በሀገራችን ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ቤተ እምነቶች አካባቢ ግጭት እና ቀውሶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ እንደኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ላይ ደግሞ በእምነት ተቋማት አካባቢ የሚፈጠር ቀውስ ምን ያህል በሀገር ላይ ከባድ ችግር ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ በተለይም አሁን ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በኩል እየታየ ያለው ክፍፍልና ትርምስ የጉዳዩ አሳሳቢነት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ አመላካች ነው፡፡ ሀገራዊ መዋቅር ያላት ቤተክርስቲያን በዘርና በክልል እየተከፋፈለች በመጣች ቁጥር የሚፈጠረው ችግር እጅጉን የከበደ እንደኾነ መረዳት አይገድም፡፡ ከአምስት ወራት በፊት ሕገ ቤተክርስቲያን ጥሰው ሹመት የፈጸሙ አባቶች እና እርሱን ተከትሎ የመጣው ቀውስ ለዚህ ጥሩ የቅርብ ጊዜ ማሳያ የሚኾን ነው፡፡ የኾኖ ኾኖ ያ ክስተት ከተፈጸመ በኋላ አፈንግጠው የነበሩ አባቶች በብዙ ውጣ ውረድ ወደቤተክህነቱ ማዕቀፍ ቢመለሱም ሌላ አፍራሽ ኃይል ግን ከወደ ትግራይ ብቅ ማለቱ አልቀረም፡፡
ይህ ኃይል ከፖለቲከኞች በላይ እራሱን ስውር የፖለቲካ ተዋናይ አድርጎ የቀረበ ይመስላል፡፡ ያለምዕመኑ ፈቃድና ፍላጎት በእምነቱ ስም ልዩ ልዩ ኹነቶችን በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ እንደዚህ ቡድን እሳቤ አሁን ላይ የትግራይ ቤተክህነትን ከማቋቋም አልፎ ጳጳሳት መሾም ያስፈለገው በትግራይ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ‹‹ሁለት እጅና እግሯን አስገብታ የጦርነቱ መሪ ተዋናይ፣ ሎጂስቲክ፣ አዋጊ፣ ጀነራል፣ ኮረኔል፣ ሻለቃ በመኾኗ›› ምክንያት እንደኾነ ይነገራል፡፡ ይህ ሐሳብ ጦርነቱ ቆሞ ፖለቲከኞች ስምምነት ከፈጠሩ በኋላ ወደ አደባባይ ወጥቶ የሌላ ጠብ ሰበበ ምክንያት መኾኑ ብቻ በቁሙ የወደቀ ሐሳብ ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም ፖለቲከኞች በእርቅ የቋጩትን ጉዳይ ቤተክርስቲያን እንደእምነት ተቋምነቷ ለእርቅ የማትገዛበት አንዳችም ምክንያት ሊኖር ስለማይችል ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ማንም እንደሚያውቀው ይህንን ጦርነት ባርካና ቀደሳ አላስጀመረችውም፡፡ ከዚያ ይልቅ ጦርነቱ እንዳይጀመር፣ ከተጀመረ በኋላም እንዲቆም ልዩ ልዩ ጥረቶችን ስታደርግ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳን በአንዳንድ የሃይማኖት አባቶች በኩል የተለያዩ ጦርነት ደጋፊ ሐሳቦች ቢንጸባረቁም ቤተክርስቲያኒቱ እንደተቋም አንድም ጊዜ ጦርነቱን በይፋ ደግፋ ግን አታውቅም፡፡
ይልቁንም ቤተክርስቲያን በዚህ ጦርነት ምክንያት በርካታ ምዕመኖቿና አያሌ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶቿን አጥታለች፡፡ በጦርነቱ በትግራይም ይሁን በፌደራል መንግሥት በኩል የበርካታ ዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡ ከእነዚህ ዜጎች ውስጥ ደግሞ ከፍተኛውን የሞት ድርሻ የሚወስዱት የቤተክርስቲያኒቱ ምዕመናን መኾናቸው አይታበልም፡፡ በዚህም ሁለት ሦስት ድርብ ጉዳት ያስተናገደች ቤተክርስቲያን ይህን መሰሉ ክስና እንቅፋት አይገባትም ነበር፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ሌላ በመኾኑ በእምነት አባቶች ስም ሌላ እምነት ለበስ ፖለቲካዊ ቁማር እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ‹‹የትግራይ ቤተ ክህነት ነኝ›› ባዩ ‹‹መንበረ ሰላማ›› ዛሬ ላይ የሚያሳየው ባሕሪ ቀደም ሲል ህወሓት የነበረውን ዕብሪት ዐይነት መገለጫ የኾኑ ትዕይንቶችን ነው፡፡
