበር ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ዓላማው ወጣቶች የራሳቸውን ኢኮኖሚያዊ አቅም በመፍጠር ማኅበራዊ ተሳትፏቸውን ማሳደግ እንዲችሉ ማድረግ ነው፡፡ ወጣቶች በሁሉም መስክ የመሳተፍ እድል ቢያገኙ ሀገራቸውን ወደ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና መምራት ይችላሉ፡፡ ይህን ሐሳብ መሠረት በማድረግም ወጣቶችን ሁለገብ ለማድረግ እሠራን ነው፡፡ ‹‹ከፍታ ለወጣቶች›› የተቀረፀም ይህን ለማሳካት ነው፡፡ ሥራው የሚሠራው ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች  ጋር በመኾን ነው፡፡ ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የሚሠራ ነው፡፡ ወጣቶቹ በንቃት ተሳታፊ በመኾን የራሳቸውን መልካም ዕድል የሚፈጥሩበት ሥራ ነው፡፡ በውሳኔ ሰጭነትና አመራርነት ሁሉንም ነገር ተግባራዊ የሚያደርጉበት ፕሮግራም ነው፡፡

ፕሮግራሙ ሲታሰብ ወጣቶችን በማሳተፍ የተቀረፀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸው ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ አብዛኛው ከ15-29 ዕድሜ ያለ ወጣት እንዴት ማስተናገድ እንደሚቻል እና የወጣቶችን አቅም እንዴት መጠቀም እንደሚገባ፣ የወጣቶቹን የሥነ-ምሕዳር ተጠቃሚነት እንዴት ማመቻቸት ይቻላል? ለሀገሪቱ ዕድገትስ በምን መልኩ ይጠቅማሉ? ተብሎ ነው የአሜሪካን የልማት ተራድኦ ድርጅት በ2018 ጥናቱን አጠናቆ ይፋ ያደረገው፡፡ ይህ ጥናት አጠናቆ ይፋ ከኾነ በኋላ በ2021 እንዲተገብር ፀደቀ፡፡ ለዚህ ተግባራዊነት ከጎናችን ብዙ አጋር ድርጅቶች አሉ፡፡ ወደ ሰባት የሚኾኑ ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በ18 ከተሞች ላይ እየተገበሩ ይገኛሉ፡፡ ወደ ሦስት የሚኾኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም አሉ፡፡ በርካታ የግል ተቋማትም አብረው በአጋርነት ይሠራሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ‹‹ኤጋ›› የሚባለው የግል ተቋም የእኛን ተቋማዊ ብቃት በየጊዜው እየገመገመና እየለካ የትግበራ የፕሮጀክት አፈፃፀማችን የሚረዳን ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ ከአመራርና አስተዳደር አንስቶ የውስጥ አደረጃጀት እስከ ተቋማዊ ዘላቂነት ይፈትሸናል፡፡ ፕሮግራም አፈፃፀማችንን፣ የፋይናንስ አያያዛችንን፣ የሰው ኃይል ሃብት አስተዳደራችንን፣ የክትትልና ግምገማ የምርምር ሥራችንን፣ የእኛን የአመራር የማኔጅመት ሁኔታ በሙሉ ይገመግማሉ፡፡

በአጠቃላይ አጋሮቻችን ወጣቶች፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት፣ የውጩ ድርጅቶችና የመንግሥት ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ በጋራ በመጣመር ነው ‹‹ከፍታ ለወጣቶች›› ፕሮጀክትን እየተገበርን ያለነው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት አመርቂ ውጤት መጥተዋል፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ተጠቃሚ ኾነዋል፡፡

ግዮን፡- ማመስገን የምትፈልገው ተቋም ካለ? እንዲሁም ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥህ?

ዜናዬነህ፡- ማመስገን የምፈልገው በመጀመሪያ ወጣቶቻችንን ነው፡፡በመቀጠልም የድርጅቱን ሠራተኞች በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ እኛ በምንሠራቸው እያንዳንዱ ሥራ ውስጥ አጋዦቻችን (አጋሮቻችን) ኾነው ወጣቶቻችን ተጠቃሚ የኾኑበትን ሁኔታ በመፍጠራቸው ላመሠግናቸው እወዳለሁ፡፡ የድርጅቱን ‹‹ለኢትዮጵያ ወጣቶች መልካም ዕድል ማመቻቸት›› የሚል መሪቃል በመቀበል አብረው በመሥራታቸውም እንዲሁም የላቀ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ማመስገን የምፈልገው የግል ዘርፎችን ነው፡፡የተለያየ የመንግሥት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ከእኛ ጋር በጋራ የሚሠሩትን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ሚዲያዎችም መጥተው ስራዎቻችንን በመጎብኘታቸው የሠራነውን ሥራ ለሌሎች አስተማሪ በሆነ መልኩ በማቅረባቸው ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

በሌላ በኩል አዲስ ዓመት ያለፈውን ዓመትና አዲስ የሆነውን ዓመት የማሰላሰያ ጊዜ ነው፡፡ ይህን ታላቅ በዓል በህይወት ውስጥ ካሉ አሰፈላጊ ሰዎች ጋር ለአዳዲስ ጅምሮች እድሎችና በሕይወታችን ውስጥ ሙሉ አዲስ ምዕራፍ በደስታ የምናከብርበት ጊዜ ነው፡፡ አዲሱ ዓመት፣ በአዲስ ራዕይ፣ በአዲስ ጉልበት እና በአዲስ መንፈስ የምንገለጥበት ይሁን ማለት እፈልጋለሁ፡፡ በእውቀት ላይ ተመሥርተን በላቀ አስተዋፅኦ ተቋምን የምንመራበት እንዲኾን እንመኛለሁ፡፡ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የልማትና የብልፅግና ይሁንልን፡፡ ሀገራችን ወደ ላቀ ደረጃ እና ወደሚገባት ከፍታ የምትደርስበት ዓመትም ይሁንልን፡፡ዘላቂ ሰላም የምታገኝበት ዓመትም እንዲኾንም እመኛለሁ፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 215 ጳግሜ 2 / 2016 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በ2026 የዓለም ዋንጫ ላይ ለተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖች የሚጫወቱ ወንድማማቾች

የ2026 የፊፋ የዓለም ዋንጫ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ምርጥ ተጫዋቾችን...

ኢንፊኒቲ ለቤትና ለመኪና መግዣ ብድር እየሰጠ እንደሚገኝ አስታወቀ

ኢንፊኒቲ ኃላፊነቱ የተወሠነ መሠረታዊ የቁጠባ እና ብድር ኀብረት ሥራ...

የአዲሱ የወንጀል ህግ ስነ-ስርዓት የእርማት ስራዎች ሳይጠናቀቁ በሥራ ላይ እየዋለ ነው

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላለፉት 64 ዓመታት...

ናይጄሪያው ዩናይትድ ካፒታል በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የውጭ ኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድ አገኘ

​የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በሀገሪቱ የካፒታል ገበያ ታሪክ ለመጀመሪያ...