በኢንዶኔዥያ ሱላዌሲ ደሴት ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ከ500 በላይ የሚሆኑ ደግሞ መትረፋቸውን የአደጋ ጊዜ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
በታላድ ደሴቶች አውራጃ ከምትገኘው ሜሎንጉዌን ወደብ ወደ ሰሜን ሱላዌሲ ግዛት ዋና ከተማ ወደሆነችው ማናዶ ከተማ ተሳፋሪዎች ኪ ኤም ባርሴሎና 5 ተሳፍረው የነበረ ሲሆን እሁድ እለት ምሽት እሳቱ ከተነሳ በኋላ በመዝለል ህይወታቸውን አትርፈዋል።
በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የተሰራጨው ፎቶ እና ቪዲዮ፣ ከተቃጠለው ጀልባ ላይ ብርቱካናማ ነበልባል እና ጥቁር ጭስ ሲወጣ ያሳያል።በአብዛኛው የህይወት ኡድን ጃኬቶችን የለበሱ ሰዎች ባህር ውስጥ የዘለሉ ተሳፋሪዎች በፍርሃት ተውጠው ታይተዋል። በማናዶ የነፍስ አድን ኤጀንሲ የተለቀቀው ቪዲዮ የባህር ዳርቻ ጠባቂ መርከብ በጀልባው ላይ ውሃ ሲረጭ እና ጥቁር ጭስ ሲያወጣ ያሳያል።
የኢንዶኔዥያ ባለስልጣናት ቀደም ሲል በአደጋው አምስት ሰዎች መሞታቸውን ቢገልጹም በኋላ ላይ ሁለት ተሳፋሪዎች ሆስፒታል ውስጥ ከገቡ በኋላ በተደረገላቸው ህክምና ተርፈዋል። ሳንባው በባህር ውሃ የተሞላ የሁለት ወር ህጻን በህክምና እገዛ ህይወቱን ማትረፍ ተችሏል።
ከጀልባው ቢያንስ 568 ሰዎች መትረፋቸውን የብሄራዊ ፍለጋ እና አድን ኤጀንሲ ሰኞ እለት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። የባህር ዳርቻ ጠባቂ መርከብ፣ ስድስት የነፍስ አድን ሰራተኞች መርከቦች እና በርካታ በአየር የሚነፉ ጀልባዎች በነፍስ አድን ስራ ላይ ተሰማርተው እንደነበር የማናዶ የባህር ሃይል ጣቢያ ዋና አዛዥ ፍራንኪ ፓሱና ሲሆምቢንግ ለአሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ጀልባው የተመዘገበው 280 መንገደኞች እና 15 የበረራ ሰራተኞች ለማሳፈር ብቻ ነው። የባህር አደጋዎች በደቡብ ምስራቅ እስያ ወደ 17,000 የሚጠጉ ደሴቶች ባሉባት ሀገር በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ሲሆን አደጋዎቹም በዝቅተኛ የደህንነት ደረጃዎች ወይም በመጥፎ የአየር ሁኔታ ምክንያት ይደርሳሉ።
በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
