(1937 – 2017 ዓ.ም)
ፕሮፌሰር በፍቃዱ ደግፌ ከእናታቸው ወ/ሮ ጌጤ ብሩ እና ከአባታቸው አቶ ደግፌ ሆርዶፋ ነሐሴ 12 ቀን 1937 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በቀድሞው አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ተወለዱ። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በቀራኒዮ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ቄስ ትምህርት ቤት በየኔታ እፎዬ ሲራክ አማካኝነት ፊደል ቆጥረው ዳዊትና ወንጌልንም ተምረዋል።
በመቀጠልም ዘመናዊ ትምህርትን በአጋጣሚ በጀመሩበት በወንዶች የክርስቲያን ማሰልጠኛ ት/ቤትና በልዑል ወሰን ሰገድ ት/ቤት የመጀመሪያና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ተከታትለዋል።
ቀጥለውም የከፍተኛ ትምህርታቸውን በመከታተል ከዓለማያ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ በሌላ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል። ከዚያም የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በአሜሪካን ሀገር ቴነሲ ከሚገኘው ቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።
ፕሮፌሰር በፍቃዱ በሥራው ዓለም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ20 ዓመታት በማስተማርና በምርምር መስክ በመስራት እስከ ተባባሪ ፕሮፌሰርነት ደረጃ ደርሰው በ1984 ዓ.ም በወቅቱ በነበረው መንግስት ከተባረሩት 42 መምህራን አንዱ ናቸው። እኤአ 1974 እስከ 1991 ዓ.ም በተለያዩ በአፍሪካ ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተጋባዥ ፕሮፌሰር External Examiner ሆነው አገልግለዋል። በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በኢኮኖሚ ተመራማሪነት በማገልገል እኤአ ከ1994 እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ በየዓመቱ ይወጡ የነበሩት ዓመታዊ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ሪፖርቶች የቡድን መሪና የሪፖርቶቹም ዋና ጸሐፊ ሆነው አገልግለዋል። በዓለማቀፍ የገንዘብ ድርጅት እና በዓለም ባንክም ውስጥ የፖሊሲ ተመራማሪ ሆነው አገልግለዋል።
ፕሮፌሰር በፍቃዱ ደግፌ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚከስ ማኅበርን ከቅርብ ወዳጃቸው ዶ/ር እሸቱ ጮሌ ጋር በመሆን በመመስረትና የማኅበሩም ሶስተኛ ፕሬዝደንት ሆነው ለሁለት የምርጫ ጊዜያት አገልግለዋል።
የሰብዓዊ መብት ጉባኤንም ከመስራቾቹ አንዱ በመሆን በቦርድ አባልነትና በፋይናንስ ኃላፊነት አገልግለዋል። ከራእይ 2020 ጠንሳሾች መካከልም አንዱ ነበሩ።
በ1997 ዓ.ም የቀስተ ደመና ፓርቲን ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ዶ/ር ቆንጅት ፈቃደ፣ ዶ/ር ሺመልስ ተ/ጻዲቅና ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር በመሆን አቋቁመው ፓርቲው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲን ከመሰረቱ ፓርቲዎች አንዱ እንዲሆን ያስቻሉ ሲሆን ቅንጅትን ወክለው በወረዳ 24 ተወዳድረው ለተወካዮች ምክርቤት አባልነት ተመርጠዋል። በጥቅምት ወር 1998 ዓ.ም የቅንጅት አመራሮች ሲታሰሩም ለ21 ወራት በእስር ቤት አሳልፈዋል።
ከእስር ቤት ከወጡም በኋላም በአሜሪካን ሀገር በኒው ስኩል ፎር ሶሻል ሪሰርች ውስጥ የሪሰርች ፌሎው ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው ወደሀገራቸው ተመልሰዋል።
በተለያዩ የውጪ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች በመምህርነትና በሶስተኛ ዲግሪ ምርምር አማካሪነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ በሀገሪቱ አዲሱ ለውጥ ሲመጣ በቀድሞው መንግስት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በግፍ ተባረው የነበሩ ምሁራን ተመልሰው እንዲያስተምሩ የቀረበውን ጥሪ ተቀብለው ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በማስተማርና በማማከር አሳልፈዋል።
በ2013 ዓ.ም በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫም ኢዜማ ፓርቲን ወክለው በወረዳ 24 ምርጫ ክልል ተወዳድረዋል።
ፕሮፌሰር በፈቃዱ ደግፌ በስራ ዘመናቸው በርካታ የምርምር ጽሑፎችን ያሳተሙና ሲሆን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበርም ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅናን አግኝተዋል። ለስኬት የበቁ በርካታ ተማሪዎችንም አስተምረዋል፣ አማክረዋል።
ፕሮፌሰር በፈቃዱ ደግፌ ከወ/ሮ ዓለምጸሐይ አስፋው ጋር በ1979 ዓ.ም ጋብቻ መስርተው ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ለ38 ዓመታት በፍቅር የኖሩ ሲኾን የአንዲት ሴት ልጅ አባትም ናቸው።
በመኖሪያ አካባቢያቸው የሰፈሩ አድባርና ትልቁንም ትንሹንም አከባሪ የነበሩት ፕሮፌሰር በፍቃዱ ደግፌ ባደረባቸው ህመም በህከምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ79 ዓመታቸው ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም በቀራኒዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡
ፕሮፌሰር በፈቃዱ ደግፌ በዕንቁ መጽሔት ምን አሉ?
