ቡልቻ ደመቅሳ ሰንበቶ

Date:

(1923 – 2017 ዓ.ም)

ታላቁ ኢትዮጵያዊ፣ በምጣኔ ሀብት ባለሙያነታቸው ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ያገለገሉት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ታህሣሥ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ስለ አቶ ቡልቻ በእንግሊዝኛ ቋንቋ አንድ የግለ-ታሪክ መጽሀፍ ታትሞ ለንባብ የበቃ ሲሆን በበርካታ መገናኛ ብዙሀንም አበርክቷቸው በጉልህ ተጽፏል፡፡ ለመኾኑ አቶ ቡልቻ ማን ናቸው? አስተዳደጋቸው እና የትምህርት ቆይታቸውስ ምን ይመሥላል? በኢትዮጵያ ፖለቲካ የነበራቸው አበርክቶስ እንዴት ይገለጻል? የሚለውን በተከታዩ ሐተታ መልስ ለመሥጠት እንሞክራለን፡፡ 

ትውልድ እና እድገታቸው

በምእራብ ወለጋ ዞን በቦጂ ብርመጂ ወረዳ በጊንቢ ዞን ከአባታቸው አቶ ደመቅሳ ሰንበቶ እና ከእናታቸው ነሲሴ ሰርዳ በ1923 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ አቶ ቡሌቻ ደመቅሳ የቤተሰቡ 4ኛ ልጅ እና ብቸኛ ወንድ ልጅ ናቸው፡፡ ክቡር አቶ ቡልቻ አባታቸውን በልጅነት በሞት ቢያጡም አጎታቸው ጎቡ ሰንበቶ እንደ አባት ሆነው የወንድማቸውን አደራ ተቀብለው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ አድርገውላቸዋል፡፡

የትምህርት ህይወታቸው

የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጊንቢ አድቬንቲስት እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኩየራ አድቬንቲስት ተምረዋል፡፡ በወቅቱ ምንም እንኳን ከፍተኛ ውጤት በማምጣት  ትምህርታቸውን ቢያጠናቅቁም ከመንግስት ትምህርት ቤት ተከታትለው ካጠናቀቁ ተማሪዎች ውጭ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመግባት እድል አይገኝም ነበር፡፡ 

ክቡር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ  ግን  የቀድሞ የዩንቨርሲቲ አስተዳዳሪዎችን ዶክሜንታቸውን በማሳየት እና በማናገር ተቀባይነትን አግኝተው ወደ አራት ኪሎ ዩንቨርሲቲ በመግባት የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በመከታተል በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ከፍተኛ ውጤት በማምጣትም ተመርቀዋል፡፡

ዩንቨርስቲው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ለተመረቁ 10 ተማሪዎች  መካከል አንዱ በመሆን ወደ አሜሪካ  በመሄድ  በሲራኪዩዝ  ዩንቨርሲቲ ውስጥ ተመድበው ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡

ትዳር እና ህይወት

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከቀድሞ ባለቤታቸው ገና የ18 አመት ወጣት እያሉ ነበር ከትዳር አጋራቸውና አዲስ አበባ ውስጥ የነርሲንግ ተማሪ የሆነችውን መንበረ ዱጉማ ጋር የተጋቡት፡፡ አቶ ቡልቻ እና መንበረ በ26 ዓመታቸው የአምስት ልጆች ወላጆች ነበሩ፡፡ ከሁለተኛ ባለቤታቸው ከሆነችው ወ/ሮ ሄለን ገ/እግዚያብሔር ጋር ለስራ ምክንያት ወደ ግብጽ ሀገር በሚመላለሱበት ወቅት ነበር የተገናኙት፡፡ አቶ ቡልቻ እና ወ/ሮ ሄለን አብረው በቆዩበት 50 የትዳር ዓመት አንድ ልጅን በመውለድ በአጠቃላይ የስድስት ልጆች አባት እንዲሁም አስራ አንድ የልጅ ልጅ አያት ሆነዋል፡፡ 

