በታሪክ ስነዳ፣ በመፅሐፍት እና በኹነት ዝግጅትን ጨምሮ በጋዜጣ ሥራ የሚታወቀው ተወዳጅ ሚዲያ 22ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በየወቅቱ አብረው የነበሩ ባለሙያዎችን እና ተቋማትን በማመስገን ሊያሳልፍ ነው።
“ማክበር መሰልጠን ነው” በሚል መሪ ቃል ከፊት፣ ከጎን እና ከጀርባ የነበሩ የሥራውን ዋና አንቀሳቃሾች ማመስገን አስፈላጊ መሆኑን የድርጅቱ መሥራች ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ተናግሯል።
ጋዜጠኛ እዝራ ከተወዳጅ ሚዲያ ጋር አብረው በነበሩ ባለሙያዎች እና ተቋማት ምክንያት ሰው ተወዳጅ ሚዲያ ለዚህ ደረጃ መብቃቱን ይናገራል።
ተወዳጅ ሚዲያ በተለይ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ለ25 ሰዎች የኮንትራት የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ብዙዎችም አቅማቸውን እንዲያውቁ እና እንዲጠቀሙ አድርጓል።
የካቲት 2 ቀን 1996 ዓ.ም በይፋ ህጋዊ ሰውነቱን አግኝቶ ሥራውን የጀመረው ተወዳጅ ሚዲያ “ተወዳጅ” የማስታወቂያ ጋዜጣን በማሳተም ወደ ሚዲያ ሥራው ገብቷል።
በአሁኑ ሠአት ተወዳጅ ሚዲያ ታሪክ በመሰነድ ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ከ23 በላይ መፅሐፍትን ለአንባቢ ያደረሰ ሲሆን፥ 45 ታሪኮችን በሲዲ እና በዲቪዲ በማቅረብ ልዩ ልዩ ኹነቶችንም አዘጋጅቷል።
ተወዳጅ ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን በተለይ የሰዎች የሕይወት ታሪክ ከጎግል ላይ በቀላሉ ተፈልጎ እንዲገኝ ያደረገ ሲሆን ለዚህ ጥረቱም ዳላስ ከሚገኘው የአርአያ ሰው ሽልማትን ማግኘት ችሏል።
ተወዳጅ ሚዲያ የኢንሳይክሎፒዲያ ፕሮጀክትን በመቅረፅ ከሚያዝያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ “መዝገበ አዕምሮ” የተሰኘውን እና የ400 የሚዲያ እና የጥበብ ሰዎችን ታሪክ የያዘ መፅሐፍ በ2 ቅፅ አሳትሟል።