በቅርቡ በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም የተለዩን አንጋፋው ኢኮኖሚስ ፕሮፌሰር በፈቃዱ ደግፌ፣ ከዓመታት በፊት ለንባብ ትበቃ በነበረችው ዕንቁ መጽሔት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ ሰፋ ያለ ቆይታ አድርገው ነበር፡፡ እኛም ከዚያ ሰፊ የቃለ ምልልስ ክፍላቸው የተወሰነው መርጠን ወደኋላ ልናስታውሳቸው መርጠናል፡፡
እድገት ካለና በተለይም እንደ አገራችን ባለ ሁለት አሐዝ እድገት እየተመዘገበ የሕዝብ ኑሮ ካልተሻሻለ ምኑን ነው እድገት አለ የሚባለው?
ፕ/ር በፈቃዱ፡- እንዳልኩህ ለኑሮ መሻሻል እድገት የግድ ቢልም እድገት ሁሉ ኑሮ ያሻሽላል ማለት አይደለም፡፡ የእኛ አገር ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ የአገራችን ኢኮኖሚ አድጓል፡፡ 11 በመቶም ይሁን 20 በመቶም ይሁን አድጓል፡፡ ከቁጥሩ ችግር የለኝም፡፡ አይደለምም ብዬ አልከራከርም፡፡ የት እንደሚያደርሰኝ ስለማውቅ፡፡ አይዞህ አንተን ፈገግ ወዳሰኘህ አይደለም የሚያደርሰኝ፡፡ 11 በመቶ አይደለም ያደገው ብልና ታዲያ በስንት ነው ያደገው ብባል በዚህን ያህል ነው ለማለት በቂ መረጃ ስለሌለኝ ነው፡፡
ታዲያ ኢኮኖሚው አድጓል ካልን ያደገው ምንድነው ብለህ ስትጠይቅ ሁለት ነገር ሆኖ ታገኛለህ፡፡ አንዱ ለእድገት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶች አድገዋል፡፡ ግብአቶችን ወደ አምራች፣ ምርትን ወደ ሸማች የሚያደርስ መንገድ ተሠርቷል፡፡ ለማምረቻ እጅግ አስፈላጊ የሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል በከፍተኛ ደረጃ መንጭቷል፡፡ ምርት እንዲያድግና የተመረተውም ለበላተኛው እንዲደርስ የሚያስችሉ የአገልግሎት ተግባራት ተመንድገዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችና ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ በነገራችን ላይ ዛሬ ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች ብዛት እኔ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ዘመን ከነበሩት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በቁጥር ሳይበልጥ ይቀራል ብለህ ነው?
ሁለተኛው የኢህአዴግ በረከት ፍላጎትን ማሳደጉ ነው፡፡ ኢኮኖሚን ለማሳደግ ገበያ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ እንደኛ ኋላቀር በሆኑ ኢኮኖሚዎች ትኩረት መደረግ ያለበት ቁሳዊ ምርቶች ላይ ነው፡፡ ይኽም ግብርናና ኢንዱስትሪ ማለት ነው፡፡ ለነዚህ ምርቶች የእድገት ሞተራቸው ፍላጎት ነው፡፡ የተመረተ ካልተሸጠ እድገት አይኖርም፡፡ አምራች ተጨማሪ የሚያመርተው ያመረተው ሲሸጥ ነው፡፡ ለዚህም ገበያ ያስፈልጋል፡፡ በኢህአዴግ ዘመን የሃገር ውስጥ ሸማችና የውጪ ገዢዎች ቁጥር በርክቷል፡፡ ለመሸመት የሚፈልጉትም መጠን ጨምሯል፡፡ እነዚህ የኢሕአዴግ ትልቅ አበርክቶቶች ናቸው፡፡ ለዚህ ሥራው ኢህአዴግን የዛሬው ብቻ ሳይሆን መጪውም ትውልድ ይመርቀዋል፡፡ ኢህአዴግን ለሚተካ የፖለቲካ ድርጅትም ትልቅ ፈተና ይሆናል፡፡ ኢህአዴግ እንኳን ይህን አደረገ፤ እሱ ምን ሠራ እንዳይባል፡፡
ይሄ እንግዲህ ጠንካራ ጎኑ ነው፡፡ ኢኮኖሚ ሁለት ገፅታዎች ናቸው ያሉት፡፡ አንዱ ገፅታ ፍላጎት ነው፡፡ ከላይ የጠቋቆምኳቸው ግንባታዎች ሲካሄዱና ሌሎች ተጓዳኝ ተግባራቱ ሲከናወኑ ፍላጎትን አሳድገዋል፡፡ ሰዎች ተቀጥረዋል፡፡ ደመወዝ ተከፍሏል፡፡ ይህ ገበያ ወጥቷል፡፡ ይህ ነው ፍላጎት፡፡ ሁለተኛው ገፅታ አቅርቦት ነው፡፡ የሰከነና የተረጋጋ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ፍላጎትና አቅርቦት መስተካከል አለባቸው፡፡ መስተካከል አለመስተካከላቸውን የምታውቀውና የምትለካው በገበያ ዋጋ ነው፡፡ አቅርቦት ከፍላጎት ከበለጠ ዋጋ ይወርዳል፡፡ አቅርቦት ከፍላጎት ካነሰ ዋጋ ይነሳል፡፡ ዝበቱ ከፍተኛ ከሆነ ዋጋ በጣም ይሰቀላል ወይም ይወድቃል፡፡ እኩል ከሆኑ ዋጋ ይረጋል፡፡
በኛ ሃገር ችግር የተፈጠረው የተገነቡትን መሠረተ ልማቶች ተጠቅመን ለአገርም ለውጪም የሚሆን ምርት በብዛት አለማምረታቸን ነው፡፡ ለአምራች በጣም የተመቻቸ ሁኔታ ቢኖርም አልተጠቀምንበትም፡፡ ገበያው አልረካም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ያደገና እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚ ችግር ያስከተለው፡፡
ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ የምግብ እህል አምራች ገበሬና ወደ ዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልግ ባለኃብት ያልረካ ፍላጎት በመኖሩ ቢያመርት ጥሩ ገበያ እንዳለው ያውቃል፡፡ የአምራች ምኞቱ ብዙ አምርቶ ብዙ ገንዘብ አግኝቶ ሀብታም መሆን ነው፡፡ የምግብ እህሎችን በብዛት ለማምረት የሚያስችል ብልሀትም፤ መሣሪያም፤ መሬትም፤ አቅምም አለን፡፡ ታዲያ ምን ችግር አጋጠመ? የችግሩን ምንነት ነው እንጂ ያላወቅንለት ችግርማ ቢኖርበት ነው ገበሬ ያላመረተው፡፡ ለምን አምርቶ እንዳያበላንና እሱም እንዳይከብር ተደረገ?