የሥራ ዘመን ታሪክ

ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በመምህርነት ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ በገንዘብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ በበጀት ዳይሬክተር እንዲሁም ምክትል የገንዘብ ሚኒስተር በመሆን  አገልግለዋል፡፡ በወቅቱም በቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ኃይለሥላሴ እጅግ የሚወደዱ እና ቅቡልነት ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ የደርግ መንግሥት ስልጣን ላይ ሊወጣ አከባቢ የፋይናንስ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱን ለቀው ወደ ሀገረ አሜሪካ ሄደው ነበር፡፡ ደርግ የሥልጣን መንበሩን  እንደ ተቆጣጠረ ወደ 60 የሚጠጉ ባለስልጣናትን እና ምሁራንን ሲገድል የሳቸው ባልደረቦችን በማጣታቸው በእጅጉን ያዝናሉ፡፡ በዩኤን ዲፒ እንዲሁም በአለም ባንክ 20 አፍሪካ ሀገራትን ወክለው ሰርተዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት አበርክቶ

ከደርግ ውድቀት በኋላ ከ17 አመት የውጭ ሀገር ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ቀጥለዋል፡፡ ክቡር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከምጣኔ ሀብት አበርክቷቸው አዋሽ ባንክ እንዲቋቋም እና አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የባንኩ መስራችና ፕሬዚዳንት በመሆን ረዘም ላለ ጊዜ ካለ ክፍያ ሰርተዋል፡፡ በተጨማሪም የባንኩ ቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል፡፡ የራሳቸውን አስተዋጽኦም አበርክተዋል፡፡

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በምጣኔ ሃብት ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ስጦታ ተበረክቶላቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማህበር በጋራ ባዘጋጁት ሥነ ስርዓት ላይ ለአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ለገጣፎ በሚገኘው በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝተው ስጦታ አበርክተውላቸዋል፡፡ ስጦታው የተበረከተላቸው ለሀገራቸው በምጣኔ ሃብት ዘርፍ ላበረከቱላት የረዥም ዘመን አገልግሎት ነው፡፡ ሰኔ 25 2014 ነበር እውቅና ያገኙት፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርስነት የሚያዝ የልዩ ታሪካዊ ሁነቶች ማስታወሻ የወርቅ ሳንቲም በመሸለም የወርቅ ካባም አልብሷቸዋል፡፡ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ  ደግሞ የምስጋና የምስክር ወረቀት እና የወርቅ ሜዳሊያ አበርክቶላቸዋል፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው ፣ የአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ባለቤት ወይዘሮ ሔለን ገብረእግዚአብሔርና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የፖለቲካ ታሪክ

በሀገራችን ዲሞክራሲ እንዲስፋፋ በፖለቲካው ዓለም ተሰማርተው የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ እንዲሁም የኦሮሞ ኮንግረስ ፓርቲ ውስጥ በመሳተፍ እና ምርጫ በመወዳደር  አሸንፈው ፓርላማ በመግባት የወቅቱ ጠቅላይ ሚንስተር የነበሩትን አቶ መለስ ዜናዊን በመተቸትና ሀሳባቸውን በነጻነት በመሰንዘር ይታወሳሉ፡፡

አቶ ቡልቻ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ታህሣሥ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲኾን የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም ጥር 4 ቀን 2017 ዓ.ም በጴጥሮስ ወጳውሎስ ተፈጽሟል፡፡

የቅርብ ሰዎች አስተያየት

‹‹ሀገርን መውደድ፣ ማንነትን ማክበር፣ ሀቀኝነት፣ ሰው ወዳድነት፡ ሩህሩህነት የእርሳቸው መገለጫ ጭምር ነው››

ወ/ሮ ሄለን ገ/እግዚአብሔር (ባለቤት)