ለምሳሌ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በትግራይ የሃይማኖት አባቶች በኩል የሚነሳው ተቋውሞ እውነትነት ካለው በሚል ይቅርታ ጠይቃ ነበር፡፡ ከይቅርታውም በላይ ፓትርያሪኩን ያካተተ ልዑክ ወደ ክልሉ ልካ ነበር፡፡ ምላሹ ግን እንደፖለቲከኞች በእብሪት ተወጥረው ቤተክርስቲያንን ዘግቶ መጥፋት ኾነ፡፡ ከፍ ሲልም ኢ ቀኖናዊ በኾነ መንገድ ‹‹ትግራይ ቤተክህነት›› ሲሉ ላቋቋሙት የይስሙላ ድርጅት ‹‹አቡነ ማትያስ እና ሉዑካቸው በመቀሌ አቀባበል ያልተደረገላቸው ምንም ዓይነት የተጻፈልን ደብዳቤም ይሁን የተያዘ መርሃ ግብር ስላልነበረ ነው›› ሲሉ ምጸታዊ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ይህን ላስተዋለ በዐውደ ውጊያ ያበቃ የመሰለው የፖለቲከኞቹ ጦርነት ልብሱን ቀይሮ ሃይማኖት ካባ ሥር መሸጎጡን ይረዳል፡፡
ሰሞኑን በትግራይ ክልል ሀገረስብከቶች ምን ተከሰተ ብለን ስናይ በክልሉ የሚገኙ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት የዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ አካሒደዋል፡፡ የአራቱ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት እና ስምንት ሥራ አስፈጻሚዎች የሚገኙበት አካል፣ 101 ድምፅ ሰጪዎች የተሳተፉበትን የዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ፣ በአክሱም ከተማ አትሮንስ ሆቴል አካሒደዋል፡፡ በዚህ ሕገወጥ ምርጫ 19 መነኰሳት ከሀገር ውስጥ፣ ሰባት መነኰሳት ከውጪ ሀገር በጠቅላላው 26 መነኮሳት ተወዳድረዋል፡፡ በውጤቱም፣ ከፍተኛ ድምፅ ያገኙ አምስት መነኰሳት ለሀገር ውስጥ፣ አምስት መነኰሳት ደግሞ ለውጭ አህጉረ ስብከት ለኤጲስ ቆጶስነት ሹመት እንደተመረጡ ታውቋል፡፡ በዚህም መጋቤ ሃዲስ ቆሞስ አባ ዘስላሴ ማርቆስ፣ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ሃ/ሚካኤል አረጋይ፣ ሊቀ አእላፍ አባ እስጢፋኖስ ገ/ጊዮርጊስ፣ ንቡረ እድ ቆሞስ አባ መሓሪ ሃብቴ ቆሞስ አባ ኤልያስ ታደሰ ገብረኺዳን በትግራይ ውስጥ የሚያገለግሉ ኤጲስ ቆጶሳት ኾነው መመረጣቸው ተገልጿል። በተመሳሳይ ቆሞስ አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደሳሙኤል፣ መልአከ ገነት አባ ፅጌ ገነት ኪዳነ ወልድ፣ አባ ዘርአ ዳዊት ብርሃነ፣ መልአከ ፀሐይ አባ የማነ ብርሃን ወልደሳሙኤል፣ መልአከ ፅሓይ ቆሞስ አባ ዮሃንስ ከበደ ከአገር ውጭ የሚያገለግሉ ኤጲስ ቆጶሳት ኾነው ተመርጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክዋስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ግን ይህ ከመኾኑ በፊት ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም በሰጠው ይፋዊ መግለጫ ኢ-ሕጋዊና ኢ-ቀኖናዊ አካሄድ በመኾኑ የጳጳሳት ምርጫ እንዲቆም የፌደራል መንግሥትና የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ለዚህ ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቋል። የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫው ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር ተገቢ ያልኾነ የቤተ ክርስቲያንን ማዕከላዊነት የሚጥስ፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚጎዳና በጦርነት የተጎዳውን ሀብት ንብረቱ የወደመበትን ገዳማቱና አብያተ ክርስቲያናቱ የተጎዱበትን ሕዝብ የማይጠቅም ተገቢነት የሌለው በመሆኑ እንዲቆም ሲል አስረግጦ ተናግሯል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ በማናቸውም ሁኔታ መግባት እንደማይችል በግልጽ ቢደነግግም፣ ተቋማቱን እነደተቋም የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት የሚዘነጋ አይደለም። ኾኖም ግን መንግሥት የቤተክርስቲያኒቱን ሕጋዊ ሰውነትና ሕግ ያጎናጸፋት ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌን ወደ ጎን በማለት ትደፈር ዘንድ በር ከፍቶ እየሠራ የሚገኝ ይመስላል፡፡
ሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ይህን በትግራይ ክልል የተከሰተው ወቅታዊ የቀኖና ጥሰት የቤተክርስቲያኒቱን አንድነትና ሉዓላዊነት የሚፈታተን፤ ማዕከላዊ የመንበረ ፕትርክና መዋቅር የሚንድ አድራጎት እንደኾነ አመላክቶ በክልሉ የሚገኙ ብፁዓን አባቶች የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የከፈተውን የሰላም በር ከመጠቅም ይልቅ በቀኖና ጥሰቱ በመቀጠል፤ ሐምሌ 9/2015 በተደረገ ስብሰባ 10 ቆሞሳትን በዕጩነት ለኤጲስ ቆጶጶስነት ሹመት ምርጫ በማከናወን ለመሾም የያዙትን ዕቅድ አጠናክረው የቀጠሉ መኾኑን ጉባኤው ተገንዝቦ በሰፊው በመወያየት ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት የችግሩን አሳሳቢነት ኹሉን አህጉረ ስብከት ለአደጋ የሚያጋልጥን የቤተክርስቲያኒቱን አንድነትና ሉዓላዊነት የሚፈታተን፣ የቤተክርስቲያኒቱ ማዕከላዊ የመንበረ ፕትርክና መዋቅር የሚንድ አድራጎት እንደመሆኑ መጠን ኹሉም አህጉረ ስብከት ድርጊቱን በመቃወም የሰላም ጥሪ እንዲያስተላልፉ እንዲደረግ፣
የክልሉ ተወላጅ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና በመንበረ ፓትርያርክ የሚገኙ ሊቃውንት ቤተክርስቲያን የድርጊቱን ኢ-ቀኖናዊነት በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት አስመልክቶ በክልሉ ቋንቋ ተደጋጋሚ የሆነ ቀኖና ቤተክርስቲያንን የሚያስጠብቅ አንድነትና ሰላምን የሚያመጣ በትምህርትና መልዕክ በቤተክርስቲያኒቱ ሚዲያ እንዲያስተላልፉ፣ በየደረጃው ያሉ የቤተክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሊቃውንተ ቤተርክስቲያን እና ምዕመናንና ምዕመናት እንዳሁን ቀደሙ ኹሉ በአንድነትና በኅብረት በመቆም ድርጊቱን እንዲቃወሙና በማዕከል ደረጃ የሚተላለፉትን ውሳኔዎች ተግባራዊ በማድረግ ለቤተክርስቲያኒቱ አንድነትና ሉዓላዊነት የበኩላቸውን አስተዋጾ እንዲያደርጉ፤ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር በልዩ ልዩ የሥራ አገልግሎት ላይ የሚገኙ የክልሉ ተወላጆች የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በሚያመቻቸው የውይይት መድረክ የችግሩን አሳሳቢነት አስመልክቶ ግንዛቤ በማስጨበት የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ ጥሪ እንዲተላለፍ፣
በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ላይ እየተከሰቱ ያሉ የሕገ ቤተክርስቲያንና የቀኖና ጥሰቶች ከቤተክርስቲያኒቱም አልፎ ሀገራዊ አንድነትና ሉዓላዊነትን የሚያናጋ ብሎም አገራዊ ቀውስ የሚያስከትል እንደመሆኑ መጠን የፌዴራል መንግሥቱና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለችግሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት የውይይት መድረክ በማዘጋጅት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ እንዲደረግ፣ የሕገ ቤተክርስቲያንና የቀኖና ጥሰት የሚያስከትለውን ቀውስ በመረዳት ዛሬም ድረስ ለቤተክርስቲያናችን አንድነትና ሉዓላዊነት መጠበቅ በሐሳብና በጸሎት ዘወትር የሚተጉ በትግራይ የሚገኙ ሊቃውንት እንዳሉ አስተዳደር ጉባኤው በጽኑ እንደሚያምን ገልጾ ይህ ኃላፊነታቸውም በክልሉ የሚገኙ ምዕመናን በየደረጃው ላሉ የቤተክርስያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች ተገቢውን ምክረ ሐሳብ በመስጠት የተጀመረው የሰላምና የዕርቅ ተልዕኮ ለውጤት እንዲበቃ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፏል፣ በክልሉ የሚገኙ አበው ሊቃነ ጳጳስት ሕገ ቤትክርስቲያንና ቀኖና ቤተክርስቲያንን ጠብቀው በማስጠበቅ በቀኖና ጥሰት “እንሾማለን” የሚሉትን አቁመው የሰላም በራቸውን ለውይይት ክፍት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