በአጭሩ ስትገመግመው ኢህአዴግ ገንዘብ ያለው በላተኛ ፈጥሮና ወደ ገበያ አሰማርቶ (እጅግ በጣም ሰናይ ተግባር) የሚሸምተውን አሳጣው (እጅግ በጣም እኩይ ተግባር)፡፡ የእድገቱ ውጤት ወይም ትርፍ የዋጋ ንረት ሆነ፡፡ ይህም በሕዝብ ላይ ትልቅ ጉዳት አደረሰ፡፡ ድኽነት አደገ፡፡ በተለይ የከተሜው፡፡ በኔ እይታ ይህ ነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዛሬ ያለበት ሁኔታ፡፡
የኑሮ ውድነት የመጣው ከምርት እጥረት ሳይሆን ገንዘብ ስለበዛ ነው የሚባለውስ?
ፕ/ር በፈቃዱ፡- በዚህ በኩል ብዙ ብዙ ይባላል፡፡ የንግድ ሥርዓቱ ኋላ ቀር በመሆኑ ነው ይባላል፡፡ ገበሬው አዝመራውን ውድማው ላይ እያለ መሸጥ አቁሟል ይባላል፡፡ በሞባይል የዋጋውን ሂደት እየተከታተለ ነው ይባላል፡፡ የዓለም የምግብ ዋጋ ስለጨመረ ነው ይባላል፡፡ ነዳጅ ስለጨመረ ነው ይባላል፡፡ ገንዘብ ስለበዛ ነው ይባላል፡፡ አልሰማሁም እንጂ የእናቴ ቀሚስ ስለጠለፈኝ ነውም ሳይባል አይቀርም፡፡ አሁን ለያዘን አባዜ እነዚህና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ምክንያቶች ውሃ እንደማይቋጥሩ ለአቅመ ኢኮኖሚክስ የደረሰ ሁሉ የሚያውቀው ነው፡፡ ሕዝቡም ያውቃል፡፡ ሕዝብ እንደሚያውቅ ፖለቲከኞችም ያውቃሉ፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ነገር የሥርዓቱ ደጋፊዎችና ተጠቃሚዎች እውነቱን እየሸፋፈኑ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ሥርዓቱን ለአደጋ ማጋለጣቸው ነው፡፡
መልሰን መላልሰን መገንዘብ ያለብን የምግብ ዋጋ የናረው በቂ ስለማናመርት ነው፡፡ ይኸው ነው ችግሩ፡፡ ሌላ ምንም ችግር የለንም፡፡ የቀረው ሰበብ ነው፡፡ የገንዘብ መብዛት የፈላጊውን ብዛትና የሚፈለገውን መጠን ይጨምራል፡፡ ይሄ የሚደገፍ ነገር ነው፡፡ በተለይም ሠርቶ ለመብላት የሚፈልግ ግን የሚያሠራው ያጣ ጎበዝ በሞላበት፤ ታርሶ ምርት ሊሰጥ የሚችል ግን ጦም አደር መሬት ባለበት፤ ምርትን ሊያሳድግ የሚያስችል ብልሐት በሞላበት አገር፡፡ ሊሰመርበት የሚገባው የዋጋ ንረቱ የመነጨውና የሚገፋው ብዙ ሰው ገንዘብ ባገኘና ባገኘው ገንዘብ ሊሸምት እህል በረንዳ ሲወጣ የሚፈልገውን እህል በሚፈልገው መጠን ባለማግኘቱ ነው፡፡ ይሄ ዛሬ ሥራ ሠርቶ ገንዘብ ያገኘ፣ ሥራ ባይሠራም ምግብ መፈለጉ አይቀርም፡፡ ጉዳዩ የሕልውና ነገር ነው፡፡ ገንዘብን በመቀነስ ሠርቶ በሚያገኘው ገንዘብ የመብላት ዕድል ከነፈግኸው ለምኖ ወይም ሰርቆ ከባሰም ዘርፎ መብላቱ አይቀርም፡፡ የቱ እንደሚሻል ምርጫው ያንተ ነው፡፡
