ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ከፖለቲካ ራሳቸውን አገለሉ

Date:

ላለፉት 5 አስቸጋሪና ፈታኝ ዓመታት (ከ2014 እስከ 2018 ዓ.ም) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውድ ሕዝባችንን በመወከል ያደረግሁትን የፓርላማ ቆይታ ትናንት በይፋ አጠናቅቂያለሁ።

ይህ ምዕራፍ ሲጠናቀቅ፣ ወደዚህ የሕዝብ አገልጋይነት ያመጣኝንና ያለፍኩበትን የ10 ዓመታት የማኅበረሰብ አገልግሎት እና የትግል ጉዞዬን መለስ ብዬ የምመለከትበት አጋጣሚ ሆኖልኛል።

ወደ ፖለቲካ ሕይወት ከመግባቴ በፊት፣ በዩኒቨርሲቲ ከነበረኝ ማስተማርና ኃላፊነት ጎን ለጎን ለ2 ዓመታት በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ትኩረት እንዲያገኝ በአክቲቪዝም እና ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበረሰብ በመመስረት በግንባር ቀደምትነት መርቻለሁ።

ባለፉት 8 ዓመታት ደግሞ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፓርቲ ምስረታ እስከ ከፍተኛ አመራርነት፣ በተለይም ደግሞ ባለፉት 5 ዓመታት በፓርላማ አባልነት ድምፅ ለሌላቸው ወገኖቼ እውነተኛ ድምፅ መሆን በመቻሌ የተሰማኝ ክብርና ኩራት የላቀ ነው።

በነዚህ እጅግ አስቸጋሪ ዓመታት፣ በፈተና እና በጭንቅ ሰዓት ለህዝቤ የገባሁትን ቃል እንድጠብቅ፣ እንዳልናወጥ፣ በቅንነትና በድፍረት የሕዝቤን ችግር እና ስቃይ በታሪክ ፊት እንድመሰክር ፍርሃትን አርቆልኝ ማስተዋልንና ጽናትን ላደለኝ፤ እስከዚች ሰዓትም በሰላም ላደረሰኝ ለቸሩ አምላክ ለልዑል እግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይድረሰው።

ያለ እሱ መለኮታዊ ጥበቃና መሪነት፣ ያለ ቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅርና እናታዊ ምልጃ ይህንን ከባድ የሕዝብ አደራ መወጣት ፈጽሞ አይቻልም ነበር።

የባሕር ዳር ከተማ መራጮቼን ጨምሮ፣ ላለፉት ዓመታት እያንዳንዱን የፓርላማ ውሎዬን እየተከታተላችሁ አስተያየት እና ምስጋና የቸራችሁኝ፣ በተለይም ደግሞ ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ በፊት ለ45 ቀናት በታሰርሁበት ወቅት በጸሎትና በሐሳብ ያገዛችሁኝ ውድ ወገኖቼ፣ በየአጋጣሚው የለገሳችሁኝ ፍቅር ጉልበት ሆኖኝ ዛሬ በኩራትና በነጻ ሕሊና የሕዝብ አገልግሎቴን እንድፈጽም አድርጎኛል። የሕዝብ አገልጋይ መሆን ምንኛ መታደል እና ታላቅ ክብር እንደሆነ በተግባር ያየሁበት አጋጣሚ ነው።

በምክር ቤቱ ቆይታዬ በሀሳብ ለደገፋችሁኝ፣ በሰለጠነ መንገድ አክብሮታችሁን ለገለጻችሁልኝ የተለያዩ ፓርቲዎች የምክር ቤት አባላት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች፣ ለምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች፣ የምክር ቤቱን ውሎዎች በታማኝነት ለዘገባችሁ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተቋማት፣ እንዲሁም ለቅርብ የትግል አጋሮቼ በሙሉ ያለኝ ምስጋና የላቀ ነው።

በትናንትናው የምክር ቤቱ ጉባዔ ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ «አብረን እንስራ» በማለት ላቀረቡልን ጥሪና ላሳዩን አክብሮት ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ከጉባዔው መጠናቀቅ በኋላ ጥያቄ ያቀረብን የተቃዋሚ የምክር ቤት አባላት ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረን የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ላይም በ7ኛው ዙር ምርጫ በባሕር ዳር ከተማ ለመወዳደር ተመዝግቤ ቢሆን ኑሮ እጩ ላለማቅረብ ወስነው እንደነበር ገልጸውልኛል።

በምክር ቤቱ ሳነሳቸው የነበሩ ሀሳቦች ጠቃሚ እንደነበሩ፣ በትኩረት እንደሚወስዷቸው እና በምክር ቤቱ ብቀጥል ፍላጎታቸው እንደነበር የገለጹልኝን ሀሳብም በበጎ ጎኑ እና በቅንነት ተመልክቼዋለሁ።

ይሁን እንጂ፣ ላለፉት 10 ዓመታት የሕዝብን አደራ ለመወጣት ካደረግሁት ከፍተኛ ጥረትና ድካም በኋላ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ውሳኔዬ በሙያዬ ሀገሬን ለማገልገልና ጎን ለጎን ደግሞ ወደ ግሉ ሴክተር በመግባት የማስባቸው የሥራ ውጥኖች (startups) ላይ ለመሰማራት እና ለቤተሰቦቼ በቂ ጊዜና ትኩረት መስጠት መሆኑን በታላቅ አክብሮት ለመግለጽ እወዳለሁ።

ከዚህ የፓርላማ ተሳትፎዬ ማጠናቀቂያ ማግስት ራሴን ከማንኛውም ቀጥተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማገል ሲሆን፣ ለጊዜው በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ በአባልነትም ሆነ በደጋፊነት የማልሳተፍ መሆኑን በይፋ አሳውቃለሁ።

ይሁን እንጂ፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎዬ ቢያበቃም የአማራን ሕዝብ አንድነት በሚያጠናክሩ፣ የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ያለውን አብሮነትና መስተጋብር በሚያሳድጉ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያውያንን ኑሮ በሚያሻሽሉ ማኅበራዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሙያዬ ማድረግ የምችለውን አስተዋጽኦ ሁሉ አደርጋለሁ።

ለሀገሬ ዘላቂ ሰላም፣ ለእውነተኛ ብሔራዊ ውይይትና እርቅ፣ እንዲሁም ለዜጎች የኑሮ ሁኔታ መሻሻል ያለኝ መሻት አሁንም ወደፊትም ጽኑ ነው።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
በአዲሱ የ2019 ዓ.ም ለሀገራችን እውነተኛ የሰላም፣ የፍቅር እና የተስፋ ዘመን ይሁንልን!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ንባብ ለሕይወት  እየመጣ ነው !!!

በንባብ ለሕይወት ፕሮጀክትና በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት አዘጋጅነት የሚካሄደው...

“ወጣቱን በጉልበት እያፈሱ ወደ ጦርነት እየነዱት ነው!”

"ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት በትግራይ፦ የመገናኛ ብዙኃን እና የማኅበረሰብ አንቂዎች...

ለኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ ሶፍትዌር አቅራቢዎች እስከ 250 ሺህ ዶላር ዋስትና

የገቢዎች ሚኒስቴር በታክስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለመሰማራት በሚፈልጉ የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ...