የፈረንሳዩ የነዳጅና ኢነርጂ ግዙፍ ኩባንያ ቶታልኢነርጂስ (TotalEnergies) በኢትዮጵያ ለበርካታ አስርት ዓመታት ሲያካሂድ የቆየውንና ወደ 120 የሚጠጉ የነዳጅ ማደያዎችን የያዘውን መረብ ለአፍሪካ አቀፉ የነዳጅ አከፋፋይ ኦላ ኢነርጂ (OLA Energy) ለመሸጥ ከስምምነት መድረሱ ተገለጠ።
አፍሪካ ቢዝነስ የተሰኘው የኢኮኖሚ መጽሔት ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው፣ ሁለቱ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያለውን የቶታልኢነርጂስ የችርቻሮ ነዳጅ ስርጭት መረብ ሙሉ በሙሉ ወደ ኦላ ኢነርጂ ለማዛወር የሚያስችለውን ስምምነት አጠናቀዋል።
ቶታልኢነርጂስ በኢትዮጵያ የነዳጅ ስርጭት ገበያ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ካላቸው ግንባር ቀደም ኩባንያዎች አንዱ ሲሆን፣ እንደ ኩባንያው መረጃዎች ከሆነ በአገሪቱ ውስጥ ከ120 እስከ 143 የሚደርሱ የነዳጅ ማደያዎች አሉት።
ይህ የታቀደው ሽያጭ ተግባራዊ ከሆነ፣ ላለፉት ረጅም ዓመታት በአገሪቱ የነዳጅ ገበያ ላይ የነበረውን የኃይል ሚዛን በእጅጉ እንደሚቀይረው ተገምቷል።
ኩባንያው ይህንን ውሳኔ ያሳለፈበት ምክንያት በይፋ ባይታወቅም፣ ከአጠቃላይ የኩባንያው ስትራቴጂካዊ ሽግሽግ ወይም በአፍሪካ ካለው የንግድ ፖርትፎሊዮ ማሻሻያ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል የዘርፉ ተንታኞች ይገምታሉ።
ይህ በኢትዮጵያ የነዳጅ ስርጭት ገበያ ላይ ከፍተኛ መነቃቃትንና ለውጥን ይፈጥራል የተባለው ስምምነት መረጃው ቢወጣም፣ ካፒታል ግን ከኩባንያዎቹ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።