እኔ ግብጽ ሀገር ሆኜ ኢትዮጵያን ኤምባሲ ውስጥ እሰራ ነበር፡፡ እርሱ ደግሞ ካይሮ ለኮንፈረንስ  ከመጡ ልኡኳን መካከል አንዱ ነበር፡፡ ከእህትሽ መልእክት መጥቶልሻል ከኢትዮጵያ አለኝ፡፡   በወቅቱ በጣም ደስ አለኝ፡፡ ምክንያቱም አለም አቀፍ የስልክ ልውውጥ ስላልነበረ እጅግ በጣም ደስ አለኝ፡፡ የመጣልኝ መልእክት ለመቀበል ቸኮልኩኝ፡፡ እሱ ከስብሰባ እንደጨረሱ ‹‹…ቡና እንጠጣ›› አለኝ፡፡ እሺ ብዬ ቡና እየጠጣን ‹‹…ስለ አንቺ ብዙ የሰማሁት ጥሩ ነገር አለ›› አለኝ፡፡ ቀጥሎ ስለ እራሴ ልንገርሽ አለኝ፡፡ እኔ ደግሞ በልቤ እዩ ሁሉ ምን ያስፈልጋል እያልኩ አዳመጥኩት፡፡ ስለ ራሱ ከነገረኝ በኋላ መልእክት አልመጣልሽም አለኝ፡፡ ትውውቃችንን እንዲህ ጀምረን አብረን በብዙ ውጣውረድ ውስጥ አልፈን 50 የትዳር አመታትን አብረን ኖረናል፡፡ የፓርላማ አባል ሆኖ ላመነበት ሀሳብ ሲሟገት ነበር፡፡ እኔም እንደ ባለቤት በምችለው ሁሉ ከአጠገቡ ሳልለይ እረዳው ነበር፡፡

‹‹ሰው በመርዳት ያምናል ፡፡ የተቸገረ ሰው ካለ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋል››

ብስራት ቡልቻ (ልጅ)

አባቴ እራሱንም ለመደገፍም ይሁን ቤተሰብን ለመደገፍ እያስተማረ መማር ነበረበት፡፡ እንግሊዘኛ ቋንቋ ቶሎ ስለለመደ ከሚሲዮኖች ጋር በማስተርጎም ሥራ እየሰራ ትንሽ ደሞዝ እያገኘ እራሱን እየደገፈ ያስተምርም ነበር፡፡ አባቴ ሀቅ የሚናገር ቅጥፈትን የሚቃወም እውነት ተናጋሪ ነው፡፡ አባቴ ውጭ ሀገር ሆኖ የረር ተራራን ማየት ሁሌም ይናፍቀው ነበር፡፡

አቶ ለይኩን ብርሃኑ

የቀድሞ የብሄራዊ ባንክ ገዥ እና የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት የነበሩ

በአካባቢያችን እንደ አርአያ ከሚታዩና እና ከተማሩ  ሰዎች መካከል አቶ ይልማ ዴሬሳ እና አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ናቸው፡፡ እኛ ልጅ ሆነን እነርሱን እንደ አርአያ እያየን ነው ያደግነው፡፡  ታንዛኒያ ሀገር ለአንድ ስብሰባ ሄጄ  ስብሰባችንን እንደ ጨረስን  ቡና እየጠጣን አንድ ኢትዮጵያዊ እኮ አለ አለን፡፡ አዎ ብዙ ኢትዮጵያዊያን እኮ እዚህ ሊኖሩ ይችላሉ አልኩት፡፡ ቀበል አለኝ እና አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የሚባል ሰው ታውቃለህ አለኝ ፡፡ በመገረም እርሳቸውን ከልጅነት ጀምሮ በዝና ነው የማውቀው አልኩት፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ አቶ ቡልቻን በአካል ያወኩት ያኔ ነው፡፡ ያኔ የጀመረው ግንኙነታችን እስካሁን ድረስ የተለያዩ ስራዎችን አብረን በመስራት በተጨማሪም ቤተሰብ ሆነን ቀጥለናል፡፡  ያገራችን ኢኮኖሚ እንዲያድግ የራሱን አስተዋጽኦ  አበርክቷል፡፡ በተለይ በግሉ ዘርፍ ባንኮች ብዙም ባልነበሩበት ወቅት እርሳቸው ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን አዋሽ ባንክ እንዲከፈት እና እንዲስፋፋ የራሱን አስተዋፆ አበርክቷል፡፡

ሶፍያ ይልማ

ቤተሰብ

በወቅቱ አባቴ የገንዘብ ሚኒስቴርን ዘመናዊ እንዲሆን የተማሩ ሰዎችን ከያሉበት እያሰባሰበ  ነበር፡፡ ከነዚህ ሰዎች መካከል አቶ ቡልቻ ደመቅሳ አንዱ ነበር፡፡ የገንዘብ  ሚኒስቴር ዘመናዊ እንዲሆን መስሪያ ቤቱን ባገለገሉበት ወቅት የራሳቸውን አስተዋጽኦ አሳርፈዋል፡፡

