የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚከፈቱ ማንኛቸውም የባንክ ቅርንጫፎች ከባንኩ በቀጥታ የተለየ የሥራ ፈቃድ ማውጣት እንደሚኖርባቸው የሚያስገድድ አዲስ መመሪያ ማውጣቱን አስታወቀ።
ብሔራዊ ባንክ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚከፈቱ የባንክ ቅርንጫፎች ሊያሟሏቸው የሚገቡ አሥር ዋና ዋና ነጥቦችን ያካተተ መመሪያ ትናንት ታህሳስ 29 ቀን 2018 ዓ.ም ይፋ አድርጓል።
ባንኩ በእነዚህ ዞኖች ውስጥ ቅርንጫፎቻቸውን የሚከፍቱ ባንኮች የተጠቀሱትን መስፈርቶች ማሟላት እንዳለባቸውም አሳስቧል።
በመመሪያው መሰረት፤ በኢኮኖሚ ዞኖቹ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ የባንክ ቅርንጫፎች፣ ከብሔራዊ ባንክ ቀጥተኛ የሥራ ፈቃድ ማግኘት እንዳለባችውና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት አገልግሎት መስጠት ግዴታቸው ሲሆን የተጠቀሱትን አገልግሎቶች መስጠት ስለመቻላቸውም አስቀድሞ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።
ቅርንጫፎች አገልግሎት መስጠት ያለባቸው በቀጠናው ውስጥ ለሚኖሩ ነዋሪዎች እና እዚያው ለተሰማሩ የንግድ ተቋማት ብቻ መሆኑን እንዲሁም የሚከፈቱትን የቅርንጫፎች ብዛት ብሔራዊ ባንክ ራሱ እንደሚወስን በመመሪያው ተመልክቷል።
ለእነዚህ ልዩ ቅርንጫፎች የሚከፈለው የፈቃድ ክፍያ በብሔራዊ ባንክ መመሪያ ቁጥር SBB/85/2022 ወይም በቅርቡ በታደሱ መሰል ድንጋጌዎች መሠረት የሚፈጸም መሆኑን ባንኩ አመልክቷል።
ይህ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚከፈቱ የባንክ ቅርንጫፎች አስተዳደር መመሪያ ታህሳስ 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆን መጀመሩም ተገልጿል።
