የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ሰፊ ተደራሽነት ካለው ቦቲም ኩባንያ ጋር ህጋዊ የገንዘብ ማስተላለፊያ ዘዴዎችን ለማሳደግ እና በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የሽርክና የጋራ የመግባቢያ ሠነድ መፈራረሙ ተገለጸ።
ስምምነቱ የተፈረመው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ የተመራ ልዑክ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከነሐሴ 22-28 ቀን 2017 ዓ.ም ጉብኝት ባደረገበት ወቅት ነው፡፡
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱ በገበያው እንዲመራ በመደረጉ ማህበረሰቡ ገንዘቡን በህጋዊ የገንዘብ ማስተላለፊያ ዘዴዎች ተጠቅሞ እንዲያስተላልፍ ለማድረግ እንደ ቦቲም ያሉ አማራጮች የሚኖራቸውን ድርሻ ግምት ውስጥ በማስገባት ሥምምነቱ የሚኖረውን ጠቀሜታ እና አስፈላጊነት አንስተዋል፡፡
የቦቲም ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ዶ/ር ጣሪቅ ቢን ሄንዲ በበኩላቸው የመግባቢያ ሰነድ ሥምምነቱ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በቦቲም መካከል በጋራ አብሮ ለመስራት የሚያስችል መሠረት የጣለ መሆኑን ገልጸው በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገንዘባቸውን ደህንነቱ በተጠበቀ የገንዘብ ማስተላለፊያ መንገድ ወደ አገራቸው እንዲልኩ አማራጭ ዕድል እንደሚያመቻች ተናግረዋል፡፡
በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶ/ር ዑመር ሁሴን በበኩላቸው ባንኩ ከቦቲም ጋር በጋራ ለመስራት ሥምምነት ላይ መድረሱ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚገኙ ዜጎች በቀላሉ ገንዘብ ወደ አገር ቤት ለማስተላልፍ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርላቸው ጠቅሰው ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያለውን ግንኙነትም የበለጠ ለማጠናከር እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡
ቦቲም በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ደህንነቱ የተጠበቀ የድምጽ እና የቪዲዮ ጥሪ መተግበሪያ መድረክ በመሆን የተጀመረ ሲሆን አገልግሎቱን በማስፋት ወደ (fintech) እና የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር በአሁኑ ሰዓት እንደ አለምአቀፍ እና የሀገር ውስጥ የገንዘብ ዝውውሮች፣ ዲጂታል ካርዶች፣ ክፍያዎች፣ የመንግስት አገልግሎቶች (እንደ የመንጃ ፍቃድ እና የኤሚሬትስ መታወቂያዎችን ማደስ የመሳሰሉ) አገልግሎቶችን እንዲሁም የቤት አገልግሎቶች፣ ግብይት እና የጤና ክትትል ያሉ አገልግሎቶችን የሚሰጥ መተግበሪያ መሆኑ ተመላክቷል።
