ታዋቂው ጋዜጠኛና የጥበብ ሰው ተመስገን ባዲሶ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈጸመ

Date:

በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነትና የሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ ጉልህ አሻራ ያሳረፈውና በብዙኃኑ ዘንድ “የማይረሳውና ጨዋታ አዋቂው” እየተባለ የሚጠራው ተመስገን ባዲሶ፣ ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በ51 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

​የጋዜጠኛው የቀብር ሥነ-ሥርዓት ዛሬ የካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም በብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተክርስቲያን፣ ወዳጅ ዘመዶቹና የሙያ ባልደረቦቹ በተገኙበት በክብር ተፈጽሟል።

​ተመስገን ባዲሶ ታህሳስ 16 ቀን 1967 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ “አውቶቢስ ተራ ደጃዝማች ገነሜ ትምህርት ቤት” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከአባቱ ከአቶ ባዲሶ ባደታና ከእናቱ ከወይዘሮ ባዬሽ ዳዊት ተወለደ።

ትምህርቱን በደጃዝማች ገነሜ ትምህርት ቤት የጀመረው ተመስገን፣ ገና በወጣትነቱ ለጥበብና ለንባብ የነበረው ፍቅር ለየት ያለ እንደነበር ይነገርለታል።

​በ1985 ዓ.ም “የፍቅር ማህደር” በተሰኘ ጋዜጣ ላይ ታሪኮችን በመጻፍ የጀመረ ሲሆን፣ ከዚያም ባለፉት ዓመታት በበርካታ ታዋቂ ህትመቶች ላይ በመሳተፍ ለአንባቢዎች ምክርና እውቀትን ሲያጋራ ቆይቷል። ከእነዚህም መካከል ቃልኪዳን፣ ጽጌረዳ፣ ማክዳ፣ እንኮይ እና ሮዝ መጽሔቶች እና ሊቢሮ፣ ኔሽን እና ሆሊዴይ በተሰኙ ጋዜጣዎች ላይ ተሳትፏል።

​ተመስገን ባዲሶ በህትመት ውጤቶች ብቻ ሳይወሰን በቴሌቪዥን መስኮትም ተወዳጅነትን አትርፏል።
​ከ1999 – 2002 ዓ.ም፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ)

“ጉራማይሌ” ፕሮግራም ላይ በጋዜጠኝነት ሰርቷል።
​ከ2005 – 2007 ዓ.ም “ጉራማይሌ ቶክ ሾው” በዩቲዩብ ላይ አስተማሪና አዝናኝ ፕሮግራሞችን በማቅረብ የሚዲያ ዘርፉን አገልግሏል።

​በማህበራዊ ሚዲያ በነበረው ንቁ ተሳትፎና ተፅዕኖ ፈጣሪነት በስነጽሁፍ ዘርፍ በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው ሶስተኛው የ”ጣና አዋርድ” ሽልማት አሸናፊ መሆን መቻሉም የሚታወስ ነው።

​ተመስገን ከሙያው ባለፈ በደግነቱና ለሰዎች በነበረው አሳቢነት ይታወቃል። ጓደኞቹን በማስተባበር የተቸገሩ ወገኖችን እስከ እለተ ሞቱ ድረስ ሲረዳ የቆየ ሲሆን፣ በተለይም ​ከከተማ ርቀው የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እንዳይዘጉና አገልግሎታቸው እንዳይቋረጥ በገንዘብና በቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

​ተመስገን ባዲሶ ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ የካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

የግዮን መጽሔት ዝግጅት ክፍል በተመስገን ባዲሶ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን ትገልጻለች ።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንግሊዝ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ አገደች

የእንግሊዝ መንግሥት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች...

አሜሪካ 300 ሚሊዮን ዶላር ለኢራን ልትሰጥ ነው መባሉን ትራምፕ አስተባበሉ

አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ከደረሱ በኋላ አሜሪካ እና አጋሮቿ...

ደህና ሁን! ሰሜ…ስሜ!

“ከልጅነታችን ጀምሮ ጥበብ አገናኝታን ፣ በግሽ አባይ የባህል ቡድን...

✌️ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው

✌️ከዕድሜው የገዘፈው የታሪኩ ጁዋር ጀግናውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር የጀግንነት...