ወ/ሮ እሌኒ ከበደ

የቀድሞ ፀሃፊ

አቶ ቡልቻ እና እኔ ትውውቃችን  ገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ፀሃፊ በነበርኩበት ወቅት ነበር፡፡ ያኔ እንደ እርሳቸው እንደ አለቃም እንደ ቤተሰብም ሆነን አብረን ሰርተን ነበር፡፡ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በወቅቱ በነበሩት ንጉስ እጅግ ተቀባይነት ያላቸው እና ገንዘብ ካለ አግባብ እንዲወጣ የማይፈቅዱ ስራቸውን በአግባቡ የሚሰሩ እና ሰው አክባሪ ሰው ናቸው፡፡ የዛን ጊዜ የጀመርነው  ቤተሰባዊነት እስከ አሁን ድረስ አብረን ዘልቀናል፡፡ ጥሩ ቤተሰቦቼ ናቸው፤ በሰርግም በለቅሶም ቢሆን ከነ ሙሉ ቤተሰባቸው እንጠያየቃለን፡፡

ሉሲ ገ/እግዚአበሔር

ቤተሰብ

ጋሼ ሀገሩን የሚወድ ሰው አክባሪ ባህሉን የመጣበትን ማህበረሰብ የሚያከብር እና የሚያስከብር ሀሳብ ያለው ሰው ነው፡፡ እኔም ልጅ እያለው ትምህርታችን ላይ እንድንበረታ ጠንክረን እንድናጠና የራሱን አስተዋፆ  አበርክቷል፡፡ እኔም አውን አስተማሪ ነኝ፡፡ እሱ አንብቡ አጥኑ ስለሚል ያኔ የጀመርኩት ጥናት አስተማሪነትን እንድወደው እና እንድሰራበት የጋሼ አስተዋፆ ቀላል አይደለም፡፡

ኢ/ር ተረፈ ራስ ወርቅ

ጓደኛ

አቶ ቡልቻ ክርክር የሚወድ ያለውን ሀሳብ በስርኣት የሚያስረዳ ሰው ነው፡፡የገዳ ስርኣትን እንድማር እና እናዳውቅ ለመጀመርያ ጊዜ ያስተማረኝ አቶ ቡልቻ ነበር፡፡

ኢ/ር እሸቱ አበበ

ጓደኛ

አቶ ቡልቻ ወለጋ ጊንቢ ተወልዶ ይደግ እንጂ የወለጋ ልጅ ብቻ አይደለም የመላው ኢትዮጵያዊ ልጅ ነው፡፡ሁሌ ሳስበው ኢትዮጵያ በሚለው ሀሳብ ነው ፡፡ ሁሉን ነገር ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን የሚል ሀሳብ ነው ያለው፡፡

አቶ ሙላቱ ገመቹ

የኦሮሞ ፌደራሊስት  ኮንግረስ ፓርቲ ም/ሰብሳቢ

የኦሮሞ ፓርቲዎች ባልተስፋፉበት ወቅት አቶ ቡልቻ ፓርቲ አቋቁመው ለኦሮሞ ህዝብ ድምፅ ለመሆን ጥረዋል፡፡ ፓርላማ ውስጥም በመግባት ሃሳባቸውን በነጻነት ሲናገሩ ልክ ያልሆነን ሀሳብ ሲተቹ ነው የማውቃቸው፡፡ አቶ ቡልቻ እስከአሁን ድረስ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ፓርቲያችንን እየደገፉ እና እየረዱ ይገኛሉ፡፡ እኔ ሰው ወዳድና እውነት ተናጋሪ ከምላቸው ሰዎች መካካል አንዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ናቸው፡፡ የአዋሽ ባንክ ሲቋቋም እርሳቸው ካለ ክፍያ ረዘም ላለ ጊዜ በነጻ በማገልገል ባንኩ አሁን ያለበትን አቋም እንዲይዝ የራሳቸውን አበርክቶ አበርክተዋል፡፡ ይህ ከፖለቲካው ባሻግር ለሀገራችን ምጣኔ ሀብት የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

***

አቶ ቡልቻ በግዮን መጽሔት ምን ብለው ነበር?

