ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ አስተዳደራዊ እርምጃና ቀኖና ሰጡ

Date:

ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ እና ስልጤ ሀድያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ “በመመረቂያ ጋውን” ጸሎተ ቅዳሴ ባከናወኑ  ካህን እና  የደብሩ አለቃ ላይ አስተዳደራዊ ርምጃና ቀኖና ሰጡ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅድሳት መጻሕፍትን መሠረት፣ ትውፊትን እንደመቀነት ቀኖናን እንደ አጥር  አድርጋ ሥርዐተ አምልኮን እስካሁን ባለመለወጥ እያከናወነች የምትገኝ ድንቅና ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ናት።

ይሁንንና መነሻቸው የተለያየ ሆኖ በአሁኑ ጊዜ  በሰማይ ሥርዐት በመላእክት ምስጋና የምታመሰግንበት ድንቅ አገልግሎት ሳይቀየር  ሥርዐተ አበውን ወደ ጎን በመተው ሥጋዊ ደማዊ አመለካከትን  ደባል ማድረግ ከጀመረ ዋል ሰንበት ብሏል።

ለዚህ እንደማሳያ በቅርቡ በጀሞ ፈለገ ዮርዳኖስ ቅዱስ ዮሐንስና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመውና በተለያዩ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወር  የቆየው   ኢቀኖናዊ ድርጊትን እንደማሳያ ይጠቀሳል።

ሰኔ 29/2017 ዓ/ም በዕለተ ሰንበት የቅዳሴ ማጠናቀቂያ ሥርዐት ላይ የቀደሰው ዲያቆን “አድንኑ አርእስቲክሙ ቅድመ እግዚአብሔር አምላክነ በእደ ገብሩ ካህን ከመ ይባርከነ/ይባርክሙ የሚለው ለመጨረሻው ማስናበቻ ቡራኬ ዝግጁ ማድረጊያ ጸሎትን ሥርዐተ ቅዳሴው ከሚያዘው ውጪ ኢቀኖናዊ በሆነ አለባበስ “የመመረቂያ ጋውን” በመልበስ ጸሎቱን ያከናወኑ ሲሆን ሀገረ ስብከቱም ይህንን ኢቀኖናዊ ድርጊት በሰነድና አጣሪ ልኡክ በመመደብ ካጠራ በኋላ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ አስተዳዳራዊ ርምጃ ወስደዋል ቀኖናም ሰጥተዋል።

ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ  “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” (የሐዋርያት ሥራ  ፳፥፳፰) እንደሚለው ሊቃነ ጳጳሳት ቤተ ክርስቲያን በተባለው ልክ የመጠበቅ ሐላፊነት አለባቸው።

ቤተ ክርስቲያን በምትመራባቸው ሌሎች  የሥርዐት መጻሕፍት በተለይም በዲዲስቅልያ በፍትሕ መንፈሳዊና  በሕገ ቤተ ክርስቲያን ተጠቅሶ ይገኛል።

በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፬፡፷፭ እንደተቀመጡ ሊቀ ጵጵስና ሃይማኖትን የመጠበቅና አማኞችን በመንፈሳዊና በሕጋዊ መንገድ የመምራት ሐላፊነት እንዳለበት ይናገራል።

በዚህም  መነሻነት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ  ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የተፈጸመውን ድርጊት አስመልክተው ድርጊቱን ለፈጸሙ እና በዝምታ ሐላፊነታቸውን ላልተወጡ የደብሩ አስተዳዳሪያ እና የዕለቱ ቀዳሽ ሠራኢ ዲያቆን ቀኖና ሰጥተዋል።

አንደኛ  ቀሲስ ሀብታሙ ቢነጋ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አክብረው ማስከበር ሲገባቸው የቀደሱበትንና የከበረውን ልብሰ ተክህኖ አውልቀው በኮሌጅ የመመረቂያ ጋወን አድንኑ በማለት ለፈጸሙት ስህተት ከ21 ቀን ደመወዝ ቅጣት ጋር  ከነሐሴ 1 ጀምሮ ለ21 ቀናት በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም በቀኖና ተወስነው እንዲቆዩ፤

ሁለተኛ  መልአከ ፀሐይ አባ ገብረ ሥላሴ ጎበዜ የደብሩ አስተዳዳሪ  ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን አክብረው ማስከበር ሲገባቸው የሚያስነቅፍ ሥራ ሢሰራ በቸልተኝነት በመመልከታቸው እንደ መጀመሪያ ጥፋት ተቆጥሮ ከነሐሴ 1 ጀምሮ ለ21 ቀናት በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም በቀኖና ተወስነው እንዲቆዩ በማለት ብፁዕነታቸው  ቀኖናውን ሰጥተዋል።

ድርጊቱ በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና አኳያ  ክህነት የሚያሲዝና ሌላ ተጨማሪ አስተዳደራዊ እርምጃ የሚያስወስድ ቢሆንም የድርጊቱ ፈጻሚና ተባባሪ በመጸጸት ይቅርታ ስለጠየቁና ቤተ ክርስቲያናችንም ይቅርታ ለሚጠይቅ ደጇ ሁልጊዜም የተከፈተ በመሆኑ  ቀኖና እና መጠነኛ አስተዳደራዊ ርምጃ መወሰዱ  ተገልጿል።

© የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከ ሚዲያ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንግሊዝ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ አገደች

የእንግሊዝ መንግሥት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች...

አሜሪካ 300 ሚሊዮን ዶላር ለኢራን ልትሰጥ ነው መባሉን ትራምፕ አስተባበሉ

አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ከደረሱ በኋላ አሜሪካ እና አጋሮቿ...

ደህና ሁን! ሰሜ…ስሜ!

“ከልጅነታችን ጀምሮ ጥበብ አገናኝታን ፣ በግሽ አባይ የባህል ቡድን...

✌️ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው

✌️ከዕድሜው የገዘፈው የታሪኩ ጁዋር ጀግናውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር የጀግንነት...