አሜሪካ በኢራን አዲስ ዙር ጥቃት ስትከፍት፤ ቴህራን የባሕረ ሰላጤ አገራትን አጠቃች

Date:

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ዛሬ ምሽት በድጋሚ በኃይልን እንመታቸዋለን” በማለት ከተናገሩ በኋላ፤ የአሜሪካ ጦር ኢራን ላይ አዲስ ዙር ጥቃት ከፈተ።

የሆርሙዝ ወሽመጥ የወደብ ከተሞች የሆኑትን ሲሪክን እና ባንደር አባስን ጨምሮ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍሎች ፍንዳታ መከሰቱን የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ትራምፕ ከአዲሱ ጥቃት በኋላ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ “ይህ ትናንት በኢራን ለተፈጸመው የመርከቦች ድብደባ የተወሰደ የአጸፋ እርምጃ ነው። በድጋሚ ከተፈጠረ፤ ከዚህም የባሰ ይሆናል” ብለዋል።

ከአሜሪካ እርምጃ በኋላ የባህረ ሰላጤው አገራት በኢራን ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አስታውቀዋል። በባህሬን ዋና ከተማ መናማ ፍንዳታዎች መከሰታቸው የተገለጸ ሲሆን ኩዌት ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን ማክሸፏን አስታውቃለች። ኳታር የደኅንነት ማስጠንቀቂያ አውጥታለች።

የኢራን ዋና ተደራዳሪ የሆኑት የፓርላማው አፈ ጉባኤ ሞሀማድ ባገር ጋሊባፍ፤ ዋሽንግተን “ጉልበተኝነት እና ቃል ኪዳንን ማጠፍ ዋጋ የማያስከፍሉ አለመሆናቸውን አሁንም አልተማረችም” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

“በግልጽ ላስቀምጠው፤ ካጠቃችሁ፤ ትመታላችሁ” ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ሆርሙዝ ወሽመጥ የሚከፈተው ኢራን በምትዘረጋው አሰራር እንጂ “በአሜሪካ ዛቻ” እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ጥቃቶቹ የተፈጸሙት “የኢራንን በንግድ መርከቦች እና በንጹኃን ሲቪል ባሕርተኞች ላይ ጥቃት የማድረስ አቅም ይበልጥ ለማዳከም” እንደሆነ አስታውቋል።

ዕዙ ባወጣው መግለጫ በኢራን የሚገኙ 90 ወታደራዊ ዒላማዎችን መምታቱን ገልጿል። በኢራን የባሕር ዳርቻ የሚገኙ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች እና የወታደራዊ ሎጂስቲክስ መሠረተ ልማቶች ጥቃት ከደረሰባቸው ዒላማዎች መካከል እንደሆኑም አስታውቋል።

ዕዙ፤ “የአሁኖቹ ጥቃቶቹ ትናንት ምሽት የታዩትን ስኬታማ የማጥቃት እርምጃዎች የተከተሉ ናቸው” ብሏል።

ኮናራክ እና ቻባሃር የተባሉ ከተሞችን ጨምሮ በሌሎች የኢራን የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች በርካታ ፍንዳታዎች መከሰታቸው ተዘግቧል።

የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደገለጸው ባንደር አባስ ከተማ ውስጥ ስምንት ፍንዳታዎች ተከስተዋል። በደቡብ ኢራን የሚገኙት ሲሪክ እና ጃስክ ወደቦች ደግሞ በሁለት ሚሳዔሎች መመታታቸውን ገልጿል።

ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚወዛገቡበት አቡ ሙሳ ደሴትም ሁለት ጊዜ ጥቃት እንደደረሰበት ተዘግቧል።

የአሜሪካ ጥቃቶች ያደረሱት የጉዳት መጠን እስካሁን አልታወቀም። ይሁን እንጂ ቻባሃር ውስጥ የኃይል መቋረጥ እንዳጋጠመ እና ቡሸህር ውስጥ በሚገኝ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጦር ሰፈር እሳት መነሳቱን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ገልጿል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ጉምሩክ ኮሚሽን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን ገለጸ

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በ2018 በጀት ዓመት 725.25 ቢሊዮን ብር...

ከ1.5 ሚሊዮን ዶላር የአፍሪካ ንፁህ ኢነርጂ ፈንድ አምስቱ አቅኚ የኢትዮጵያ ድርጅቶች ተመረጡ

በምስራቅ አፍሪካ የንፁህ ኢነርጂ አቅርቦትን በማሳደግ የስራ እድልን ለመፍጠርና...

ታላቅ የምስጋና እና የስጦታ መርሃ-ግብር ጥሪ!

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ባለፉት 5 ዓመታት ላበረከቱት ከፍተኛና ታላቅ...

የቀድሞዉ የኢራን ላዕላይ መሪ አያቶላሕ ዓሊ ኻምኔይ ተቀበሩ

ዩናይትድ ስቴትስና እስራኤል ባለፈዉ የካቲት ማብቂያ ላይ የገደሏቸዉ የኢራን...