የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ማክሰኞ ጥር 12 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄድ የ15ኛው ዙር የውጭ ምንዛሪ ጨረታ መጥራቱን አስታወቀ። ባንኩ በዚህ ዙር 70 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለጨረታ ያቀረበ ሲሆን፣ ፍላጎት ያላቸው ባንኮች በጨረታው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።
ይህ ጨረታ በየሁለት ሳምንቱ የሚካሄደው መደበኛ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ አካል ሲሆን፣ ዓላማውም የሀገሪቱን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር እና የውጭ ክፍያ ሚዛን መረጋጋትን ለማረጋገጥ መሆኑ ተጠቁሟል።
ብሔራዊ ባንክ የገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓትን ተግባራዊ ካደረገ ወዲህ፣ በገበያው ውስጥ ያለውን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ለማሳደግ በየጊዜው እንዲህ ያሉ ጨረታዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል።
ባለፈው ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ላይ ተካሂዶ በነበረው 14ኛው ዙር የውጭ ምንዛሪ ጨረታ፣ ባንኩ በተመሳሳይ 70 ሚሊዮን ዶላር አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ የቀረበው የገንዘብ መጠን በአጠቃላይ ለ32 ባንኮች መከፋፈሉ ይታወሳል። ይህንኑ የገበያ ሁኔታ ተከትሎ፣ የአንድ የአሜሪካ ዶላር አማካይ የመሸጫ ዋጋ 154.87 ብር መድረሱ ተመልክቷል።
