በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የስደት መንገዶች ላይ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 2025 ብቻ ቢያንስ 7,667 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ወይም የደረሱበት ሳይታወቅ እንደቀረ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም አቀፍ ፍልሰት ድርጅት (IOM) አስታውቋል።
ምንም እንኳን የሟቾች ቁጥር 9,200 ሰዎች ከሞቱበት የ2024 ዓመት ጋር ሲነፃፀር መጠነኛ ቅናሽ ቢያሳይም፣ ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር ግን ከዚህ እጅግ ሊበልጥ እንደሚችል ድርጅቱ ገልጿል።
ለዚህም በምክንያትነት የቀረበው የእርዳታ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ እየቀነሰ በመምጣቱ ብዙዎቹን አሳዛኝ ክስተቶች በሰነድ መዝግቦ መያዝ አለመቻሉ ነው።
እንደ አይ ኦ ኤም ሪፖርት፣ በሜዲትራኒያን ባሕር 2,200 ገደማ ሰዎች ሲሞቱ፣ ከምዕራብ አፍሪካ ወደ ካናሪ ደሴቶች በሚወስደው አደገኛ መንገድ ደግሞ 1,200 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
እጅግ ልብ የሚሰብረው ክስተት ደግሞ 42 አስከሬኖችን የያዙ ሦስት ጀልባዎች ከአፍሪካ ተነስተው አቅጣጫቸውን በመሳታቸው በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ እየተንሳፈፉ እስከ ብራዚል እና ካሪቢያን ደሴቶች የባሕር ዳርቻ ድረስ ተገኝተዋል።
በእስያ እና ከአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን በሚወስዱ መንገዶች ላይ ደግሞ በአብዛኛው ከአፍጋኒስታን የሚሰደዱ ሰዎችን ጨምሮ 4,000 ገደማ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።