ምርት ለማሳደግ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ብዙ ብዙ እንቀባጥራለን፡፡ የማምረት አቅም አለን፡፡ የማምረት ፍላጎትም አለ፡፡ የተመረተውን የመሸመት ፍላጎትም አለን፡፡ ታዲያ ተጨማሪ ለማምረት ለምን ተከለከልን ነው ጥያቄው፡፡ ማን ከለከለ እንዳትል፤ ባይከለከል ኖሮ ገበሬው በገፍ አምርቶ፤ ራሱንም ጠቅሞ፤ አገሩንም፣ ወገኑንም ከችጋር ታድጎ፤ መስተዳድሩንም ይጠቅም ነበር፡፡ የምግብ እህል ዋጋ እንደዚህ ተሰቅሎ ቢከለከል ነው እንጂ ባይከለከል ብዙ ይመረት ነበር፡፡ መከልከል ማለት ፊት ለፊት አታምርት ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ ብዙ ስልቶችም አሉት፡፡ ግን አሁን በሥራው ላይ ያለ ገበሬና ወደዘርፉ ለመግባት የሚችልና የሚፈልግ አምራች ላይ ማዕቀብ ተጥሏል፡፡ ሌላ ምስጢር የለውም፡፡
ከዚህም ተጨማሪ ችግር አለ፡፡ የኢትዮጵያ በላተኛ የሚወዳደረው እርስ በርሱ ብቻ ሳይሆን ከውጪ ገዥዎችም ጋር ነው፡፡ ምግብ እንጀራን ጨምሮ በብስልና በጥሬ ወደ ውጪ በገፍ ይላካል፡፡ የውጪ ነጋዴዎች እህል የሚሸምቱት ከገበያ ሳይሆን በየገበሬው ቤት እየሄዱ ነው፡፡ ይህ ምስጢር አይደለም፡፡ ምናልባትም ከገበያ ሲገዙ አላስፈላጊ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩና ወደማይፈለግ አቅጣጫ እንዳያመሩ ታስቦ ይሆናል፡፡ ፍየል፤ በግ፤ በሬ በቁማቸውና ሥጋቸውም በልዩ ቄራዎች ተዘጋጅቶ ወደ አረብ አገሮች ይጫናል፡፡ ይህ ሁሉ ምስጢር አይደለም፡፡
ኢትዮጵያዊው በላተኛ ከነዚህ ገዥዎች ጋር መወዳደር አይችልም፡፡ መስተዳድሩ በአንድ በኩል ኢትዮጵያዊውን አምራች ከምርት ተግባሩ እያፈናቀለ፤ እየገደበና መቅኖ እያሳጣ በሌላ በኩል በላተኛውን በቂ ምርት በሌለበት ሁኔታ ለማይችለው ውድድር እያጋለጠ ህዝቡን ለችግርና ለችጋር አሳልፎ መስጠቱ በአፋጣኝ ካልተገታና የአገሬው ደኽንነት ትኩረት አግኝቶ ኑሮውን የሚያሻሽልበት ሥርዓት ካልተፈጠረ ሕዝብ ለምን ብሎ ይጠይቃል፡፡ መድፍና መትረየስ የማይገድበው ጎርፍ ሆኖ መስተዳድሩን ትልቅ ችግር ውስጥ ይከተዋል፡፡ ይህ የሚከሰተው በአልቃይዳ ወይም በግንቦት ሰባት ወይም በኤርትራ ወዘተ ሳይሆን በመስተዳድሩ ነው፡፡ በመሆኑም መስተዳድሩ ካሁኑ የእርምት እርምጃ ቢወስድ ይበጀዋል፡፡ የምንአባቱ ይሆናል ፖለቲካም ወሰን እንደሚኖረው ማወቅ ብልህነት ነው፡፡
ገንዘብ ይቀንስ ቢባል እንዴት ነው የሚደረገው ብትል ሁለት ስልት አለ፡፡ ሁለቱም የሚሠራው በባንኮች (ብሄራዊ ባንክንና የንግድና የልማት ባንኮችን ማለት ነው) በኩል ነው፡፡ ሁለቱም ዒላማ የሚያደርጉት ብድርን ነው፡፡ የመስተዳድር ብድርና የግለሰቦች (ድርጅቶችን) ብድር፡፡ አንዱ የመጠን ወሰን ነው፡፡ መጠኑ በኢኮኖሚው ውስጥ ዋጋን አረጋግቶ ሕዝብም የሚፈልገውን ገንዘብ ያገናዘበ መጠን ይሆናል፡፡ ባንኮችን ከዚህ የበለጠ ብድር እንዳትሰጡ የሚል ትዕዛዝ ከብሄራዊ ባንክ ይወጣል፡፡ እሱም ለመስተዳድሩና ለባንኮች የሚያበድረውን ይወስናል፡፡ ስለዚህ ሰው (የተፈጥሮና የሕግ) የሚፈልገውን ብድር አያገኝም፡፡ ባንኮችም ለማበደር ችሎታውም ፍላጎቱም ኖሯቸው አያበድሩም፡፡ በዚህ ስልት ኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ ይወሰናል፡፡ ሁለተኛው ወለድን መጨመር ነው፡፡ ለምሳሌ ባንኮች በ12 በመቶ ወለድ ያበድሩ ከነበር