ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የስፔኑን አልሜሪያ ክለብ በከፊል ገዛ

Date:

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ዶሳንቶስ አቬሮ በስፔን ሁለተኛ ዲቪዥን የሚጫወተውን የአልሜሪያ ክለብ ሩብ (1/4ኛ) ድርሻ መግዛቱ ታውቋል። ታዋቂው የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የክለቡን 25 በመቶ ድርሻ በመግዛት አነስተኛ ባለድርሻ መሆኑ ተረጋግጧል።

በአሁኑ ወቅት የ41 ዓመት ጎልማሳ የሆነውና በሳውዲ አረቢያው አል ናስር እየተጫወተ የሚገኘው ሮናልዶ፣ ይህንን ድርሻ የገዛው CR7 ስፖርትስ ኢንቨስትመንትስ በተሰኘው አዲስ ኩባንያው አማካኝነት ነው።

የአልሜሪያ ክለብ ባለቤት በሆኑትና በሳውዲ አረቢያው ባለሀብት መሐመድ አል-ከሬጂ በሚመራው የኢንቨስትመንት ጥምረት ውስጥ የሮናልዶ መካተት፣ ለክለቡ ቀጣይ ዕድገት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ታምኖበታል።

ሮናልዶ ስለ ሁኔታው በሰጠው መግለጫ፤ ከሜዳ ውጭ በእግር ኳሱ ዓለም አስተዋጽኦ የማበርከት የቆየ ምኞት እንደነበረውና አልሜሪያ ደግሞ ጠንካራ መሠረትና የማደግ ዕድል ያለው ክለብ በመሆኑ ደስተኛ መሆኑን ገልጿል።

የክለቡ ፕሬዝዳንት አል-ከሬጂ በበኩላቸው፤ ሮናልዶ በስፔን እግር ኳስ ያለውን ሰፊ ልምድና ዕውቀት በመጠቀም የክለቡን አካዳሚና ዋና ቡድን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

አልሜሪያ በ1989 የተመሰረተ ክለብ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የውድድር ዘመኑ ሊጠናቀቅ 15 ጨዋታዎች እየቀሩት፣ ክለቡ ወደ መጀመሪያው ዲቪዚዮን (ላሊጋ) ለማደግ ጥረት እያደረገ ነው።

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በስፔን ለ9 ዓመታት መጫወቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በዓመት 177 ሚሊዮን ፓውንድ እየተከፈለው በእግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያው ቢሊየነር መሆን የቻለ ተጫዋች ነው።

ፖርቹጋላዊው ኮከብ በCR7 ስፖርትስ ኢንቨስትመንት ላይ መዋለ ንዋዩን በማፍሰስና አክሲዮኖችን በመግዛት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህም ለቀጣይ የሕይወት ጉዞው ትልቅ ምዕራፍ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ከጥቂት ወራት በፊትም ሮናልዶ ከእግር ኳስ ውጭ ሌላ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ለመቀላቀል መወሰኑ ይታወሳል። ይህም በስፔን የሚገኘውና የMMA (ድብልቅ ማርሻል አርት) ሻምፒዮና አዘጋጅ የሆነው WOW FC (Way of Warriors FC) የተባለውን ሊግ የባለአክሲዮንነት ድርሻ በመግዛት በፍልሚያ ስፖርቶች ላይ ትልቅ ኢንቨስትመንት ማድረጉ ነው።

ይህ ዜና ይፋ የተደረገው በWOW FC ሊግ እና በዩኤፍሲ (UFC) የላባ ክብደት (Featherweight) ሻምፒዮን በሆነው ኢሊያ ቶፑሪያ በኩል ነው።

ቶፑሪያም በዚህ ሊግ ውስጥ ከዋና ባለቤቶች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል። የሮናልዶ ወደ WOW FC መምጣት ለድርጅቱ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ የMMA ስፖርት ዓለም አቀፋዊ ዕድገት ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ድርድር እስኪጠናቀቅ ድረስ የተኩስ አቁሙ መራዘሙን አስታወቁ

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፓኪስታን ጥያቄ መሠረት ከኢራን ጋር የገቡትንየተኩስ...

ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ የሚውል የ40 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ተፈቀደ

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የልማት ክንፍ የሆነው ኢአይቢ ግሎባል (EIB...

ሃይንከን በአልኮል መጠኑ ጠንከር ያለ ቢራ ለኢትዮጵያ ገበያ አስተዋወቀ

ሃይንከን ኢትዮጵያ በእለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆነውን ዴሰፔራዶስ (Desperados)...