የሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ያስጠናው ጥናት ላይ የተካተቱ ኢትዮጵያውያን፤ አሁን ያለው ሙስና ካለፉት አምስት ዓመታት በእጅጉ ይበልጣል ብለው እንደሚያምኑ በጥናቱ ተመላክቷል።
የፀረ ሙስና ኮሚሽን ይፋ ያደረገው ባለ 70 ገጽ አራተኛው ብሔራዊ የሙስና ዳሰሳ ጥናት ዓላማ፤ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ስላለው ሙስና የህብረተሰብን የግል አስተያየት ማወቅ እና ስለ ሙስና ያለውን ግንዛቤ መረዳት ከተዘረዘሩት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።
ጥናቱ ከጋምቤላ ክልል ውጭ ሁሉንም ክልሎች እና ሁለቱን ከተማ አስተዳደሮች ያካተተ ነው።
ከተለያዩ ክልሎች እና ከተሞች በጥናቱ 2 ሺህ 195 ሰዎችን ለማካተት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ በጥናቱ 91.4 በመቶ ሰዎችን ማካተት ተችሏል።
በጥናቱ መሠረት ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ሙስና እስካሁን ድረስ መሠረታዊ ችግር ሆኖ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በጥናቱ መሠረት ተሳታፊዎቹ ለሙስና ተጋላጭ ናቸው ወይም ሙስና ይታይባቸዋል ያሏቸውን በርካታ የመንግሥት ተቋማት ዘርዝረዋል።
የመሬት ባለቤትነት ምዝገባ ፣ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮዎች ወይም መሥሪያ ቤቶች ፣ ገቢዎች እና የትራንስፖርት መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ ሙስና አለባቸው ተብለው የሚታሰቡ ተቋማት ናቸው ይላል ጥናቱ።
የንግድ ቢሮዎች፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለሥልጣን ወይም ቢሮ አልያም መሥሪያ ቤቶችም ከፍተኛ ሙስና አለባቸው ተብለው በጥናቱ የተለዩ መሆናቸውን ያክላል።
በተጨማሪም የጉምሩክ ኮሚሽን መሥሪያ ቤቶች እና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሙስና አለባቸው።
ጥናቱ የተካተቱት ጋዜጠኞች በበኩላቸው የሚደርስባቸው ማስፈራሪያ፣ የመረጃ ክልከላ እና የፖለቲካ ጫና በሙስና ላይ የምርመራ ሥራ እንዳይሰሩ ዋነኛ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል።
ለሙስናው መንስኤዎች ናቸው ተብለው በጥናቱ ተሳታፊዎች የሚታመኑት ምክንያቶች ደግሞ በአቋራጭ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀብታም የመሆን ጉጉት፣ የሥነ ምግባር ጉድለት መጨመር፣ የተጓተተ የአገልግሎት ሥርዓት ፣ የሕግ አለመከበር ፣ ድህነት ፣ ዝቅተኛ ገቢ እና የኑሮ ውድነት ናቸው በሚል ተዘርዝረዋል።
ዜጎች የሙስና መከላከል ሥራውን እንዳያግዙ ድርጊቱ ሲፈጸም የሚጠቁሙበት መንገድ ረዥም መሆን፣ የከለላ ዋስትና ማጣት፣ እንዴት መጠቆም እንዳለባቸው አለማወቅ እንቅፋት መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል።
ጋዜጠኞች ሙስና ላይ ተከታትለው እንዲሠሩ ማድረግ እና የሕግ ከለላ መስጠት አስፈላጊ መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል።
አገልግሎት ለመስጠት ገንዘብ መቀበል መደበኛ ተግባር ተደርጓል የሚለው ጥናቱ ፣ ሙስናን ለመቀነስ በሙሰኞች ላይ ጥንካራ እርምጃ መውሰድ ችግሩን መቀነሻው ዘዴ ነው ብለው ያምናሉ ብሏል።
በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት የጉሙሩከ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርን ጨምሮ በርካታ ገለሰቦች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መያዛቸውን ያስረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽ አገልግሎት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ እና የሀገር ሀብት የሚመዘብሩ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ መናገሩ ይታወሳል።
ሸገር 102.1