አሁን 20 በመቶ ቢባል የተበዳሪው ቁጥር ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ በሁለቱም በኩል ማለትም የብድር መጠን በመወሰንና ወለድ በመጨመር የብድሩን መጠን ይቀንሳል፡፡ ይህም የገንዘቡን መጠን ይቀንሳል፡፡ ሌሎች የገንዘብን መጠን የሚወስኑ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንዱና ዋነኛው የውጭ ምንዛሪ ሲሆን ሌላኛው ብሄራዊ ባንክ የሚያካሂዳቸው ተግባራትና ወጪዎች ናቸው፡፡
ገንዘብ በመቀነስ ፍላጎትን ቀንሰን ዋጋ እናረጋጋ የሚባለው ስልት አገራዊ ፍላጎትን እንቀንስ ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ሌላ ሳይሆን አገሬው ሸምቶ ከመብላት ይቆጠብ ነው፡፡ ይህ ማለት ኢኮኖሚውን አኮማትረን፤ ዛሬ ሥራ ይዞ ደመወዝ አግኝቶ ገበያ የሚወጣውን ሠራተኛ ሕዝብ ከሥራ አባረን የመግዛት አቅሙን (የምግብ ፍላጎት ተፈጥሮአዊ ስለሆነ አይቀንስም) እንቀንስና ዋጋ ላይ ያለውን ጫና እናስወግድ የሚል ነው፡፡ ኢኮኖሚው ሲኮማተር የችግሩን ገፈት የሚቀምሰው ዝቅተኛ ገቢ የሚያገኘው ነው፡፡
ገንዘብን በተመለከተ እኔም አንተም ሌሎችም ለማለት የሚፈልጉት ኢሕአዴግ እንደመስተዳድር በግብርም፣ በቀረጥም፣ በብድርም፣ በልመናም፤ ከአገር ውስጥም፣ ከውጪም፣ ከብሔራዊ ባንክም፣ ከንግድ ባንኮችም ገንዘብ ይሰበስባል፡፡ ሲያወጣ ግን እንደ ድርጅት እንጂ እንደ መስተዳድር አይደለም፡፡ ወጪውም ገደብ የለውም፡፡ ይህ መቆም አለበት የሚል ነው፡፡ እስማማለሁ፡፡ ግን አሁን ባለው ሁኔታ ማቆም አትችልም፡፡
በሥልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በሁለት ምክንያት ገንዘብ ያወጣሉ፡፡ አንዱ በሥልጣን መሰንበትን ለማረጋገጥ፡፡ ከዚህ አኳያ አስፈላጊ መስሎ ከተገኘ ለቁጥር አዳጋች የሆነ ጠባቂ ይቀጠራል፤ መሣሪያ ይሸመታል፤ ሕዝብ ይጠረነፋል፤ ሰምቶ አደሮች ይከራያል፤ እስር ቤት ያስፋፋል፡፡ በተለይ ከሕዝብ የራቀና መራቁንም ያወቀ በሥልጣን ለመቆየት የሚችለው በዚህ ስልት ብቻ ነው፡፡ ሁለተኛው ገንዘብ የሚያወጣበት ምክንያት ለልማት ነው፡፡ መንገድ ይሠራል፤ ከተማ ይገነባል፤ ዘመናዊ ሆቴሎች ይመረቃሉ፡፡ ግድቦች ይሠራሉ፡፡ ፋብሪካዎች ይገነባሉ፡፡
ገንዘብ በዛ ይቀንስ ቢባል የቱ ይመስልኻል የሚቀነሰው? ሁለተኛው ማለትም አገርን ሊጠቅም የሚችለው እንጂ በሥልጣን አዝላቂው አይደለም፡፡ የመኖር ወይም ያለመኖር ጥያቄ በመሆኑ ይጨምራል እንጂ በኔ ይሁንብህ አይቀንስም፡፡ እንዲያውም የልማቱ ከቀነሰ የሥልጣን አድኑ ይጨምራል፡፡ ለምን ብትል ችግር ስለሚጨምርና ውጥረቱም ስለሚገን፡፡ ይህም ያሸብራቸዋል፡፡ በመሆኑም ነፍስና የሥልጣን አድኑ ወጪ ይጨምራል፡፡
በአንድ ወቅት “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በእግዚአብሔር እጅ ላይ ነው ያለው” ማለትዎ ይታወሳል፡፡ ዝናብን አስቦ የአንድን አገር የኢኮኖሚ ልማት ማቀድ አይቻልም ማለትዎ ነው?