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ተደርጎ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት በመጡበት ወቅት ከግዮን መጽሔት ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገው ነበር፡፡ ከቆይታቸው መሓል የተወሰነውን እርሳቸውን ለማሰብ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡- 

አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ካላቸው የፖለቲካ ልምድ አንፃር የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ይወጣሉ ብለው ያምናሉ?

አቶ ቡልቻ፡- በቅርቡ የሚያውቁት ሲያወሩ እንደ ሰማሁት ከሆነ ችሎታና ብቃቱ ሊኖረው ይችላል፡፡ ግን እኛ የምናወራው በፖሊሲ ጉዳይ ከማን ጋር ነው የሚሰራው? የማንን ሃሳብና እቅድ ነው የሚያስፈፅመው? ስራ ላይ የሚያውለውና የሚያምንበት ጉዳይስ ምንድነው? የሚሉት ጉዳዮች ናቸው ወሳኞቹ፡፡ ዶክተር አብይ የኢህአዴግ አመራር እስከሆነ ድረስ ማንኛውም ነገር የኢህአዴግ ነው ማለት ነው፡፡ ለውጥ አለ ብሎ በድፍረት ለመናገር የሚቻለው ለውጡ ስር ነቀልና ፖሊሲውና ስትራቴጂው ሲቀየር ብቻ ነው፡፡

ለውጡ እንዲመጣ ከተፈለገ ዶክተር አብይ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታ እንደተዛወሩ በፍጥነት መስራት አለባቸው ብለው የሚያምኗቸው ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?

አቶ ቡልቻ፡- በዋነኝነት የሚጠበቀው ወደ ህዝቡ ሰላምን ማምጣት ነው፡፡ ሰላም የሚፈጠረው ኢህአዴግ ለዘመናት ሲያደርገው እንደነበረው በግድ፣ በጉልበት፣ ሳይሆን በሰላማዊ ሥርአት ሰላምን ለዘለቄታው ለህዝቡ ማምጣት ይኖርበታል፡፡ በየሳምንቱና በየወሩ ህዝቡ ሆ ብሎ አደባባይ የሚወጣበትና የሚገደልበት፣ የሚደበደብበት ሁኔታ ከዚህ በኋላ እንዳይፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁልጊዜ በጉልበትና በሃይል እየተገዛ መኖር መሮታል፡፡ ይሄን ተከትለው የተነሱ የነፃነት ጥያቄዎች ናቸው አሁን ያየነውን ችግር የፈጠሩት፡፡ ኢህአዴግ ሁሌም ቢሆን የህዝቡን ጥያቄ ለመስማት ሳይፈልግ ቢቆይም አልሰማም የሚባልበት ጊዜ ላይ አይደለም አሁን ያለው፡፡

የዶክተር አብይ ምርጫ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመላ ኦሮሚያ የተስፋፋውን የኦሮሞ ወጣቶች አመፅ ለማብረድና በተዛማጅ የሌሎች ሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት ታስቦ የተደረገ ምርጫ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፤እርስዎ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ ቡልቻ፡- እኔ እንግዲህ ኢህአዴግ አይደለሁም ከምን አንፃር እንደመረጡት አላውቅም ነገር ግን በተወሰነ መልኩ እኔም ሰው እንደሚያስበው አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን አማራውም ሆነ ሌላው ህዝብ ዘንድ ብትሄድ ብዙ ሰው ደስተኛ አይደለም፤ ስለዚህ የእሱ መመረጥ ይሄንን ሁሉ ነገር ያስረሳል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንደ ተባለው የሚነሱትንም ተቃውሞዎች ለጊዜውም ቢሆን ጋብ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 221 ጥር 10 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንግሊዝ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ አገደች

የእንግሊዝ መንግሥት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች...

አሜሪካ 300 ሚሊዮን ዶላር ለኢራን ልትሰጥ ነው መባሉን ትራምፕ አስተባበሉ

አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ከደረሱ በኋላ አሜሪካ እና አጋሮቿ...

ደህና ሁን! ሰሜ…ስሜ!

“ከልጅነታችን ጀምሮ ጥበብ አገናኝታን ፣ በግሽ አባይ የባህል ቡድን...

✌️ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው

✌️ከዕድሜው የገዘፈው የታሪኩ ጁዋር ጀግናውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር የጀግንነት...