ፕ/ር በፈቃዱ፡- እንደዚያ ማለቴ አልነበረም፡፡ እኔ ያንተን ያህል ወደ ውስጥ አልገባሁም፡፡ እኔ ያልኩት ቀላል ነው፡፡ ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው፡፡ ግብርና ካላደገ ኢኮኖሚው ብቻ አይደለም የማይኖረው፡፡ ሕዝብም እንጂ፡፡ የሚበላ አይኖርም፡፡ ያኔ ደግሞ አምራቹ ኢትዮጵያዊ ገበሬ ብቻ ነበር፡፡ እውነትም በዚያን ጊዜ ኢኮኖሚያችን በእግዚአብሔር እጅ ነው የነበረው፡፡ የኢትዮጵያን ገበሬ ከማምረት የሚያግደውና የሚገድበው ዝናብ ብቻ ስለነበር፡፡
ዛሬ እግዚአብሔርም የባሰ ችግር ወስጥ ገብቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በገዢዎች፤ በካድሬዎች፤ በብልጣብልጦች፤ በደላሎች፤ በቻይናዎች፤ በቱርኮች፤ በአረቦችና በሕንዶች እጅ ነው ያለው፡፡ እነሱም በመስተዳድራችን እገዛ ተፈጥሮን ለመግራት እኛንም ለመግዛት እየጣሩ ነው፡፡ ዛሬ አድራጊዎቹ እነሱ ናቸው፡፡ ድሮ እግዚአብሔርን ዝናብ አዝንብልን ነበር ፀሎታችን፡፡ የዛሬውን ምህላ አንተው ንገረኝ፡፡
የሕዝብ ቁጥር መጨመር ከመሬት ጥበት ጋር ተያይዞ የእርሻውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሳደግ አስቸጋሪ ነው ይባላል፤ በእርግጥ ኢትዮጵያ ለእርሻ ይዞታ የሚሆን የመሬት ጥበት አለባት?
ፕ/ር በፈቃዱ፡- ትልቁ የምርት ቀያጆች ቁሳዊ ግብአቶች አይደሉም፡፡ እርግጥ ያስፈልጋሉ፡፡ ብቸኛው ምርት አፍላቂ ሰው ነው፡፡ የትልቅነትና የሀብታምነት ምስጢሩ ምርታማነት እንጂ የተያዘ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ትኩረት መሰጠት ያለበት ምርታማነት ላይ ነው፡፡ ጃፓንና ኮሪያ የቁስ ግብአት ድኾች ናቸው፡፡ ግን የሕዝባቸውን እውቀት አዳበሩ፡፡ እውቀትን ወደ ብልሃት (ፈረንጅ ቴክኖሎጂ የሚለው) ለወጡ፡፡ ምርታማነታቸውን፤ የፈጠራ ችሎታቸውን አዳበሩ፡፡ በአጭር ጊዜ ከሰው እኩል ሆኑ፡፡
ምርታማነትህን አሳድግ፡፡ ያመረትኸው ያንተ እንዲሆን አገርህ ያንተ መሆኗን አረጋግጥ፡፡ ለዚህም አገርህን ጠብቅ፡፡ አገር ሳይኖርህ የተመረተው የኔ ነው ማለት አትችልም፡፡ የምታመርተው እንዲያድግ እውቀትህንና ብልሀትህን አዳብር፡፡ ይኸው ነው መልእክቱ፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 221 ጥር 10 2017 ዓ.ም
